1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseዓርብ፣ ሐምሌ 26 2016

የአርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓም አርዕስተ ዜና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉ አንዳንድ ቡድኖች ጋር ውይይት መጀመሩን ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸው በክልሉ ነዋሪዎች አስተያየት እየተሰጠበት ነው። አንዳንድ የክልሉ ነዋሪዎች ሃሳቡን የተቀደሰ ሲሉ ፣ሌሎች ደግሞ ጥርጣሬ ገብቷቸዋል። በግጭት በተመሰቃቀለው በዳርፉር በሚገኘው ዘምዘም መጠለያ ኮሌራና ሌሎች መሰል በሽታዎች እንዳይሰፋፉ አስግቷል። ረቡዕ ቴህራን ውስጥ በአየር ጥቃት የተገደሉት የሃማስ ከፍተኛ መሪ የኢስማኤል ሀኔይ አስከሬን ሽኝትና ስርዓተ-ቀብር በስደት ይኖሩበት በነበረው በዶሀ በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ዛሬ ተፈጸመ።

https://p.dw.com/p/4j3UF

አዲስ አበባ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ «ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉ አንዳንድ ቡድኖች ጋር ውይይት መጀመሩን» ተናገሩ 

 

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መቀጠሉ እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤በክልሉ ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉ አንዳንድ ቡድኖች ጋር ውይይት መጀመሩን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ  ለመጀመሪያ ጊዜ ፍንጭ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ያሉት ስለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ-ግብር ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

በዚህ ላይ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች ሃሳቡን መልካም ሲሉ Ŕd,ገፉ ሲሆን፤  አንዳንዶች ደግሞ በተባለው ነገር ላይ ጥርጣሬ ገብቷቸዋል። የፌደራል መንግሥት የክልሉን ልዩ ኃይል እና የፋኖ ታጣቂዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል የተጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ንፁሃንን ጭምር እየቀጠፈ ዓመት አልፎታል።

ዘምዘም መጠለያ   በሱዳኑ ዘምዘም የተፈናቃዮች መጠለያ የጎርፍ አደጋ ያስከተለው ስጋት

ርካታ አዳዲስ ተፈናቃዮች የሚጎርፉበት በግጭት በተመሰቃቀለው በዳርፉር ሱዳን የሚገኘው ዘምዘም መጠለያ የጎርፍ አደጋ ያስከተላቸው ችግሮች አስግተዋል። ጎርፉ በመጠለያው የሚገኝ ውሀንን መጸዳጃንም ሊበክል ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። ዬል የተባለው ሰብዓዊ  የምርምር ላቦራቶሪ ደረስኩበት ባለው ግኝት በመጠለያው የሚገኙ መጸዳጃ ቤቶችና አብዛኛዎቹ ውሀ የሚገኝባቸው ስፍራዎች በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው ኮሌራና ሌሎች መሰል በሽታዎች እንዳይሰራጩ አስግቷል። ይህም በእጅጉ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለተጎዱት በመጠለያው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከባድ ችግር መሆኑም ተዘግቧል። 500 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግደው መጠለያው በሱዳኑ ጦርነት ምክንያት አሁን በእጅጉ ተጨናንቋል። በዚያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች አንዷ የምግብና የጤና አገልግሎች በእጅጉ ያስፈልገናል ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

 

አቡጃ    የናይጀሪያን የኤኮኖሚ ማሻሻያ ተቃውመው ሰልፍ ከወጡ መካከል 13 ተገደሉ

 

በናይጀሪያው የኤኮኖሚ ቀውስ ሰበብ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት ከፖሊስ ጋር በተነሳ ግጭት ቢያንስ 9 ሰዎች መገደላቸውን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ አስታወቀ። ባለሥልጣናት ደግሞ በግጭቱ አንድ ፖሊስ መገደሉን እና ሌሎችም መቁሰላቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ሌላ ባለስልጣናት እንዳሉት በሰሜን ምሥራቅ ናይጀርያ ግዛት ቦርኖ በፈነዳ ቦምብ 4 ተቃዋሚዎች ተገድለዋል፤ 34 ደግሞ ቆስለዋል።  የአምነስቲ የናይጀሪያ ቅርንጫፍ ሃላፊ ኢሳ ሳኑሲ እንዳሉት ተቋማቸው ስለ ግድያው ከዓይን ምስክሮች ከሰለባዎቹ ቤተሰቦች እና ከጠበቆች የደረሰውን መረጃ በገለልተኝነት እያጣራ ነው። ከአፍሪቃ በህዝብ ብዛት ቀዳሚዋ በሆነችው በናይጀሪያ ታቃዋሞው የተነሳው በዋነኝነት በምግብ እጥረት በመልካም አስተዳደር እጦት እና በሙስና መስፋፋት ነው። ጥቂት የማይባሉ ድሆችና ረሀብተኞች የሚገኙበት የናይጀሪያ ባለሥልጣናት ከሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት የተሻለ ተከፋይ ናቸው ። የሐገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስ ሃላፊ ትናንት ማታ እንደተናገሩት በተጠንቀቅ ላይ የሚገኘው ፖሊስ የጦር ኃይሉ እገዛ ሳያስፈልገው አይቀርም። ወጣቶች የሚያመዝኑባቸው እነዚሁ ሰልፈኞች ከሚያሰሟቸው መፈክሮች ውስጥ የተነሳው የጋዝና የኤሌክትሪክ ድጎማ ይመለስ የሚል ይገኝበታል።በኤኮኖሚ ማሻሻያው ከተሰረዙት መካከል ይህ ድጎማ ይገኝበታል።

