1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሳምንት የአራት ቀን ስራ የሙከራ ፕሮጀክት በጀርመን

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥር 24 2016

ከትናንት ጀምሮ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ 45 ድርጅቶች በአንድ የሙከራ ፕሮጀክት መሳተፍ ጀምረዋል። ይኼውም ሰራተኞቻቸው እንደተለመደው በሳምንት አምስት ቀናት ሳይሆን አራት ቀናት ብቻ እየሰሩ ተመሳሳይ ደሞዝ ይከፈላቸዋል። የዚህ የሙከራ ፕሮጀክት ዓላማ ለሰራተኛው ተጨማሪ የዕረፍት ቀን መጨመር ብቻ ሳይሆን የድርጅቱንም ምርታማነት ማሳደግ ነው።

https://p.dw.com/p/4bx5U
ባዶ ቢሮ
ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ሰዎች በብዛት ከቤት መስራት ጀምረዋል።ምስል Ute Grabowsky/imago images/photothek

በሳምንት የአራት ቀን ስራ የሙከራ ፕሮጀክት በጀርመን

በሳምንት አራት ቀናት ብቻ ሰርቶ ለአምስት ቀናት መከፈል በርካታ ተቀጣሪ ሰራተኞችን ሊያጓጓ ይችላል። ጤና ይስጥልኝ ውድ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች፤  የጎርጎሮሲያኑ የካቲት ወር ትናንት ከጀመረ አንስቶ  45 የጀርመን ድርጅቶች  ለግማሽ ዓመት ያህል የሚሳተፉበት የሙከራ ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪ ነው ተብሎ ይጠበቃል። በሳምንት አራት ቀናት ብቻ መስራት የሰራተኛውን ምርታማነት ያሳድጋል፣ ከዚህም በተጨማሪ የሀገሪቱን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ለመቅረፍ ይረዳል ሲሉ አንዳንድ የሰራተኛ መብት ተሟጋቾች ይከራከራሉ። 


ምርታማነት ምንድን ነው? 


 ጀርመን ላለፉት ጥቂት አመታት ዝቅተኛ ምርታማነት አስመዝግባለች። ለዚህም አንዱ ምክንያት ከፍተኛ የኩባንያዎች የሃይል ወጪ ነው። የሰራተኛ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ሰራተኞች በአምስት ፈንታ በሳምንት አራት ቀናት ብቻ የሚሰሩ ከሆነ የበለጠ የስራ ተነሳሽነት ሊኖራቸው እና የበለጠ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው። በዛ ላይ ደግሞ በሀገሪቱ ያለውን የሰራተኛ እጥረት ለመቅረፍ ያግዛል ባይ ናቸው።
ሬድዋን በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ኢትዮጵያዊ ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራል። በአንዳንድ የጀርመን መሥሪያ ቤቶች አሁን መሞከር የተጀመረው የአሰራር ሁኔታ የግድ እሱ በሚሰራበት መሥሪያ ቤት ባይሆንም በበርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚታሰብ ነው ይላል። « ለምሳሌ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሰው ጠዋት ይገባል ይፈርማል። ያን ያህል ጫና የለባቸውም። የሳምንቱን ስራ በሶስት ቀናትም ሊጨርሱ ይችላሉ። ይህ ግን ባንክን የመሳሰሉ መሥሪያ ቤቶችን አይጨምርም።  በNGO ደግሞ የበለጠ የሚያተኩረው ውጤቱ ላይ ነው። እኔ አሁን ቢሮ መግባቴ ሳይሆን ከኔ የሚጠበቀው በታቀደው መሰረት ስራ ተሰራ ወይስ አልተሰራም የሚለው ነው።» ይላል ሬድዋን።  መንግሥት ሊያሻሽል ብዙ ይሞክራል የሚለው ሬድዋን እስካሁን ግን« እየተሻሻለ ሳይሆን እየባሰበት» ነው ይላል።


በተጨባጭ በሳምንት የ4 ቀን ስራ የተሞከረባቸው የሌሎች ሀገር ተሞክሮ ምን ይመስላል?


እንደ ታላቋ ብሪታንያ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ አውስትራሊያ፣ አየርላንድ እና ዩናይትድ ስቴትስ ባሉ ሀገራትም ከጎርጎሮሲያኑ 2019 ዓ ም አንስቶ ተመሳሳይ ሙከራዎች ተደርገዋል። በሙከራ ፕሮጀክቱ ላይ ከ 500 በላይ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን ሰራተኞቻቸውም ከሙከራ ባለፈ እንደዚህ አይነት አሰራር እንዲቀጥል ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
በታላቋ ብሪታንያ ለምሳሌ 3,000 የሚጠጉ ሰራተኞች የተሳተፉበት ሙከራን በሚመለከት የካምብሪጅ እና የቦስተን ተመራማሪዎች ይፋ እንዳደረጉት 40% የሚጠጉ ተሳታፊዎች ከሙከራው በኋላ የጭንቀት ስሜታቸው እንደቀነሰ እና የስራ መልቀቂያ የሚያስገቡት ቁጥር በ57 በመቶ ቀንሷል ይላሉ።  ከዚህም ሌላ በህመም ምክንያት የሀኪም ፍቃድ አግኝተው የሚቀሩ ሰራተኞችም ቁጥር በሁለት ሶስተኛ ቀንሷል። 

