1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

Hirut Melesseዓርብ፣ ግንቦት 23 2016

አርዕስተ ዜና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ዛሬ ወደ ፓርላማ የመራው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ማሻሻያ ህወሓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሆኖ እንዲመዘገብ መንገድ የሚከፍት ነው። በደቡብ አፍሪቃው ምርጫ የድምጽ ቆጠራ ኤ ኤን ሲ ከ50 በመቶ በታች ድምጽ ማግኘቱ ከታወቀ በኋላ ሌሎች ፓርቲዎች ዛሬ የጥምረት ንግግር ለማካሄድ ዝግጅት መጀመራቸው ተሰማ ። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀረቡባቸው 34 ክሶች በሙሉ ጥፋተኛ በመባላቸው ላይ የተለያዩ መንግስታትና የፓርቲዎች መሪዎች አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።

https://p.dw.com/p/4gW22

አዲስ አበባ    32ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች

 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ማሻሻያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ወሰነ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ዛሬ ወደ ፓርላማ የመራው ማሻሻያ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሆኖ እንዲመዘገብ መንገድ የሚከፍት ነው።

አዋጁ የሚሻሻለው “ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል” አሰራር ስላልነበረው እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው ማሻሻያ የተጠቀሱት የፖለቲካ ቡድኖች “በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል” እንደሆነ መግለጫው ይጠቁማል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ የምክር ቤቱን ውሳኔ “ሰላምን ለማጠናከር በትክክለኛው አቅጣጫ የተወሰደ አንድ እርምጃ” ብለውታል።

ህወሓት “የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል” ተብሎ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው በጥር 2013 ነበር።

 

አዲስ አበባ    ምርጫ ቦርድ የአራት ክልሎችን ምርጫ በአንድ ሳምንት አራዘመ

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአራት ክልሎች ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ የሚካሔድበትን ቀን ወደ ሰኔ 16 ቀን 2016 አራዘመ። ምርጫው ሰኔ 9 ቀን 2016 ሊካሔድ ቀነ ቀጠሮ ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም ከሐይማኖታዊ በአል ጋር ስለተገጣጠመ መራዘሙን ቦርዱ ዛሬ አርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።በአዲሱ መርሐ ግብር መሠረት ከሁለት ሣምንታት በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ክልሎች ቀሪ በጅግጅጋ 2 እና መስቃን እና ማረቆ ምርጫ ክልሎች የድጋሚ ምርጫ ይካሔዳል። 

 

ሚድራንድ       የደቡብ አፍሪቃ ፓርቲዎች የጥምረት ንግግር ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ናቸው ተባለ

 

በእስካሁኑ የደቡብ አፍሪቃው ምርጫ የድምጽ ቆጠራ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በእንግሊዘኛው ምህጻር ANC ከግማሽ በታች ድምጽ ማግኘቱ ከታወቀ በኋላ በምርጫው የተሳተፉ ሌሎች ፓርቲዎች ዛሬ የጥምረት ንግግር ለማካሄድ ዝግጅት መጀመራቸው ተሰማ ።  በ57.3 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች በተካሄደ ቆጠራ ውጤት መሠረት ኤ.ኤን.ሲ 41.9 በመቶ ድምጽ ብቻ ነው ያገኘው። ይህም በጎርጎሮሳዊው 2019 በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ፓርቲው ካገኘው 57.7 በመቶ ድምጽ እጅግ ያነሰ ነው። ዴሞክራሲያዊ ኅብረት በምህጻሩ DA የተባለው ፓርቲ  በ23.4 በመቶ ድምጽ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ጄኮቡ ዙማ የሚመራው ኡምክሆንቶ ዊ ሲዝቬ በምህጻሩ MK የተባለው አዲስ ፓርቲ ደግሞ 11.3 በመቶ ድምጽ አግኝቷል። ፓርቲው በተለይ በዙማ የመኖሪያ ከተማ ክዋዛሉ ናታል የኤ.ኤን.ሲ ደጋፊዎችን ድምጽ መውሰድ እንደቻለ ተዘግቧል። የዴሞክራሲያዊ ኅብረት ፓርቲ መሪ ጆን ስቲንሁዊሰን እለቱን ለደቡብ አፍሪቃ በጣም ጥሩ ቀን ብለውታል። ነገ ደግሞ የተሻለ እንደሚሆን በመጠቆም የምርጫው ውጤት ለደቡብ አፍሪቃ አዲስ የፖለቲካ ምኅዳር ይከፍታል ብለዋል።