ታሊን ኤስቶንያ        ሞስኮ ከእስር ከተለቀቁት ዜጎቿ የደኅንነት ሠራተኞቿ እንደሚገኙበት አስታወቀች

ምዕራቡ ዓለምና ሩስያ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ትልቁ ከተባለው የትናንቱ የእስረኞች ልውውጥ በኃላ  ክሬምሊን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሩስያውያኑ እስረኞች አንዳንዶቹ የደኅንንነት መስሪያ ቤቷ ሠራተኞች እንደነበሩ አሳወቀች።የክሬምሊን  ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት  በልውውጡ ከተለቀቁት 8 ሩስያውያን እስረኞች መካከል ሰው በመግደል ጀርመን ውስጥ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የነበረው ቫዲም ክራሲኮቭ የሩስያ ፌደራል ደኅንነት አገልግሎት መኮንን ነበር። አሶስየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ሞስኮ ግን ከዚህ ቀደም እስረኞቹ ከመንግሥት ጋር ንክኪ የላቸውም ብላ ነበር። ክራሲኮቭ የዛሬ አምስት ዓመት አንድ የቀድሞ የቼችንያ ተዋጊን ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ በመግደል ጀርመን ውስጥ የእድሜ ልክ እሥራት ተፈረዶበት ነበር። የጀርመን ዳኞች ያኔ ግድያው የተፈጸመው በሩስያ ባለስልጣናት ትዕዛዝ ነው ብለው ነበር። ባልታሰበው የእስረኞች ልውውጥ ከተለቀቁት መካከል ሩስያ ውስጥ ታስረው የነበሩት አሜሪካውያኑ ጋዜጠኞች ኢቫን ጌርሽኮቪች እና  አልሱ ኩርማ የቀድሞ ባህር ኃይል ባልደረባ ፖል ውሄላን ትናንት ምሽት ሜሪላንድ ዩናይትድ ስቴትስ ሲደርሱ ቤተሰቦቻቸውና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተቀብለዋቸል።የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ትናንት ነጻ የወጡ የሩስያ እስረኞችን በሞስኮ ቭኑኮቮ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው  አቀባበል አድርገውላቸዋል። ፑቲን በዚሁ ወቅት ለተለቀቁት ሩስያውያን መንግሥት ሽልማት እንደሚሰጣቸውና ስለ ወደፊቱ እጣ ፈንታቸውም እንደሚያነጋግሩዋቸው ቃል ገብተውላቸዋል። በእስረኞች ልውውጡ ሞስኮ 15 አሜሪካውያን ጀርመናውይናን የሩስያ ዝርያ ያላቸውን ሰዎች ለቃለች። ቤላሩስ ደግሞ ሌለ የጀርመን ዜጋ ለቃለች።

 

ዶሀ    የሀኔይ ሽኝትና ስርዓተ-ቀብር

ቴህራን ኢራን ውስጥ ባለፈው ረቡዕ በአየር ጥቃት የተገደሉት የሃማስ ከፍተኛ መሪ ኢስማኤል ሀኔይ ሽኝትና የቀብር ስነ ስርዓት በስደት ይኖሩበት በነበረው በዶሀ ዛሬ ተፈጸመ። በርካታ ሀዘነተኞች ከቀብሩ በፊት በዶሀው ትልቁ የኢማም አብዱል ዋሀብ መስጊድ በተካሄደው የፀሎት ስነ ስርዓትና ሽኝት ላይ ተካፍለዋል።  በፍልስጤም ባንዲራ የተሸፈኑት የሀኔይና የጠባቂያቸውን አስከሬኖች የያዙት ሳጥኖች ፊት ወንዶች ተንበርክከው ሲጸልዩ መቀመጫው ኳታር የሆነው እስራኤል፦ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን የሐማስ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪዎች ደግሞ ለሀኔይ ቤተሰቦች ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ከመካከላቸው እርሳቸውን ይተካሉ የተባሉት ክሃሊ አልሀያ የሀማስ ከፍተኛ ባለሥልጣንና የቀድሞው የሐማስ ሃላፊ ካሌድ ማሻል ይገኙበታል። በጸሎትና ,ቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የቀጠርና የየሌሎች አረብ ሀገራት ባለስልጣናት ተገኝተዋል። ቀብራቸውም ሰሜን ዶሀ በምትገኘው ሉሴይል በተባለችው ከተማ ተፈጽሟል። ስነስርዓቱ በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ማካሄዱን የዘገበው የቀተር መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀብሩ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ብቻ እንደሚፈጸም አስታውቆ ነበር።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።