በርሊን፤ ሀኪሞች ለ 4 ቀናት ስራ በሳምንት ሰልፍ ወጥተው
በርሊን፤ ሀኪሞች ለ 4 ቀናት ስራ በሳምንት ሰልፍ ወጥተውምስል Fabian Sommer/dpa/picture alliance


26 ቢሊዮን የሚያወጣ የሀኪም ፍቃድ


ከጀርመን የጤና መድህን ኩባንያ DAK በቅርቡ የተገኘ አንድ መረጃ እንደሚጠቁመው በጀርመን ያሉ ሰራተኞች ባለፈው ዓመት በአማካይ 20 ቀናት የሀኪም ፍቃድ አግኝተው ከስራ ቀርተዋል። ይህ በምርት ሲገመት እ.ጎ.አ. በ 2023 በጀርመን አጠቃላይ የ 26 ቢሊዮን ዩሮ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አስከትሏል ሲል VFA የተሰኘ አንድ የጀርመን የጥናት ማህበር ገልጿል። የኢኮኖሚውንም ውጤት በ0.8 በመቶ ዝቅ ያደርገዋል።

በሳምንት አራት ቀናት ብቻ መስራት ምርታማነትን አይጨምርም የሚሉም አሉ። የምጣኔ ሀብት ምሁር ቤርንድ ፊትዝንበርግ እንደሚሉት ኩባንያዎች የአራት-ቀን ስራን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብለው ለከፍተኛ ወጪ ሊዳረጉ ይችላሉ » ባይ  ናቸው። ይኼውም በአምስት ቀናት ይመረት የነበረውን በአራት ቀናት ለማካካስ ሊከብድ ስለሚችል እና ሰራተኞች ትርፍ ሰዓት ለሚሰሩበት ተጨማሪ ወጪ መክፈል ግድ ስለሚል ነው። ኤንዞ ቬበር በሬግንስቡርግ ዩንቨርስቲ የስራ መስክ ተመራማሪ ናቸው። የስራ ሰዓትን መቀነስ አዲስ የስራ ሀሳቦችን ለማፍለቅ የማያበረታታ እና የሰራተኛውን ሙሉ ትኩረት ስለሚጠይቅ የማህበራዊ ግንኙነቱ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚፈጥር ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።  

«ትንሽ ሰርተን ብዙ እናገኛለን ማለት አይደለም»


በጀርመን የኢኮኖሚ ምሁር የሆኑት ዶክተር ፀጋዬ  ደግነህ የዚህ የስራ ሙከራ «ትንሽ ሰርተን ብዙ እናገኛለን ማለት አይደለም» ሲሉ ያብራራሉ፤ « የስራ ሰዓት አጠረ ማለት ሰው ያነሰ ይሰራል ማለት አይደለም። በ40 ሰዓት የሚጠበቅበትን በ 32 ሰዓት ማምጣት እንዲችል  በአርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ እየታገዙ መስራት የሚችሉበት አጋጣሚ ሲኖርም እንደሆነ ዶክተር ፀጋዬ ገልፀዋል። ምርታማነትን በተመለከተ ዶክተር ፀጋዬ የግድ አምስት ቀናት መስራት ሳይሆን ውጤት ተኮር ስራ ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ። « በፊት ላይ ከቤት መስራት የማይታሰብ ነበር።  ሰው ቤቱ ሆኖ አለቃው ሳያየው እንዴት ይሰራል ይባል ነበር። ነገር ግን ቴክኖሎጂው በፈጠረው ነገር እነዚህ ነገሮች አቋራጭ ማግኘት ችለዋል።  ይላሉ።  ሰው በፈለገው ሰዓት ገብቶ አጥጋቢ ስራ መስራቱ ቢበረታታ ጥሩ እንደሆነ የሚመክሩት ዶክተር ፀጋዬ « ከግዴታ ተኮር ውጤት ተኮር ፤ ከቁጥጥር ይልቅ ወደ መተባበበር» የመፍጠር ባህሪ መፍጠር ጥሩ ነው ይላሉ። ይህ ሲሆን ግን  በሰራተኛው ላይ ጫና እና ጭንቀት ይፈጥራል ወይ የሚለውም ሊጠና እንደሚገባ ያሳስባሉ።
 
ዶክተር ፀጋዬ ኢትዮጵያ ውስጥ  ውጤት ተኮር ሆኖ መስራት እንዲቻል ምን መደረግ ያሻል ይላሉ? ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ባይሰሩም በተለያዩ ፕሮጀክቶች የታዘቡት ነገር አለ። « ለምሳሌ በአዲስ አበባ የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጥረውም ሰው በተባለበት ጊዜ ገብቶ በተባለበት ጊዜ የሚወጣበት ሁኔታ ነው።  ፍሌክሲብል የሆነ የስራ ሥርዓት ቢኖር ጥሩ ነው። እዛ የማየው ሌላው ነገር የአለቃ እና የበታች ሰራተኛ ላይ ያለው መተማመን ላይ መሻሻል ይፈልጋል። » ሲሉ ምክረ ሀሳብ ያቀርባሉ።
 

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