1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaዓርብ፣ ነሐሴ 17 2016

https://p.dw.com/p/4jrjt

የላኦስ የጸጥታ ኃይሎች ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ በሳይበር ማጭበርበሪያ መረብ ውስጥ ሲሰሩ ነበር ያላቸውን 800 ገደማ የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ስር አዉለው ከሀገር ማባረራቸውን አስታወቁ። የጸጥታ ኃይሉ በማይናማር እና ታይላንድ አዋሳን አካባቢዎች በቁጥጥር ስራ ካዋለቸው የሀገሬውን  ጨምሮ 771 የ15 ሃገራት ዜጎች ውስጥ 282ቱ ሴቶች ናቸው።

በቀጣናው ሃገራት የተሳካለት በተባለለት የላኦስ የጸጥታ ኃይሎች  የሳይበር አጭበርባሪዎችን የማደን ዘመቻ ቻይናን ጨምሮ ከሌሎች የዓለም ሃገራት ድጋፍ ማግኘቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የላኦስ ፣ማይናማር እና የቻይና ዜጎች በብዛት በሚገኙበት እና  በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋሉት ዉስጥ ከኢትዮጵያዉያን በተጨማሪ ከቡሩንዲ ፣ኮሎምቢያ ፣ ጆርጂያ ፣ህንድ ፣ ኢንዶኔዢያ ሞዛምቢክ ፣ዩጋንዳ ፣ቱኒዚያ እና ፊሊፒንስ የመጡ ዜጎች ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹ የሳይበር አጭበርባሪዎች ብርቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው በዘመዶቻቸው ርዳታ ወደየመጡበት ሃገራት መላኩን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።

የላኦስ የጸጥታ ኃይሎች ዘመቻውን የከፈቱት በሀገሪቱ የኤኮኖሚ ዞን ተብሎ በተለየ አካባቢ መጠነ ሰፊ የሳይበር መጭበርበር ማጋጠሙን ተከትሎ ነው ተብሏል።

ዶቼ ቬለ ከሳምንታት በፊት በርካታ ኢትዮጵያዉያን በላኦስ ፣ ታይላንድ እና ማይናማር በሳይበር አጭበርባሪዎች ተታለው መውጫ አጥተው መቸገራቸውን የተመለከተ ዘገባ ማስደመጡ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቃባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ኢትዮጵያዉያኑን ለማስመለስ በአካባቢው ካሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመነጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ነበር።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንት ሀሙስ ገጠመኝ ባለው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ 42 በረራዎችን መሰረዙን አልያም ማዘግየቱን አስታወቀ።

 አየር መንገዱ አጋጥሞት በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ በረራ በመሰረዙ ከአውሮፕላን አንወርድም በማለት አምባጓሮ ያስነሱ ግለሰቦችን በህግ ሊጠይቅ እንደሚችል ገልጿል። የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ትናንት ሀሙስ ገጠመኝ ባለው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ 42 በረራዎችን መሰረዙን አልያም ማዘግየቱን ገልጿል። አየር መንገዱ እንዳለው ትናንት ምሽት  ወደ መቐለ ለመብረር በተዘጋጀ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ተሳፋሪዎች የበረራውን መሰረዝ መቀበል ባለፈለግ አምባጓሮ ቀስቅሰዋል ፤ ብሏል።

የአየር መንገዱ የህዝብ ግንኙነት እና ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሃና አጥናፉ ለዴቼ ቬለ እንዳሉት በግለሰቦች ተፈጠረ የተባለው አምባጓሮ የጥፋት ደረጃ በህግ ባለሞያዎች እየታየ ነው።

«ትናንት ከደንበኞቹ የተወሰኑት አንወርድም በሚል አምቧጋሩ ያስነሱት ከበድ ያለ ጥፋት ነው አይደለም የሚለው በህግ ክፍላችን እየታዬ ስለሆኑ ከበድ ወዳሉት ጥፋቶች ጎሮ ከገባ በህግ የሚጠየቁ ነው የሚሆነው »

ድምጻዊ እና በቲክ ቶክ የማህበራዊ መገናኛ በርካታ ተከታዮች ያሉት ጆን ዳንኤል ከአየር መንገዱ ሰራተኞች ጋር በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረውን ንትርክ በቀጥታ ስርጭት ሲያስተላልፍ በርካቶች ተጋርተውታል። ጆን ዳንኤልን ጨምሮ በአምባጓሮው ተሳትፈዋል የተባሉ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ የኮሙኒኬሽን ኃላፊዋን ጠቅሶ የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዩም ጌቱ ዘግቧል

 

በሶማሊያ ከአልሸባብ ጂሃዲስት ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሞት ቅጣት በተፈጸመባቸው  አራት ወጣቶች ጉዳይ ላይ «ጥልቅ ሀዘን »  እንደተሰማው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታወቀ።

ዩኒሴፍ እንዳለው በሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ ፑንትላንድ ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ 4 ዕድሜያቸው 18 ያልሞላ ታዳጊ ወጣቶች በሞት ተቀጥተዋል።

ድርጅቱ "የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔዎች የተሰጡ ልዩ የህጻናት ፍትህ ሂደቶች በሌሉት እና ለህጻናት ቦታ በማይሰጡ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ነው" ሲል በመግለጫው አትቷል።

