1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ባለፉት 11 ወራት 3ሺህ446 ምስክሮች መቅረብ ባለመቻላቸው 4ሺህ 653 መዝገቦች ተዘግተዋል»

ረቡዕ፣ ሐምሌ 19 2015

በአማራ ክልል የሀሰተኛ ምስክሮች መበራከት የዳኞች ስራ መልቀቅና የቅንጅት ማነስ የህዝብን ፍትህ የማግኘት መብት በእጅጉ እእየጎዳው ነው ተባለ፡፡በበጀት ዓመቱ ከተቀጠሩ ዳኞች በላይ የለቀቁት ብልጫ እንዳላቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት ተናግሯል፡፡ ባለፉት 11 ወራት 3ሺህ446 ምስክሮች መቅረብ ባለመቻላቸው 4ሺህ 653 መዝገቦች ተዘግተዋል

https://p.dw.com/p/4UPi5
Äthiopien Oberstes Gerichtshof für die Region Amhara
ምስል Alemnew Mekonen/DW

ባለፉት 11 ወራት 3ሺህ446 ምስክሮች መቅረብ ባለመቻላቸው 4ሺህ 653 መዝገቦች ተዘግተዋል

በአማራ ክልል የሐሰተኛ ምስክርና የምስክሮች በፍርድ ቤት ቀርቦ አለመመስከር የክልሉን የፍትህ ስርዓት በእጅጉ እየተፈታተነው እንደሆነ ነዋሪዎችና የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፣ ባለፉት 11 ወራት 3ሺህ446 ምስክሮች መቅረብ ባለመቻላቸው 4ሺህ 653 መዝገቦች መዘጋታቸው ተገልጧል፣ የዳኞች መልቀቅና የፍትህ አካላት ተቀናጅቶ መስራት አለመቻል የፍትህ ስርዓቱን የጎዳው ሌላው ምክንያት ነውም ተብሏል፣ በበጀት ዓመቱ ከተቀጠሩ ዳኞች በላይ የለቀቁት ብልጫ እንዳላቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት አመልክቷል፡፡ በአማራ ክልል የሀሰተኛ ምስክሮች መበራከት፣ የዳኞች ስራ መልቀቅና የቅንጅት ማነስ የክልሉን ህዝብ የፍትህ ማግኘት መብት በእጅጉ እየጎዳው እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ዶይቼ ቬሌ ያነጋገራቸው የደቡብ አቸፈርና የይልማና ዴንሳ ወረዳ አርሶ አደሮች ሐሰተኛ ምስክሮች ለፍትህ ስርዓቱ ፈተና ሆነዋል ብለዋል፡፡

የሰሜን አቸፈር ወረዳ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ልዑል አቤ በበኩላቸው ሐሰተኛ ምስክሮችና ሀሰተኛ ሰነዶች ለፍትህ ስርዓቱ ማሽቆልቆል ብቸኛ ተጠቃሽ ምክንያቶች አይደሉም፣ ይልቁንም ሌሎች ችግሮችም እንዳሉ አብራርተዋል፡፡“ሐሰተኛ ምስክርና ሐሰተኛ ሰነድ ለፍትህ ስርዓቱ ከፍተኛ ችግሮች ናቸው፡፡ እነኚህ ብቻ ናቸው ወይ መሰናክሎች? ብለን ስናይ ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ፣ ፍርድ ቤቶች በቅንጅት አለመስራት፣ ጠበቆች ለፍትህ ስርዓቱ አጋዥ ናቸው ወይ? ብሎ መናገር አስቸጋሪ ሆኗል፣ አሁን አሁን ላይ፣ በተለይ ዓላማው “ንግድና ንግድ” ስለሆነ፣ ስለዚህ እነኚህና ሌሎች መሰናክሎች አሉ” ብለዋል፡፡የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ አብዬ ካሳሁን ሰሞኑን በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ባቀረት ሪፖርት የክልሉን የዳኝነት ስርዓት የተፈታተኑ ያሏቸውን ምክንቶች ዘርዝረዋል፡፡

“ዳኞችን በሰጡት ዳኝነት ምክንያት ማሰር፣ ማስፈራራት፣ በኃይል ዳኝነትን ለማስለወጥ የሚደረግ ሙከራና ልምምድ ለክልላችን የዳኝነት ስርዓት አደገኛ ስጋት መሆኑ፣ ሐሰተኛ ማስረጃና ሐሰተኛ ምስክር በፍትህ ስርዓቱ በጠቅላላው፣ በተለይ ደግሞ ትክክለኛ ዳኝነት ለመስጠት እንቅፋት መሆኑ፣ እንዲሁም የዳኞች መልቀቅ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የነበሩ ፈተናዎች ናቸው፡፡”

