1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ተሳታፊዎችን መያዙን አስታወቀ

እሑድ፣ ጥቅምት 30 2012

በአማራ ክልል በሚገኘው በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ተማሪዎች በሞቱበት የትላንት ምሽት ግጭት የተሳተፉ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው በክልሉ በሚገኙ አስር ዩኒቨርስቲዎች ተመሳሳይ ግጭት ለማስነሳት አቅደው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ገልጿል።

https://p.dw.com/p/3Snml
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

የአማራ ክልል ሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ዛሬ መደበኛ ጉባኤውን እየካሄደ ለሚገኘው የአማራ ክልል ምክር ቤት እንደተናገሩት በክልሉ የግለሰቦች ግጭቶች ወደ ብሔር ግጭት እየተሸጋገረ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ትላንት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ያጋጠመውም ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

“ትላንትና ማታ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ላይ ተማሪዎች ኳስ ሲመለከቱ አመሹ። በኳስ ጨዋታ መደገፍ፤ በሀገራችን ክለቦች አይደለም በውጭ ሀገር ክለቦች አደጋገፍ ላይ፤ በተማሪዎች መካከል ግጭት ተነሳ። ይህን ግጭት የሚፈልጉት ኃይሎች ስላሉ ወዲያውኑ የብሔር ግጭት አደረጉት። በግጭቱ ተማሪዎች፤ ወጣቶች ተጎዱ” ብለዋል። 

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አስናቀ ለዶይቼ ቬለ (DW) በስልክ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ትናንት ምሽት አምስት ሰዓት በተነሳ ግጭት ሁለት የሶሻል ሳይንስ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ህይወታቸው ሲያልፍ አስሩ ደግሞ ቆስለዋል። የሟች ተማሪዎችን ማንነት ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

“ተማሪዎቹ ህንጻ ቁጥር ሰባት ላይ እና ግጭቱ እንደተነሳ የሚናገሩበት ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል የአውሮፓ ሊጎች የእግር ኳስ ጨዋታ ምሽት ነበረ። እዚያ ኳስ ሲመለከቱ፣ ከDSTV አምሽተው ሲወጡ፤ ‘ችግሩ እዚያ ነው የተነሳው፤ ከዚያ ጠንከር ብሎ ነው ወደ ዶርም የገባው’ የሚሉም አሉ” ሲሉ የግጭቱ መንስኤ ነው የሚባለውን አብራርተዋል። 

በግጭቱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው አስር ተማሪዎች ከተለያየ አካባቢ የመጡ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ተፈራ አሁን በወልዲያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ለተማሪዎች ግጭት መነሻ የሚሆን ምክንያት ቀደም ሲል እንዳልታዬ የሚናገሩት የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተማሪዎቹ በአንበጣ መከላከል ሥራ ተጠምደው እንደዋሉ አመልክተዋል። 

ዛሬ ረፋዱን ለአማራ ምክር ቤት አባላት በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ የሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ግን በክልሉ በሚገኙ አስር ዩኒቨርስቲዎች ላይ ሰላም እንዲደፈርስ አልመው እና አቅደው የሚሰሩ ኃይሎች እንዳሉ ጠቁመዋል። ቢሮአቸው እነዚህን ኃይሎች ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አመልክተዋል። በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ትላንት የተፈጠረውን ግጭት በአሁኑ ወቅት ማረጋጋታቸውን ለምክር ቤት አባላት የተናገሩት አቶ አገኘሁ “በዚህ ወንጀል ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል” ብለዋል።

ዓለምነው መኮንን/ ተስፋለም ወልደየስ