1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 13 2015

የምክር ቤት አባል ዶ/ር በቃሉ ታረቀኝ እንደተናገሩት ከትግራይ ጋር የአመራር ለአመራር ግንኙነቱ ባይከፋም ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እስካልወረደ ደድረስ ውጤት የለውም።ህዝብ በወኪሎቹ አማካይነት የምክር ቤት ውይይቶችን የመከታተል መብት ቢኖረውም የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ብቻ እንዲዘግቡ መደረጉና የቀጥታ ስርጭት መከልከሉም ስህተት ነው ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4UCH9
Äthiopien | Yilkal Kefale
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ

የሰሜኑን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት በፈጠረው መልካም አጋጣሚ ከትግራይ ክልል መሪዎች ጋር የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ፣ ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር የሚኖረው መልካም ግንኙነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ትናንት በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ሲጀመር ገልጠዋል። ከአማራ ልዩ ኃይል አዲስ አደረጀጃት ጋር የተፈጠረው አለመረጋጋት በክልሉ ሰላም ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፣ ወንጀል በክልሉ መጨመሩንም ተናግረዋል።
ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ ሚዲያ ዘጋቢዎች ዝግ የሆነው የአማራ ክልል 6ኛ መደበኛ ጉበኤ ትናንት በምክር ቤቱ አዳራሽ ሲጀመር የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ በነበረው ጦርነት ክልሉ በርካታ ውድመቶች የደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል፣ የወደሙ መሰረተ ልማት አውታሮችንና ማኅበራዊ ምስጫ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና በብዙዎች ላይ የደረሰውን የስነልቦና ስብራት ለመመለስ ጥረት ቢደረግም አሁንም ችግሩ እንዳልተወገደ አመልክተዋል፡፡ክልሉ ርዕስ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የክልሉን የ11 ወራት ሥራ አፈፃጠም ያቀረቡ ሲሆን በተለይም የሰሜኑ ጦርነት ከቆመ በኋላ ከትግራይ ክልል ጋር የአመራር ለአመራር ግንኙነቶች መፈጠራቸውን አንስተው ቀጣይም ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከአማራ ልዩ ኃይል አዲስ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ የክልሉ ሰላም ደፍርሶ መቆየቱን ያስታወሱት ዶ/ር ይልቃል፣ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ጥረቶች እንደሚቀጥሉ ገልጠዋል፡፡ 
የወንጀል ድርጊት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር በ23 ከመቶ መጨመሩን አመልክተው 4 ሺህ የሚጠጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል፣ህገወጥ ድርጊቶች ያሏቸውንም ዘርዝረዋል፡፡ “ ባለፉት 11 ወራት የተፈፀመው ወንወጀል ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ23 ከመቶ ብልጫ አለው፣ 1ሺህ067 የተለያዩ መሳሪየዎች፣ 2ሺህ 808 ሽጉጦች፣ 483 ቦምቦች፣336ሺህ የተለያዩ ጥይቶች ፣12 ሺህ የቁም እንስሳት፣ 116 ንዋዬ ቅድሳት 13.4 ሚሊዮን ብር፣ 309 ሐሰተኛ የብር ኖት፣  የተያዙ ሲሆን 3ሺህ 837  ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡” 
መሬትን በህገወጥ መያዝን ጨምሮ ሌሎች የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ በርካታ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው  ምርምራ እንዲጣራባቸው መደረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡“ከቀረቡት 1ሺህ 867 የሙስና ጥቆማዎች መካከል 1ሺህ 542  ምርመራ የሚያስጀምር ሆኖ በመገኘቱ ምርመራ እንዲጣራ ተወስኖባቸዋል፡፡ ”
በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተልማትና በሌሎች ዘርፎችም የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችንና ጉድለቶችን በሪፖርታቸው ያቀረቡት ዶ/ር ይልቃል፣ 9.2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ዳበሪያ ግዥ ለመፈፀም ቢታቀድም እስካሁን የተገዛው ከ33 ከመቶ እንደማይበልጥ፣ 2.99 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር በቃሉ ታረቀኝ የተባሉ የምክር ቤት አባል ለዶቼ ቬሌ እንደተናገሩት ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር የአመራር ለአመራር ግንኙነቱ ባይከፋም ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እስካልወረደ ደድረስ ውጤት የለውም፡፡
“አመራር ነው እንግዴህ ህዝቦችን ወደአልተፈለገ ያስገባው፣ አሁንም ህዝብን አምጥተህ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እስካላጠናከርህ ድረስ አመራር ብቻ  ዘላቂም አይሆንም መፍትሔም ያመጣም፡፡”ህዝብ በወከላቸው ወኪሎቹ አማካይነት የምክር ቤት ውይይቶችን የመከታተል መብት ቢኖረውም የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ብቻ እንዲዘግቡ መደረጉና የቀጥታ ስርጭት መከልከሉም ስህተት ነው ብለዋል ዶ/ር በቃሉ፡፡ትናንት የተጀመረው የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገ የሚጠናቀቅ ሲሆን ሹመቶችንም ፀድቃል ተብሎ ጠበቃል፡፡

ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር