1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ክርስትያን ታደለ ያለመከሰስ መብት ተነሳ

ሐሙስ፣ መጋቢት 5 2016

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የፌዴራል የክልሎችና የከተማ መስተዳድር 5 የምክር ቤት አባላት መካከል የ ሦስቱ ያለመከሰስ መብት ባለፈው ሳምንት ተነስቷል።ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት መነሳቱ ካልቀረ እስካሁን በእሥር ላይ ሆነው የተንገላቱበት ሁኔታ ትክክል እንዳልነበር ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4dVe2
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

የአቶ ክርስትያን ታደለ ያለመከሰስ መብት ተነሳ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የአቶ ክርስትያን ታደለ ያለመከሰስ መብታቸው ተነሳ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ጉባኤ የፍትሕ ሚኒስቴር ያቀረበለትን የምክር ቤት አባሉን ያለመከሰስ መብት የማንሳት ጥያቄ ተቀብሎ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል። 45 የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት በዛሬው ይምክር ቤቱ ጉባኤ የአቶ ክርስትያን ታደለ ያለመከሰስ መብት በ2 ተቃውሞ እና በ2 ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል ። በአስቸካይ ጊዜ ዐዋጁ የተያዙት አቶ ክርስትያን ታደለ በአማራ ክልል መንግሥትን በኃይል ለመጣል በሚደረግ የፀረ ሰላም ኃይላት በተባለ እንቅስቃሴ ውስጥ ትስስር ያላቸው እና መመሪያ የሚሰጡ ሆነው መገኘታቸው በፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ማረጋገጡን ተከትሎ ክስ ለመመስረት ይህንን ጥያቄ ማቅረቡን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ያለመከሰስ መብቱን ያስነሳው ክስ ምን ይላል ?

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ አቶ ክርስትያን ታደለ ጎጃም ውስጥ ቋሪት እና ደጋዳሞት በተባሉ አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ትዕዛዝ መስጠታቸው ተጠቅሷል። ተጠርጣሪው ፈፀሙት የተባለው ድርጊት የሽብር ድርጊትን ለመከላከል የወጣውን እና የወንጀል ሕግን የሚጥስ እና "የሚያስከስስ ከባድ ወንጀል ነውም" ተብሏል።
የፌዴራል ፖሊስ "የምርመራ መዝገብ እንደሚያሳየው ተጠርጣሪው በአማራ ክልል ተደራጅቶ ሕገ - መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል ለመናድ የሚንቀሳቀስ የፀረ ሠላም ኃይል ጋር ትስስር ያለው እና ለዚህ ቡድን መመርያ የሚሰጥ መሆኑን ተረድተናል" ብለዋል ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የምክር ቤት አባላት ጉዳይ

የምክር ቤት አባላት አስተያየት 

የምክር ቤት አባላት ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር ያለመከሰስ መብታቸው በዘፈቀደ እንደማይነሳ በሕገ - መንግሥቱ አንቀጽ 54 ተደንግጓል። ዛሬ በጉባኤው ከተሳተፉ 245 የምክር ቤቱ አባላት አስተያየት የሰጡት ሦስት አባላት ብቻ ናቸው። ይሄው ጥያቄም ቀርቦ ነበር።
"የምክር ቤት አባሉ ከታሰረ ሰባት ወር ሆኖታል። አላነሳንም። የሚያስችል ሆኖ በሕገ መንግሥት የተቀመጠውን ሳናሟላ ለምን እስካሁን ቆየ? "የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በጣም አፋኝ ከመሆኑ የተነሳ እዚህ የምንናገረው ተቃውሞ ሳይቀር ያስጠይቃል። የአስቸኳይ ጊዜ ሕጉ ሁሉንም ነገር ይፈቅዳል። ግን በሕጉ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንችላለን ብለን የሚደረግ ከሆነ አገሪቷን ለማያባራ ብጥብጥ ነው የምንዳርጋት"

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምስል Solomon Muchie/DW

ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ 

ያለመከሰስ መብት ጥያቄው እንዲነሳ ለምክር ቤቱ ጥያቄ ያቀረቡት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሜትዮስ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል።
በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ "በቅርብ ወራት ውስጥ ያበቃል የሚል ግምት ስላለን የክስ ሂደቱ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁም ካበቃ በኋላ  ሊቀጥል ስለሚችል በዚህ ረገድ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ለመድፈን ነው ይሄንን ጥያቄ ያቀረብነው"።

የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት መነሳት


የኢትዮጵያ መንግሥት በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው የፌዴራል፣ የክልሎች እና የከተማ መስተዳድር አምስት የምክር ቤት አባላት መካከል የ ሦስቱ ያለመከሰስ መብት ባለፈው ሳምንት ተነስቷል። በዚህ ጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት ለዶቼ ቬለ አስተያየት የሰጡት ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት መነሳቱ ካልቀረ እስካሁን በእሥር ላይ ሆነው የተንገላቱበት ሁኔታ ትክክል እንዳልነበር ገልፀዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉት አምስቱም የምክር ቤት አባላት ጠበቃ የማግኘትም ሆነ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸውን ተነፍገዋል። 

እስካሁን ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው የምክር ቤት አባላት 

ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተከትሎ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሃንስ ቧያለው ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል እና የሰላም ሚኒስትር ድዔታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ካሳ ተሻገር ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቷል።

ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