 የፑንትላንድ ባለስልጣናት ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ህጻናት እንደ ተጎጂ እንዲቆጥሩ ያሳሰበው ዩኒሴፍ   ህጻናት በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዳይዳኙ፣ ተገቢ የዳኝነት አካሄዶችን እንዲያገኙ እና «ልጅ» ከሚለው ትርጉም ጋር የተጣጣሙ የፍትህ ሂደቶች እንዲከተሉ ጠይቋል።

በፑንትላንድ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በጋልካዮ ከተማ በዋለው ችሎት ግድያ እና የቦምብ ጥቃት ፈፅመዋል የተባሉ 10   የአልሸባብ አባላት በተላለፈባቸው የሞት ፍርድ ባለፈው ቅዳሜ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን የሶማሊያ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ዓለማቀፉ የሰብአዊ ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው የጎርጎርሳዉያን ዓመት 2023 38 ሰዎች በሞት መቀጣታቸውን አስታውሷል።

 

በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን የሰብአዊ ርዳታ የጫኑ የተወሰኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከቻድ ተነስተው ዳርፉር መግባታቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ርዳታን ጨምሮ ሱዳን የደረሰው የርዳታ ቁሳቁስ በአስከፊ ረሃብ ውስጥ ለወደ,ቁ 13 ሺ ሱዳናዉያን ቅድምያ እንደሚሰጥ ዓለማቀፉ ድርጅት አስታውቋል። ዛሬ የቻድን ድንበር አቋርጠው ዳርፉር የደረሱት የጭነት ተሽከርካሪዎች ማሽላ ፣ ጥራጥሬ ፣ ሩዝ እና የምግብ ዘይት መጫናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪክ ተናግረዋል።

ከዓለም የምግብ ድርጅት ርዳታ በተጨማሪ ዓለማቀፉ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት IOM    አስቸኳይ የሰብአዊ ረድኤት ለሚሹ 12 ሺ ተፈናቃዮች የሚውል የርዳታ ቁሳቁስ መላኩን አስታውቋል።

በቻድ ድንበር የተከፈተው የሰብአዊ ርዳታ መተላለፊያ ለመጭዎቹ ሶስት ወራት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ የሱዳን መንግስት አስታዉቋል።

በሱዳን በሁለቱ ጄነራሎች በሚመሩ ወታደራዊ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው እና 16 ወራት ባስቆረው ጦርነት ከሞቱት፣ ከቆሰሉት እና ከተፈናቀሉት በተጨማሪ 25 ሚሊዮን የሚሆኑት ለረሃብ መጋለጣቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

 

እስራኤል ባለፉት 24 ሰዓታት ጋዛ ውስጥ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች 24 ፍልስጥኤማዉያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚንስቴር አስታውቋል።

እስራኤል በበኩሏ ከትናንት ሐሙስ አንስቶ በርካታ የሃማስ ታጣቂዎች መግደሏን ገልጻለች። ጋዛ ካን ዩኑስ ውስጥ የሚገኝ የሃማስ ታጣቂዎች የሚገለገሉበትን ዋሻ ማውደሟንም አስታውቃለች። የፍልስጥኤማዉያን ዜና አገልግሎት ዋፋ እንዳለው እስራኤል ሰላማዊ ሰዎች በተጠለሉበት የመኖሪያ አካባቢ ባደረሰችው የአየር ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

እስራኤል ግን በአየር ጥቃቱ የሃማስ የሮኬት ማስወንጨፊያ ጣቢያን ማጥቃቷን ነው የገለጸችው ።

በተያያዘ በሰሜናዊ እስራኤል ከሊባኖስ አዋሳን ስፍራዎች ከሂዝቦላ ታጣቂዎች ጋር የሮኬት እና የአየር ጥቃት ልውውጥ መደረጉን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።

በሁለቱም አካባቢዎች ስለተደረጉ ውግያዎችም ሆነ ደረሱ ስለተባሉ ጉዳቶች ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጫ አልተገኘም።

በእስራኤል እና ሀማስ መካከል በጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ዓመት ሊሞላው በተቃረበበት በዚህ ጊዜ ከ40 ሺ ባላይ ፍልስጥኤማዉያን ሲገደሉ ከ2.2 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ጊዜ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

 

ኢራን ለአውሮጳ ሕብረት የእንነጋገር ጥያቄ አቀረበች።

አዲሱ ኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራግቺ በሁለቱ ከቅርብ አመታት ወዲህ በሁለቱ ወገኖች መካከል ተበላሽቶ የቆየውን ግንኙነት ለመመለስ ያለመ ንግግር ከህብረቱ የበላይ ሰዎች ጋር ማድረጋቸው ተሰምቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ትናንት ሐሙስ በሰጡት መግለጫ «ከአውሮፓ ህብረት ጋር በጋራ መከባበር ላይ በተመሰረተ አካባቢ ያለውን የግንኙነ ማደግን በደስታ ይቀበላል» ብለዋል።

የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው በ X ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ   "በጋራ ጥቅም ላይ በሚውሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ እንደገና የመገናኘት ተስፋ የሚያሳድር" ጉዳይ ላይ ከኢራን አቻቸው ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል።

የሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ንግግር «ውጥረት ማርገብ እና ከማባባስ መቆጠብን ጨምሮ በዩክሬን ጦርነት ላይ ከሩስያ ጋር «ወታደራዊ ትብብር ማቆም» ን ማካተቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ስልጣናቸውን በይፋ የተረከቡት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራግቺ ለምዕራቡ ዓለም ባላቸው ግልጽነት ይታወቃሉ ።

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።