1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ፍፃሜ፣ የሪፐብሊኪቱ እጣ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2016

ግራማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚ አብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ።የአገዛዝ ሥልት፣ መርሕ፣ዓላማ-ግባቸዉ፣ ስኬት-ዉድቀታቸዉ እስከዛሬም ድረስ ብዙ ያከራክራል።ኢትዮጵያን ለዘመነ ዘመናት በጠንካራ ክርን-መዳፋቸዉ ጨምድደዉ መግዛታቸዉ ግን ሐቅ ነዉ።ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ሕገ መንግስት፣ ፓርላማ ሁሉም የእሳቸዉና የእሳቸዉ ብቻ ነበሩ።

https://p.dw.com/p/4kR1k
አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1963 ዩናይትድ ስቴትስን ሲጎበኙ
አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1963 ዩናይትድ ስቴትስን ሲጎበኙ።የተቀመጡት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲምስል Prince Ermias Sahle-Selassie

የንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ፍፃሜ፣ የሪፐብሊኪቱ እጣ

ጎሕ መቅደዱ ነዉ።ከማለዳዉ 10 ሰዓት።-«--ወደ መሿለኪያ እየነዳሁ ስጓዝ» ይላሉ የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባልና የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዝደንት ሌትናንት ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ ባሉት መፀሐፋቸዉ።«ኃይለኛ ነፋስ ይነፍሳል።» ቀጠሉ ኮሎኔሉ። ባደጉበት ባሕል ኃይለኛ ነፋስ አንድም የትልቅ ሰዉ ሞት፣ ሁለትም መንግሥት ይገለበጣል የሚል መጥፎ ሚልኪ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።የዚያን ቀን የሆነዉ ግን ሁለተኛዉ ነበር። መስከረም 2፣ 1967።

«የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር ደርግ ለግርማዊነትዎ ደሕንነትና ጤንነት በሠፊዉ እሚያስብ እንደመሆኑ መጠን፣ለጤንነትዎም ሆነ ለደሕንነትዎ የተዘጋጀ ሥፍራ ሥላለ ወደዚያ እንዲሄዱልን በትሕትና እንለምናለን።»

ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ (ድል አድራጊዉ የይሁዳ አበሳ) ድል ሆነ።የዘመነ ዘመናት ሥርዓቱ ተገረሰሰ።በዚሕ ሳምንት ሐሙስ 50 ዓመቱ።የዚያን ቀኑ እርምጃ መነሻ፣ የቀጠለዉ ሒደት ማጣቃሽ፣ የዛሬዉ የኢትዮጵያ  እዉነት መድረሻችን ነዉ።

የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1971 ኢራንን ሲጎበኙ
አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1971 ቴሕራን ኢራንን በጎበኙበት ወቅት ከኢራን ንጉስ ሻሕ መሐመድ ሬዛ ጋር ምስል picture-alliance/Bildarchiv

በሥልጣን አድገዉ፣ በሥልጣን ኖረዉ፣ ለሥልጣን አርጅተዉ----ወረዱ

ከ12 ዓመታቸዉ ጀምሮ ደጅ አዝማች፣ራስ፣ አልጋ ወራሽ፣ ንጉስ፣ ንጉሰ ነገሥት ነበሩ።የጠቅላይ ግዛቶች አገረ ገዢ፣የንግሥተ ነገሥታት ዘዉዲቱ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ፣ አልጋ ወራሽ፣ ንጉስ፣ ከ1923 ጀምሮ ደግሞ ንጉሠ ነገሥት ሆነዉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በየደረጃዉ ለ71 ዓመታት አሹረዉታል።

ግራማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚ አብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ።የአገዛዝ ሥልት፣ መርሕ፣ዓላማ-ግባቸዉ፣ ስኬት-ዉድቀታቸዉ እስከዛሬም ድረስ ብዙ ያከራክራል።ኢትዮጵያን ለዘመነ ዘመናት በጠንካራ ክርን-መዳፋቸዉ ጨምድደዉ መግዛታቸዉ ግን ሐቅ ነዉ።ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ፍርድ ቤት፣ ሕገ መንግስት፣ ፓርላማ ሁሉም የእሳቸዉና የእሳቸዉ ብቻ ነበሩ።

