1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2016

የነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና በኮንሶ ዞን ዋና ከተማ ሰገን የገቡት ታጣቂዎች ከተማዋን ተቆጣጠሩ፤የፖሊስ አባላትና ሰላማዊ ሰዎችንም ገደሉ። የ7 ዓመትዋን ሄቨን አዎትን አስገድዶ በመድፈርና አንቆም በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ጌትነት ባዬ ላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን የ25 ዓመት የእሥር ፍርድ በመቃወም በበይነ መረብ ፊርማቸውን ያኖሩ ሰዎች ቁጥር ዛሬ ከ240 ሺህ በላይ መድረሱ ተገልጿል። ኬንያ ውስጥ በርካታ ሰዎችን በተከታታይ በመግደል ተጠርጥሮ የታሰረው ኬንያዊና 12ኤርትራውያን እስረኞች ናይሮቢ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያመልጡ በመርዳት የተከሰሱ አምስት የኬንያ ፖሊሶች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

https://p.dw.com/p/4jkrG

 

ታጣቂዎች የሰገን ከተማን ተቆጣጠሩ፤የፖሊስ አባላትና ሰላማዊ ሰዎችንም ገደሉ

 

የታጠቁ ቡድኖች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን የሚገኘውን የሰገን ከተማን መቆጣጠራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ሰገን የገቡት ታጣቂዎቹ ሰባት የወረዳውብ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ 12 ሰዎች መግደላቸውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ከዚያም የወረዳው አመራሮች ወደ ካራት ከተማ መሸሻቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።  ሁለት የከተማው ነዋሪዎች እንዳሉት አካባቢው እስከ ዛሬ ረፋድ ድረስ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ነው ፡፡

ሌላ የከተማው ነዋሪ “ በአሁኑ ወቅት ከታጣቂዎቹ በስተቀር በአካባቢው የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎችም ሆኑ በሥራ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት የሉም ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ዶቼ ቬለ ስለጥቃቱ ያነጋገራቸው የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ ቁጥሩን ባይናገሩም በከተማው በተፈጸመ ጥቃት የፖሊስ አባላት እና ሲቪሎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል። እሳቸው እንዳሉት ግድያው አሰቃቂ ነው።

አቶ ሠራዊት አካባቢውን ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል። ፖሊሶቹ የተገደሉት ቅዳሜ እና እሁድ ከታጣቂዎቹ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሲሆን የነዋሪዎቹ ህይወት ያለፈው በተኩስ ልውውጥ መኻል በተባራሪ ጥይት ተመተው እንደነበርም ተገልጿል።በአካባቢው የተደራጁ ቡድኖችንም የሰገን ዙሪያ ወረዳን ከኮንሶ ዞን በመነጠል የራሳቸውን አስተዳደር ለመመሥረት እንደሚንቀሳቀሱ ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከሀዋሳ ዘግቧል።

 

 

መቀሌ     የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋዜጣዊ መግለጫ

የትግራይ ክልል ኃይሎች ከማንኛውም የፖለቲካ ኃይል እና  ውግንና ገለልተኛ ሆነው እንደሚቀጥሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት እና የክልሉ  የፀጥታ ኃይሎች አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ አስታወቁ። ጀነራል ታደሰ የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ አለመግባባት ወደተለየ ሁኔታ እንዳይሸጋገር ወይም የሰላምና ፀጥታ ችግር እንዳይፈጥር፥ የሚመሩት ኃይል በገለልተኝነት እና በጥንቃቄ እየሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።ለክልሉ መገናኛ ብዙሐን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጀነራል ታደሰ ዛሬ በሰጡት ማብራሪያ በትግራይ ፖለቲካዊ ውጥረት መንገሱን አንስተው የትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ግን የማንም ወገን ደጋፊ ሳይሆኑ ገለልተኛ ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል። ጀነራል ታደሰ እንዳሉት በትግራይ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ የውጭ  ኃይል ተፅእኖም ይሁን ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት አይኖረውም። በትግራይ በማእድናት ምዝበራ፣ ብረታብረት ዝርፍያ እና ሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ አካላትን እየለዩ ለሕግ ማቅረብ እንደሚቀጥል  ጀነራል ታደሰ ወረደ ማስታወቃቸውንም ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ከመቐለ ዘግቧል።

 

