1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ውይይት

ረቡዕ፣ ግንቦት 7 2016

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና፤ በተለይም ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን መሰረታዊ ችግር ምንነት፣ ሰላምን ለመፍጠር አስቻይ ሁኔታውን በተመለከተና በኢትዮጵያ በጅማሮ ላይ ባለው በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምን ያህል ችግሮቹ ሊፈቱ ይችላሉ የሚሉ ነጥቦች በውይይቱ ስለመነሳታቸውም ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4ftVm
USA/Äthiopien Mike Hammer US-Sonderbeauftragter am Horn von Afrika
ምስል Seyoum Getu/DW

የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ውይይት

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛው አምባሳደር ማይክ ሀመር ከኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት በኦሮሚያ ያለውን የፖለቲካ እና ጸጥታ ችግር ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ድርድር እዲደረግ ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡
አምባሳደር ሀመር ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና እና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባደረጉት ውይይት በተለይም በከሸፈው የታንዛንያ ድርድር እና በአገራዊ ምክክር ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል፡፡


የመወያያ ነጥቦች


በአጠቃላይ በአገሪቱ  የፖለቲካ አለመረጋጋት እና እልባቱን ማፈላለግ ላይ ያተኮረ ነው በተባለው በዚህ ውይይት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛው አምባሳደር ማይክ ሀመር ከሁለቱ ታዋቂ ፖለቲከኞች ግብኣት ይሆናሉ የተባሉ ሀሳቦችን ስለማሰባሰባቸው ተጠቁሟል፡፡ ውይይቱ ባጠቃላይ ሰላምና መረጋጋትን በሚመለከት ነው የሚሉት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና፤ በተለይም ኦሮሚያ ውስጥ ያለው መሰረታዊ ችግር ምንነት፣ ሰላምን ለመፍጠር አስቻይ ሁኔታውን በተመለከተ እና በኢትዮጵያ በጅማሮ ላይ ባለው በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምን ያህል ችግሮቹ ሊፈቱ ይችላሉ የሚሉ ነጥቦች በውይይቱ ስለመነሳታቸውም ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ውይይት መሰረታዊ የአገሪቱ ችግር ያሏቸው ነጥቦች ላይ ሀሳባቸውን ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡ቃለ መጠይቅ፤ የኢትዮጵያ ሰላም፣ ድርድርና ኦነግ
“መሰረታዊ የአገሪቱ ችግሮች ከየት ተነስተው የት ደረሱ የሚለው በተለይም  ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ለለውጥና ለዴሞክራሲ ደረገቻቸው ሙከራዎች አልተሳኩም፡፡ አሁንም ችግሮቹ ስላልተሳኩ አገሪቷ ኦሮሚያን ጨምሮ አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ መግባቷን፤ መሰረታዊ የኦሮሞ ህዝብ የዴሞክራሲ ጥያቄ በተለይም እራስን በራስ ማስተዳደር እና በራስ ንብረት መወሰንን ጨምሮ ሰላምና መረጋጋት የማግኘት ጥያቄዎች መሆናቸውን ተወያይተንበታል” ሲሉም በውይይቱ ስለተነሱ አበይት ነጥቦች ዘርዝረዋል፡፡
ፕሮፌሰር መረራ ለነዚህ ለተዘረዘሩ ችግሮችም እልባት ነው ብለው ያሰቡትን ለልዩ መልእክተኛው መግለጻቸውን ሲያስረዱ፤ “ባጠቃላይ በኢትዮጵያ በኦሮሚያም ውስጥ ያሉት ችግሮች የተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ያሉት ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች እንደመሆኑ ገዢው ፓርቲ ከአንድ ፓርቲ አውራነት ይልቅ ወደ ሀቀኛ ሁሉን ፓርቲ አቃፊ ውይይት እንዲገባ ግፊት እንዲደረግ” መጠየቃቸውን አልሸሸጉም፡፡ 

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ  ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ምስል Seyoum Getu/DW


የታንዛንያው ድርድር እና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን 

 

የአሜሪካ ልዩ መልእተኛው ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሚያ በትጥቅ መንግስትን የሚወጋው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ባለው የታጠቀ ቡድን መካከል በሁለት ዙር በታንዛንያ ተሞክሮ በከሸፈው ድርድር እና የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በተመለከተም ለፖለቲከኞቹ ጥያቄ ማንሳታቸው የተነገረ ሲሆን ፕሮፈሰር መረራ በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን ማንጸባረቃቸውንም ገልጸዋል፡፡ “ከታንዛንያው የከሸፈ ድርድር ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄ በራሴ በኩል የሰጠሁት ምላሽ ገዢው ፓርቲ ለሀቅና ድርድር ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጅት አለማድረጉ ይመስለኛል እንሁም በኦሮሚያ ላይ ገዢው ፓርቲ የስልጣን የበላይነቱን ማስጠበቅ እንደሚፈልግ ሀሳብ ሰጥቻለሁ” ብለዋል፡፡ ከአገራዊ ኮሚሽን ጋር ተያይዞም ተቋሙ የአገሪቱን ችግር አይፈታም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ኮሚሽኑ በአንድ ፓርቲ (ወገን) የተመሰረተ እንደመሆኑ የገለልተኝነት ስጋት እንደሚነሳበት” አስተያየታቸውን ማንሳታቸውን እንዲሁ አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም በሰፊው የኢትዮጵያ ግዛት ለሚስተዋለው የጸጥታ ችግር “ነጻና ገለልተኛ” ያሏቸው ውይይቶች እንዲደረጉ ግፊት ማድረግ እንደሚገባ መጠየቃቸውንም አስረድተዋል፡፡ 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳምስል Seyoum Getu/DW


ከኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በተጨማሪ የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም በዚሁ ውይይት ላይ ተሳትፈው ፓርቲያቸው በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ የተባለ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ለልዩ መልእክተኛው ማብራራታቸውን የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ በማህበራዊ ሚዲያቸው አጋርተዋል፡፡
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሀመር ከሚያዚያ 30-ግንቦት 11 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በጂቡቲ በሚኖራቸው የ12 ቀናት ቆይታ በኢትዮጵያ ሶስት ክልሎች ስላለው ግጭት እና የአፍሪካ ቀንድ ቃጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው ጋር እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ 
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ   
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