1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ባንኮች የገንዘብ ቀውስ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 16 2015

የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ የሃገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማረጋጋት በተከታታይ የወለድ ጭማሪ በማድረግ ላይ ነው።ጭማሪው የተደረገው በአሜሪካ ለረጅም ዓመታት ያልታየ የዋጋ ግሽበት ባጋጠመበትና አንዳንድ የሃገሪቱ ባንኮችም በገጠማቸው የፋይናንስ ውድቀት መዘጋታቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4PF0h
Professor Minga Negash
ምስል privat

የአሜሪካ ባንኮች የገንዘብ ቀውስ

የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ፌደራል ቋት ሰሞኑን እንደገና የወለድ ጭማሪ አድርጓል። በተከታታይ እየተካሄደ ባለው የወለድ ማሻሻያ፣ባለፈው ረቡዕ የዜሮ ነጥብ 25 ጭማሪ በማድረግ አሁን ስምንት በመቶ ደርሷል። ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸውና በዴንቨር ሜትሮፖሊታን ስቴት እንዲሁም በደቡብ አፍሪቃ ዌትዋተርፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች የፋይናንስና የሂሳብ አያያዝ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ለወለድ መጨመር ምክንያት ናቸው ስለሚባሉ ጉዳዮች አብራርተውልናል።
"ዋናው ምክንያት እንግዲህ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመታገል ነው፤ለማሸነፍ ነው። የዋጋ ግሽበት በሚጨምርበት ጊዜ የኑሮ ውድነት ስሚጨምር አሁን ወደ ሰባት በመቶ ያህል ይህ ብዙ ጊዜ በአሜሪካ ታይቶ ያልታወቀ ነው። በአውሮፓም እንደዚሁ ነው።ለምሳሌ እንግሊዝ ላይ ብንመለከት በ10. 4 በመቶ ያህል ነው።በዓለም ዙሪያ ደግሞ ካየነው በአፍሪቃ ውስጥ በደቡብ አፍሪቃም ሰሞኑን ረብሻ ነበር። ኬኒያ በኢትዮጵያም እንደዚሁ የኑሮ ውድነት በዓለም ደረጃ እየጋሸበ በመሄዱ የተነሳ፣ ያንን ለመዋጋት ብለው ነው የወለድ መጠኑን የሚጨምሩት።"
ይሁንና ይህ በተከታታይ እየተካሄደ ያለው የወለድ ጭማሪ፣የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በማስከተል አሉታዊ ተጽእኖ ማድረሱ አልቀረም።
ዶክተር ሚንጋ እንደሚሉት፣ በኒውዮርኩ ሲግኔቸርና ሲልቨርጌት ባንኮች ላይ የፋይናንስ ውድቀት ማስከተሉ ግን፣ያልታሰበና ያልተገመተ ጉዳት ነበር።
"የወለድ መጠኑን ሲጨምሩ፣በአንድ በኩል የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ሲሞክሩ በሌላ በኩል ደግሞ ምጣኔ ሃብቱ ሊጎዳ ይችላል። ስራ አጥነት እንዳይበዛ ደግሞ ያንን ማመጣጠን አለባቸው።አሁን ደግሞ ያልታየውና ያልተገመተው የወለድ ጭማሪ ደግሞ ባንኮች ላይ አደጋ እየጣለ ሁለት ባንኮቾ ወድቀዋል። ከዛ በላይ ደግሞ ሶስተኛውንም ችግር ላይ ያለው።"
ከዚህም በላይ፣የባንኮች አክሲዮን ገበያ ወድቆ ታይቷል።ባንኮቹ፣ኦዲት ተደርገውና አስተማማኝነታቸው ተገልጾ 15 ቀን ሳይሞላ፣ ውድቀት ገጥሟቸው መዘጋታቸው በዘርፉ አነጋጋሪ ሁኔታ መፍጠሩንም የሂሳብ አያያዝና ፋይናንስ ምሁሩ ተናግረዋል።
ለጊዜው ከአሜሪካ ተነስቶ ወደ ስዊዝ የተዛመተው፣የባንኮች የፋይናንስ ችግር፣የሚያመጣው ጣጣ ዓለም አቀፍ ስጋት ያስከትል ይሆን ስንል የጠየቅናቸው ዶክተር ሚንጋ ሲመልሱ 
"እዚህ ያሉት ሁኔታዎች፣ በሀብታም ሃገሮች አንድ ነገር በሚፈጠረበት ጊዜ በሌሎች ሃገሮች ላይ በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሀገሮችን መነካካቱ አይቀርም።የዓለም ኤኮኖሚ የመጠን ጉዳይ ነው እንጂ፣የተያያዘ ነው። በአሁኑ ሰዓት ላይ ግን የምንመለከተው እንደ ወርልድ ኢኮኖሚ ፎረም ግምት ከሆነ በዋጋ ግሽበት የተነሣ ብዙ ቦታ ላይ ያመረጋጋት እየተፈጠረ ነው።ደቡብ አፍሪቃ አይተነዋል፣በኬኒያ አይተነዋል።እነዛ ነገሮች የሚሰፉበት ነገር ይመጣል። ምክንያቱም የኑሮ ውድነት እጅግ በጣም ተልቋል።የዋጋ ግሽበት ተልቋል።አውሮፓም በጦርነት የተነሣ ብዙ የህዝብ እንቅስቃሴ አለ።ጥሩ ሰዓት አይደለም ዓለም ላይ ያለውና እንደው ብድሩን ጠንቀቅ ማድረግ ያስፈልጋል በግለሰብ ደረጃ።" ብለዋል።

ታሪኩ ሀይሉ
ፀሀይ ጫኔ