ዩኒቨርስቲዉ፣ ሆስፒታሉ፣መንገዱ፣የቲአትር አዳራሹ፣ የቤተ መንሥግት አጥሩ፣ ወንበር ጠረጴዛዉ ሳይቀር ቀኃስ ነዉ።«ጠቅልል» ነዉ የፈረስ ስማቸዉ።ሁሉን ጠቅልለዉ ለተንዛዛ ዘመናት መግዛታቸዉ፣ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ፣ የቅርብ ዘመድ፣ ታዛዥ፣ ታማኝ ባለሥልጣናቸዉን  ሳይቀር አንገሽግሾ ነበር። ።ማን ይናገረ የነበረ።ልዑል ዶክተር አስፋ ወሰን አሥራተ ካሳ።

«በልጅ እንዳልካቸዉ መንግሥት እንደተቋቋመ፣ የነበረዉ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበረዉ ደስታ፣ የነበረዉ ተስፋ፣ አየሕ የለዉጥ አጥቢያ ማለት ነበር።ሁሉ ነገር በመለወጥ ላይ ነበር።አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲቋቋም ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር።የመሬት ይዞታን የሚያጠና ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር።ኢንኳየሪ (መርማሪ) ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር።-----(ጥያቄ፣ እርስዎም ደስ አለዎት? ምክንያቱም የገዢዉ መደብ አካል ነዎች፣ ለዙፋኑ በጣም ቅርብ የሆነ ቤተሰብ አባል ነዎች)---እንደዚያን ቀን ከዚያ ወዲሕ ተደስቼ አላዉቅም።»  

የያኔዉ የደርግ ሊቀመንበርና የኋላዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትግላችን ባሉት መፅሐፍ በተለይ ደርግ ከተመሠረተበት ከሰኔ 21፣ 1966 በኋላ የነበረዉን የፖለቲካ ትኩሳት «ደርግ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ደርግ የሆኑበት» ይሉታል።

የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት እንዲወገድ ሲታገሉ ከነበሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አንዱ፣ የኋላዉ የኢሕአፓ ተዋጊ፣ የብአዴን መሥራች ያሬድ ጥበቡ ደግሞ «የሚጠበቅ ግን አስገራሚ» ብለዉታል።ዋዉ ብለዉ

ከፊት ከግራ ወደ ቀኝ ሁለተኛዉ አፄ ኃይለ ሥላሴ እና ከጀርባቸዉ የዮunኢeትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በ1963 (እግአ)
ከፊት ከግራ ወደ ቀኝ ሁለተኛዉ አፄ ኃይለ ሥላሴ እና ከጀርባቸዉ የዮunኢeትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በ1963 (እግአ)ምስል STAFF/AFP/Getty Images

«ኃይለ ሥላሴን ያክል ታላቅ ንጉስ ሲወርድ መሬት እሚሰነጥቅ ዓይነት ነዉ።ያም ሆኖ ግን ሳይኮሎጂካሊ እየተዘጋጀን እንድንመጣ አድርጓል (አስቀድመዉ) የተወሰዱት ርምጃዎች------ ሥለዚሕ በጣም ያልተጠበቀ ፍፃሜ አይደለም።ያልተጠበቀም ሆኖም ግን ዋዉ የሚያሰኝ ነበር»

ረቂቋ ኢትዮጵያ፣ ረቂቁ ንጉሷ

አየርላንዳዊዉ ጋዜጠኛ ብሌር ቶምሰን እንደጠቀሰዉ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ከመወገዳቸዉ አመት ከመንፈቅ ቀደም ብለዉ «ኢትዮጵያ በፈጠሪ እጅ ያለች ረቂቅ ሐገር ናት» ብለዉ ነበር።ንጉሰ ነገሥቱ ራሳቸዉ ከኢትዮጵያም በላይ በርግጥ ረቂቅ ነበሩ።ባልተዋጉበት «ድል አድራጊዉ ንጉሳችን» ተዘምሮላቸዋል።በሌሉበት በስማቸዉ ይማልበታል።ተሰግዶላቸዋል።የሳቸዉ አሽከር በመሆን ወይም በማለት ብዙዎች ኮርተዉበታል።«የጠቅል አሽከር።»

ከበሽታ፣ሐይቅ ዉስጥ ከመስጠም፣ከጦርነት፣ ከመኪና አደጋ፣ከተደጋጋሚ ሴራ፣ ከመፈንቅለ መንግሥት አምልጠዋል።«ተንፏቃቂ» ወይም «የሚድኸ» መፈንቀለ መንግስት ከሚባለዉ በትር ግን በርግጥ ማምለጥ አልቻሉም።ግን የዚያን ቀንም «በቃዎት» ሲባሉ፣ በዚሁ «ማቆም» ነዉ አሉ-ሰዉዬዉ።83 ዓመታቸዉ ነበር።