«ባለፉት 30 ዓመታት ደቡብ አፍሪቃን መታደግያው መንገድ የኤ.ኤን.ሲን አብላጫ ድምጽ መስበር ነው ብለን ነበር። እናም አሁን የእነርሱ መጨረሻ አነስተኛ አርባ በመቶዎቹ ድምጽ ይሆናል። ይህም መሰናክሎቹን በመስበር እና ለደቡብ አፍሪቃውያንና ለሀገራችን ህዝብ የተሻለ ነገር መገንባት ለመጀመር ፣ በግልጽ በደቡብ አፍሪቃ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ይከፍታል።»

ኤ.ኤን.ሲ የአናሳ ነጮች አገዛዝ ካበቃበት ከታሪካዊ የጎርጎሮሳዊው 1994ቱ የደቡብ አፍሪቃው ምርጫ በኋላ የተካሄዱ ምርጫዎች አሸናፊ ነበር። ባለፉት አሥር ዓመታት ደቡብ አፍሪቃውያን የኤኮኖሚያቸው እድገት መገታት፣ ስራ አጥነት፣ እና የተባባሰው ድኅነትና የመሠረተ ልማት መንኮታኮት ያስከተለው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሲያማርራቸው ቆይቷል። ከአሁኑ ምርጫ ውጤት በመነሳት ኤ ኤን ሲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሊጣመርና በመንግሥቱ ውስጥ ሊቆይ እንደሚችል ወይም በዝግ ስብሰባ ከሌሎች ጋር ድርድሮች እየተካሄዱ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ግምቶች እየተሰነዘሩ ነው። ይሁንና ስቲንሁዊሲን ፓርቲያቸው DA በጥምረት ንግግሩ ውስጥ መኖር አለመኖሩን ሲጠየቁ የለም ሲሉ መልሰዋል።

ዱባይ የየመን ሁቲዎች በአሜሪካኑ አይዘናወር የጦር መርከብ ላይ የሚሳይል ጥቃት አደረስን አሉ

የየመን ሁቲዎች አይዘናወር በተባለው በአሜሪካኑ የጦር አውሮፕላኖች ጫኝ መርከብ ላይ የሚሳይል ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ። የየመን ሁቲዎቹ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ዛሬ እንዳሉት የሚሳይል ጥቃቱ በቀይ ባህር በጦር አውሮፕላኖች ጫኟ መርከቧ አይዘናወር ላይ የተፈጸመው ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ በየመን ለፈጸሙት ጥቃት አጸፋ ነው። ቃል አቀባዩ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ  በየመን በፈጸሟቸው ስድስት ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 16 ሰዎችን መግደላቸውንና 41 ደግሞ ማቁሰላቸውን ተናግረዋል።በሆዴይዳ ክፍለ ግዛት በሚገኘው ሳሊፍ ወደብ ላይ ባነጣጠረው  በዚሁ ጥቃት አል ሀውክ በተባለው ወረዳ የሚገኝ የራድዮ ህንጻና የግሀሊፋ ካምፕና ሁለት ቤቶችም መውደማቸውንም ገልጸዋል። ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ የሚሊሽያዎቹ ቡድን በቀይ ባህር በሚቀዝፉ መርከቦች ላይ ተጨማሪ ችግር እንዳያስከትል ለማድረግ በሁቲ ዒላማዎች ላይ ጥቃቱን መጣላቸውን አስታውቀዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ እዝና የብሪታንያ ኃያላት ሁቲዎች የሚቆጣጠሩዋቸውን 13 ዒላማዎችን መተናል ብለዋል። የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች  ካለፈው ህዳር አንስቶ በቀይ ባህር የሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው። ይህ የሚያደርጉትም በእስራኤል ሀማስ ጦርነት ለፍልስጤማውያን ድጋፋቸውን ለመግለጽ መሆኑን ይናገራሉ። 

 