የአማራ ክልል ምክር ቤት  የሕግ፣ የፍትህና የአስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወርቅነህ እንደግ  የግድያ ወንጀል ባለፈው በጀት ዓመት መጨመሩን ጠቁመው፣ በክልሉ ከተቀጠሩ ዳኞች በላይ የለቀቁት እንደሚበልጡ ተናግረዋል፡፡አቶ ወርቅነህ፣ “በበጀት ዓመቱ ከ2ሺህ 275 በላይ የግድያ ወንጀል የተፈፀመ ሲሆን 3ሺህ 446 ምስክሮች (ፍርድ ቤት) ባለመቅረባቸው 4ሺህ 653 መዝገቦች እንዲዘጉ ሆኗል(በተጠቀሰው ጊዜ) 173 ዳኞች የተቀጠሩ ቢሆንም 175 የወረዳና የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ለቅቀዋል፤  በአንዳንድ ወረዳዎች አንድ ብቻ ዳኛ የሚገኝበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡” ብለዋል፡፡

የምስክሮች ወደ ፍርድ ቤት መጥቶ አለመመስከር በዋናነት የፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶች ተቀናጅተው መስራት ባለመቻላቸው እንደሆነ  የሰሜን አቸፈር ወረዳ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ አቶ ልዑል አቤ አስረድተዋል፡፡“ለምስክሮች አለመቅረብ ከፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ያአለመስራት ውጤት ነው፣ መዝገብ ዝም ብሎ አይዘጋም፣ ምክንቱም ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ፣ ዳኞች ተግባብተው በቅንጅት ካልሰሩ መጨረሻው የሚሆነው መዝገቡን መዝጋት ነው፣ ይህ የሚያሳየው ለፍትህ ስርዓቱ  ተቀናጅተው እየሰሩ አይደለም” ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ዋና ክፍል  ኃላፊ ኮማንደር ግርማ ጫኔ በበኩላቸው፣ የቅንጅት ችግር አለ ለማለት ብዙም ባያስደፍርም መዝገቦች የሚዘጉባቸው ምክንያቶች ግን፣ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታዎች ከሳሽና ተከሳሽን ማቅረብ አለመቻል፣ እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ተጠርጣሪዎች በዋስ ከተለቀቁ በኋላ ስለሚጠፉ፣ በአነስተኛ የገንዘብ ዋስትና የሚለቀቁ ሰዎች መሰወርና ሌሎች ምክንቶች ለመዝገቦች መዘጋት ምክንቶች ሊሆኑ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ገበያው ይታየው እንደሚሉት ደግሞ ምስክሮች ዛቻ ስለሚደርስባቸውና ስለሚፈሩ፣ አገር ስለሚለቁ፣ በሞትና በህመም ምክንያቶች ፍርድ ቤት ላይቀርቡ እንደሚችሉ ተናግረዋል፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ አለመመስከር ግን በሕግ እንደሚያስቀጣም አመልክተዋል፡፡የሐሰት ምስክርን በተመለከተም ባለሙያው ችግሮች እየታዩ አንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አሁን አሁን አንዳንድ ምስክሮች በተለያዩ መንገዶች በመደለል በሐሰት እንደሚመሰክሩ አመልክተዋል፡፡

“ምስክር በአብዛኛው፣ አሁን ደግሞ በቅርብ እየተለመደ የመጣው ሰዎችን በገንዘብ እየደለሉም ቢሆን የማያውቁትን ነገር እንደሚያውቁት፣ ያወቁትን ነገር ደግሞ ፣ እንዳይናገሩ እንዳላወቁት ቆጥረው የምስክርነት ቃላቸውን በፍርድ ቤት እንዲሰጡ እየተደረጉ በገንዘብ ተገዝተው ሐሰትን የመናገር ሁኔታዎች ይስተዋላል፡፡”አንዳንድ ጠበቆች ከሙያዊ ስነ ምግባር ውጪ ሙያውን ለገቢ ማግኛ ብቻ ይጠቀሙበታል ስለተባለው ስሞታም ጠበቃ ገበያው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“ብዙውን ጊዜ ዳኛ ሊሆኑ ይችላሉ፣ አቃቤ ሔግ ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ሌሎች ተቋማት ላይ የሚሰሩ ግለሰቦች፣ በሚሰሩበት ተቋም አመኔታ ሲታጣባቸው ወይም በስነ ምግባር ችግር ሊከሰሱ ሲሉ፣ ሊቀጡ ሲሉ ጠበቃን እንደማምለጫ የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ፣ በዚህም ምክንያት በጥብቅናው ሥራ ውስጥ ወደ ፍትህ ተቋሙ ሲቀላቀሉ አሁንም በስነምግባራቸው የፀዳ አካሄድ ስለማይኖራቸው ከግለሰቦችና ከተቋማት ጋር በመመሳጠር ኢ-ፍትሀዊ የሆነ ክርክር የማካሄድና ኢ-ፍትሀዊ የሆነ ውሳኔ እንዲሰጥ የማደረግ ውሳኔዎችን ያካሂዳሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