«በየጊዜዉ የሚለዋወጠዉ ነገር ደግሞ ለአገር የሚጠቅም ነገር እስካለበት፣ የአገርን ጥቅም በሌላ ለመለወጥ አይቻልምና ያነበባችሁትን ሠምተናል በዚሁ ማቆም ነዉ።»

ድል አድራጊዉ ግን ያረጀ-ያፈጀዉ የይሁዳ አንበሳ ያለምንም ደም መፋሰስ ድል ሆነ።«ያለምንም ደም ተዘመረ።»፣ «ኢትዮጵያ ትቅደም» መዓለት ወሌት ተፈከረ።ተሰበከ።ለዉጡ ብዙ ደጋፊ አፈራ።ብዙ አስቦረቀ።ጋዜጠኛ ብሌር ቶምሰን ግን የንጉሠ ነገስቱን መወገድ «ኢትዮጵያ ራስዋን (ጭንቅላቷን) የቆረጠች ሐገር» ብሎ ገለጠዉ፣ ፃፈበም።ልዑል ዶክተር አስፋ ወሰን አስራተ ካሳም የእንዳልካቸዉ መኮንን ካቢኔ ሲመሰረት ጠቃሚ፣ አስደሳች፣ ተስፋ ሰጪም የነበረዉ ለዉጥ (አንዳዶች የጥገና ለዉጥ ይሉታል) ንጉሠ ነገስቱ ከሥልጣን ሲወገዱ ተቀጨ ዓይነት ይላሉ።

 «ንጉሠ ነገሥታዊዉ መንግሥት ሲወድቅና አብሶ ሪፎርሚስት የተባለዉ፣ ሕዝብ ሁሉ የተቀበለዉ  የልጅ እንዳልካቸዉ ሥርዓት የፈረሰ ጊዜ ነገሩ ሁሉ እንዳለቀለት ገባኝ።ከዚያ ወዲሕ አመራሩ ቀጥታ ወደ ሶሻል ፋሺዝም መለወጡ ለማንኛችንም ግልጥ ነዉ።»

ጋዜጠኛና ዲፕሎማት ተፈራ ሻዉል እንደሚሉት ግን የንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መዉረድ አሳዛኝ ግን ተስፋ ሰጪም ነበር።ቅይጥ ስሜት።

«ያመንግሥት ሲወርድ አዲሱ ደግሞ እኛ ተማሪ ቤት ሆነንr እምንዋጋለት ሶሻል ዴሞክራቲክ  ዝንባሌ ያለዉ ማሕበራዊ ፍትሕ የሚያመጣ ሥርዓት ይመጣል ብለን በተስፋና በሐዘን መሐል ነበርን።»                      

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የመሩት ደርግና ኋላ ኢሠፓ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት መርቷል።
ከግራ ወደቀኝ ከፊት ሁለተኛዉኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የደርግ ሊቀመንበርና የኢሕዲሪ ፕሬዝደንትምስል Privat

ይሁንና ብዙ ኢትዮጵያዉያን በተለይ የግራ ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ ወገኖች ለዉጡን  የኢትዮጵያ ዳግም ልደት፣ የሕዝቦችዋ እኩልነት፣የዕድገት ብልፅግናዋ መሠረት፣ የሚል ተስፋ ነበራቸዉ።ደርግ በቀድሞ ባለሥልጣናት፣ በራሱ አባላትና መሪ ላይም ምሕረት የለሽ ሰይፉን ሕዳር ላይ ሲያሳርፍ ግን የነ አምባሳደር ተፈራ ተስፋ እየጫጨ ሐዘኑ ሳይበረታ አልቀረም።

ዘዉዱን እንደ አንድነት ምልክት አስቀምጦ፣ አስተዳደራዊ ለዉጥ ይደረግ ባዮችም፣ ሕብረተሰባዊነት ወይም የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም አቀንቃኞችም፣የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ተከታዮችም፣ ጥቂት ቢሆኑም የጦር ኃይሉ አባላትም ባንድ አብረዉበት የነበረዉ ለዉጥም ይደነቃቀፍ ገባ።በተለይ መሬት ላራሹ እያለ ሲጮኽ የነበረዉ አብዛኛዉ ተማሪ  መከፋፈል፣ እርስበርስ መሻኮት፣ኋላም መገዳደል ያዘ።አቶ ያሬድ ጥበቡ።