ኒውዮርክ  በትራምፕ ላይ ስለተላለፈው የጥፋተኝነት ብይን የሰጡ አስተያየቶች

 

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአንድ የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት በቀረቡባቸው 34 የክስ መዝገቦች  በሙሉ ጥፋተኛ በመባላቸው ላይ የተለያዩ መንግስታትና ፓርቲዎች መሪዎች አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ትራምፕ ጥፋተኛ የተባሉት የተጭበረበረ የሒሳብ ሰነድ አቅርበዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ነው። ትራምፕ ክሱንም ሆነ ውሳኔውን «ህገወጥና አሳፋሪ» ብለውታል።

«አሳፋሪ ነው። ይህ በሙሰኛ የተወዛገበ ዳኛ የተጭበረበረ የፍርድ ሂደት ነበር ። የተጭበረበረ የተጭበረበረ የፍርድ ሂደት ነበር። ለኛ የለውጥ መድረክ አይሰጡንም በዚህ ወረዳ በዚህ አካባቢ አምስት ወይም 6 በመቶ ነበርን። ትክክለኛው ፍርድ  ህዳር አምስት ቀን ህዝቡ የሚሰጠው ነው የሚሆነው። እዚህ የሆነውን ያውቃሉ። ሁሉም እዚህ የሆነውን ያውቃል ።»

ስለ ውሳኔው የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በሰጡት አስተያየት « የፖለቲካ ተቀናቃኞችን  በሁሉም መንገድ በሕጋዊው ሆነ ሕጋዊ ባለሆነ መንገድ በቀላሉ ማስወገድ ግልጽ ነው ብለዋል። የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን የተከበሩ ሰው፣ ሁሌም አሜሪካንን የሚያስቀድሙ ሲሉ አወድሰው ህዝቡ በመጪው ህዳሩ ምርጫ እንዲወስን ይተውለት፤ ሚስተር ፕሬዝዳንት ትግልዎን ይቀጥሉ ሲሉ አበረታተዋቸዋል።

ተቃዋሚው የብሪታንያ ሌበር ፓርቲ መሪ ኬይር ስታርመር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ገልጸው ከአሁን በኋላ የመጨረሻ ፍርድና ይግባኝም ሊኖር ይችላል። የቀድሞ የብሬግዚት ፓርቲ መሪ ኒጌል ፋራጅ የችሎቱን ውሳኔ በፖለቲካዊ ተነሳሽነት የተወሰነ ሲሉ አጣጥለዋል። የኢጣልያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሳልቪኒ ለዶናልድ ትራምፕ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸው ትራምፕ የፍትህ ወከባ ሰለባ እንደሆኑና እና ሂደቱም ፖለቲካዊ ባህርይ እንደነበረው ገልጸዋል። ትራምፕ እንደሚያሸንፉ ተስፋቸውን ገልጸው ይህም ለታላቅ መቻቻል ዋስትና የሚሰጥና ለዓለም ሰላምም ተስፋ ነው ብለዋል። ጃፓን በበኩልዋ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች

 

ኦስሎ   አትሌት ሐጎስ ገብረህይወት በ5 ሺህ ሜትር ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት አስመዘገበ

 

አትሌት ሐጎስ ገብረህይወት በ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር የዓለም ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በስመዝገብ አሸነፈ። ትናንት ኦስሎ ኖርዌይ የተካሄደውን የዳይመንድ ሊግ የ5 አምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ሐጎስ በ12 ደቂቃ 36.73 ሴኮንድ በመጨረስ ነው ያሸነፈው። አትሌቱ በኦሎምፒክ ሻምፕዮናው በጆሹዋ ቼፕቴጊ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን ለመስበር ከሁለት ሰከንድ ያነሰ ጊዜ ብቻ ነበር የቀረው። ሆኖም  ለበርካታ ዓመታት በአንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የነበረውን የኢትዮጵያን ክብረ ወሰን ማሻሻል ችሏል። ዮሚፍ ቀጀልቻ ርቀቱን በ12 ደቂቃ 38 ሰከንድ በመጨረስ ሁለተኛ  ወጥቷል አዲሱ ይሁኔ ደግሞ በ12:49.65 ማይክሮ ሰከንድ 4ኛ ሆኗል።

 

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።