1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል መንግሥትና የታጠቁ ኃይሎች ለእውነተኛ ውይይትና ንግግር እንዲመጡ ተጠየቁ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 25 2016

በአማራ ክልል ከአሁኑ የፀጥታ ችግር አላቆ ቀድሞ ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ መንግስትና የታጠቁ ኃይሎች እውነተኛ ውይይትና ንግግር እንዲቀመጡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላትና ነዋሪዎች ጠየቁ። የምክር ቤቱ ጉባዔ የክልሉን የ2017 ዓ ም በጀትና የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዚደንት ሹመት በማፅደቅ ዛሬ ተጠናቅቋል፡፡

https://p.dw.com/p/4j18r
Äthiopien House of Speaker for Amhara Regional State Council - Bahir Dar 01.08.2024
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

«ድርድርና ንግግር አማራጭ ሳይሆን ብቸኛ ምርጫ ሊሆን ይገባል»የአማራ ክልል ፖለቲከኞች

የነዋሪዎች ጥያቄ

የአማራ ክልል አንዳንድ ነዋሪዎች በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲፈታ የምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፣ ከመተማ፣ ከቢቸናና ከደብረማርቆስ ከተሞች ያነጋገርናቸው አንዳንድ ነዋሪዎች፣ የምክር ቤት አባላት የክልሉን ነዋሪዎች በእጅጉ እየጎዳ ያለውን የሰላም እጦት በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል የምክር ቤት አባላት፣ መንግስት፣ ከመንግስት ጋር እየተዋጉ ያሉ ኃይሎችና መላው ማህበረሰብ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ወደ ሰላማዊ ድርድርና ውይይት እንዲመጡ ግፊት ያድርጉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት ሀሳብ

የአማራ ክልል 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተሳተፉ ያሉ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ጦርነቱ የክልሉን ባህላዊ እሴቶች ጭምር እያወደመ በመሆኑ መንግስት ያልተሞከሩ የሰላም አማራጮችን ጭምር በመጠቀም የክልሉ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ ጥረቱን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ከምክር ቤት አባላት መካከል አንዷ እንዲህ ብለዋል፣ “የአማራ ክልል ታላላቅ ሀብቶች፣ እሴቶች ባህሎችና ማንነቶች በአሁኑ ሰዓት እየተበጣጠሱ፣ እየተመናመኑ ናቸው፣ “ያልተሞከሩ የሰላም አማራጮች ምን አሉ? ምክር ቤቱ ያልተሞከሩ አማራጮችን መፈለግ አለበት፣ በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም፣ ይህን ካልን ያልሞከርናቸው መፍትሔዎች ምንድን ናቸው? ብሎ በፌደራል መንግስቱ፣ በአማራ ክልል በየቤታችንና በየአካባቢያችን ችግሩን ፈልገን ማከም አለብን፡፡” ብለዋል፡፡
የክልሉ ልማት በአለው ጦርነት እየተጎዳ በመሆኑ ሁሉም ወገኖች የሰላሙንና የድርድሩን መንገድ እንዲቀበሉ ደግሞ ሌላው የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ልማት ቆሞ ወደ ጦርነት መግባት ብዙ ጉዳት እንደሚያስከትልና እያስከተለም መሆኑን ተናግረዋል፣ መንግስትም ሆነ ጫካ የገቡ ወገኖች ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ እንዲሰጡ ነው እኚህ የምክር ቤት አባል የተማፀኑት፡፡

የአማራ ክልል ጉባኤ
የአማራ ክልል ጉባኤ ምስል Alemenw Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ምላሽ

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ አሁን የክልሉ ህዝብ ከደረሰበት የፀጥታ ችግር ማውጣት ለነገ የሚባል ጉዳይ ባለመሆኑ ህዝብና መንግስት ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ ብለዋል፡፡ የተጀመረው ሰላምን የማስፈን ስራ ተጠናክሮ ይቀትላል ነው ያሉት፣ በዚህ ረእሰ መስተዳድር አረጋ “ፈታኝ” ባሉት ጊዜ አመራሩና መላው ህብረተሰብ ከዚህ ቀውስ መውጣት ለነገ የሚባል የቤት ስራ እንዳልሆነ ነው ያስረዱት፣ “የገባንበት ችግር ዘርፈ ብዙ ነው” ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ችግሩን በአግባቡ ለይቶና ተንትኖ መፍትሄ ማምጣት እንደሚስፈልግ ተናግረዋል፣ የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ ሰላም ለማምጣት ማነኛውንም ጥረት እንደሚያደርግ ነው መለከቱት፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ጥሪ

 

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተሰፋዬ የምክር ቤቱን ጉባኤ በከፈቱበት ወቅት የታጠቁ ኃይሎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡
ወ/ሮ ፋንቱ፣ “ድርድርና ንግግር አማራጭ ሳይሆን ብቸኛ ምርጫ” ሊሆን እንደሚገባ መግለፃቸውም ይታወሳል፡፡
 
የምክር ቤቱ ጉባዔ  ሹመት በማፅደቅ ተጠናቅቋል

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬምስል Alemenw Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ምክር ቤት በሌሎች ጉዳዮች ላም ሰፊ ውይት አድርጓል፣ ምክር ቤቱ  በትናንትና ውሎው የ2017 ዓ ም የአማራ ክልል በጀት 150 ቢሊዮን፣ 666 ሚሊዮን ብር እንዲሆንም አፅድቋል፡፡ ሐምሌ 22/2016 ዓ ም የተጀመረውና ዛሬ ረፋድ የተጠናቀቀው የአማራ ክልል 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ጉባኤ የአማራ ክልልን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዚደንትና ምክትል ፕረዚደነት ሹመትን አፅድቋል፣ በዚህም መሰረት አቶ ዓለምአንተ አግደው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዚደንት፣ ሙሉዓለም ቢያዝን ደግሞ ምክትል ፕረዚደንት ሆነው ተሹመዋል፣አቶ መልካሙ ፀጋዬ ደግሞ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሆነው ቃለ ማሀላ ፈፅመዋል፡፡፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