 በጦርነት ኖረዉ በጦርነት የተፈፀሙት ደርግና ኢሕአዴግ 

«ደርግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ከተማሪዉ በአብዛኛዉ ተቃዉሞ ነዉ የነበረዉ።በሕቡዕ መደራጀት የጀመሩ የግራ ድርጅቶች የነበሩበት ጊዜ ነዉ።ሁላችንም ባንድ ድምፅ በተመሳሳይ መንገድ፣ ወታደራዊ አገዛዝ ለኢትዮጵያ ጥፋት ያመጣል።በጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መተካት አለበት---ሞር ኦርለስ የተስማማ አቋም ነበረን።»

ደርግና ከደርግ ጋር ያበሩ የግራ ፖለቲከኞችመሬትን፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪና የማምረቻ ተቋማትን፣የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶችን መንግሥት እንዲቆጣጠራቸዉ (እነሱ የሕዝብ አደረግን ነዉ የሚሉት) ወረሱ።ትልቅ ነገር ይሉታል።አምባሳደር ተፈራ።ግን ሽኩቻ፣ ቁርቁስ፣ መደፋፈጡን አባሳዉ እንጂ አላስቆመዉም።

ወታደራዊዉ መንግሥትም በምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ በኩል ከሶማሊያ ጋር፣ ሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ከኤርትራ፣ ከትግራይ፣ ከኢዲሕ፣ ከኢሕአፓ፣ በምዕራብና ደቡብ  ከኦሮሞ፣ ከሲአን፣ በሌሎች አካባቢዎች በብሔር ከተደራጁ ሌሎች አማፂያን ጋር ይዋጋ ያዘ።ቀይና ነጭ ሽብር የሚባለዉ የከተማ ዉጊያም ቀጠለ።እንደገና አቶ ያሬድ።

የኢትዮጵያ የግራ ኃይላት በሙሉ ሶሻሊስታዊ ሥርዓትን ቢደግፉም እርስበርስ ከመጠፋፋት አልታቀቡም
የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ከተወገደ በኋላ ኢትዮጵያ የተከተለችዉ የሶሻሊዝም ሥርዓት ዋና ምልክት ከነበሩት አንዱምስል Getty Images/AFP/A. Joe

የረጅም ጊዜዉ ጦርነት፣የፖለቲካ ሴራ፣ የምዕራባዉያን ጫን፣ ከሶቭየት ሕብረት መፈረካከስ ጋር ተዳምሮ የደርግ ስርዓትን አስወገደ።በ1983 የአፄ ምኒሊክን ቤተ መንግሥት የተቆጣጠሩት የሕወሓት/ኢሕአዲግ መሪዎች የኤርትራን ነፃነት አፅድቀዉ ትልቂቱን፣ ታሪካዊቱን፣ የነፃነት አብነቲቱን ሐገር ወደብ አልባ ቢያስቀሩም ከግጭት፣ጦርነትና እልቂት አዙሪት ሊያድኗት አልቻሉም።ወይም አልፈለጉም።ልዑል ዶክተር አስፋ ወሰን አስራተ ካሳ «ከመንግሥቱ ኃይለማርያም የከፋ ሰይጣን» ይሏቸዋል የሕወሓት/ኢሕአዲግ መሪዎችን።

በጦርነት ሥልጣን የያዙት የሕወሓት ኢሐዴግ ኃይላት በሕዝብ አመፅ ከሥልጣን ቢወገዱም ለ27 ዓመታት የተከሉት የዘር ፖለቲካ ሐገሪቱን ለዛሬዉ ዉድቀት፣ ሕዝቧን ለመጠላላት፣ ለመከፋፈል ዳርገዋቸዋል።ልዑል አስፋወሰን እንደሚሉት በሕወሓት/ኢሕአዲግ እግር ተተክቶ በ2010 ሥልጣን የያዘዉ ኃይልም ያቺን ጥንታዊ ሐገር ወደ ከፋ ገደል እየገፋት ነዉ።

 ጀርመኖች «መጨረሻ የሚሞተዉ ተስፋ ነዉ» ይላሉ። ተስፋ እናድርግ።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