አዲስ አበባ    የህፃን ፊቨን ደፋሪ እና ገዳይ ብይን አንሷል የሚለው ተቃውሞ በበይነ መረብ ተጠናክሯል

 

በ7 ዓመትዋ ሄቨን አዎት ላይ ከአንድ ዓመት በፊት የተፈጸመው አረመኔያዊው አስገድዶ መድፈርና ግድያ  በመላ ኢትዮጵያ የቀሰቀሰው ቁጣ አሁንም አልበረደም። ብዙዎች ህጻን ሄቨንን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደላት ወንጀለኛ የተላለፈበት ብይን ከድርጊቱ ጋር የማይመጣጠን ነው ይላሉ ። ሄቨንን አስገድዶ የደፈረውና አንቆም በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ጌትነት ባዬ ላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን የ25 ዓመት የእሥር ፍርድ በመቃወም በበይነ መረብ ፊርማቸውን ያኖሩ ሰዎች ቁጥር ዛሬ ከ240 ሺህ በላይ መድረሱ ተገልጿል። ፈራሚዎቹ ለህጻኗ ፍትህ እንዲሰጣት በመጠየቅዋ ማስፈራራያ ይደርስባታል ላሉዋት ለሄቨን እናት ጠንካራ ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላትም ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ የሴቶችና የማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ መስሪያ ቤታቸው  ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን ጉዳዩን እንደሚከታተል በፌስቡክ ገጻቸው ማሳወቃቸው ተዘግቧል። ባለፈው ዓመት ባህርዳር ውስጥ ወንጀሉን በመፈጸም በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለው ጌትነት «ይግባኝ» ለማለት ማቀዱን  የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። መንግሥታዊው የኢትዮጵፕያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን እንደዘገበው የባህርዳር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህጻን ሔቨንን የሞተችው በግለሰቡ የተፈጸመባትን  አስገድዶ መድፈር መቋቋም ባለመቻሏ ምክንያትና ስላነቃትም ጭምር ነው ሲል ወስኗል።  ህጻን ፌቨን ተደፍራ የተገደለችውም ራሱ ጌትነት ባከራያቸው ቤት ውስጥ ነበር። 

 

ናይሮቢ     አምስት የኬንያ ፖሊሶች ከእስር ባመለጡት በነፍስ ግድያ በተጠረጠረው ሰውና በ12 ኤርትራውያን እስረኞች ገዳይ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ኬንያ ውስጥ በርካታ ሰዎችን በተከታታይ በመግደል ተጠርጥሮ ከአንድ ወር በፊት የታሰረውን ኮሊን ጁማይሲን ጨምሮ ሌሎች 12 እስረኞች በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያመልጡ በመርዳት የተከሰሱ አምስት የኬንያ ፖሊሶች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። በፖሊስ ዘገባ መሠረት በግድያ ከተጠረጠረው ኬንያዊው ነፍሰ ገዳይ በተጨማሪ ከእስር ያመለጡት አስራ ሁለቱ ኤርትራውያን ናቸው። አቃቤ ሕግ ማክሰኞ እለት እስር ቤቱ ሲጣስ ጥበቃ ላይ የነበሩት ፖሊሶች  በቁጥጥር ስር እንዲውሉና የፖሊስ መኮንኖችም ምርመራውን እንዲያጠናቅቁ የሁለት ሳምንታት ጊዜ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ከእስር ቤት ካመለጡት ውስጥ ቢያንስ 6 ሴቶችን ገድሎ የተቆራረጠ አስከሬናቸውን በፕላስቲክ ጠቅሎ ቆሻሻ መጣያ ስፍራ ጥሏል በሚል ባለፈው ወር የታሰረው ኮሊን ጁማይሲ ባለቤቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን በተመሳሳይ መንገድ መግደሉን አምኗል። ጠበቃው ግለሰቡ ድርጊቱን ያመነው ቁም ስቃይ ስለደረሰበት ነው  ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል። ምንም ዓይነት በደል አልተፈጸመበትም ያለው አቃቤ ሕግ ክሱን ውድቅ አድርጎታል።  ከእስር ስላመለጡት ሰዎች የተካሄዱ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች እስረኞቹ እንዲያመልጡ ውስጥ አዋቂዎች እንደረዷቸው አሳይተዋል ሲል ፖሊስ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ያመለጡትን እስረኞች መልሶ ለመያዝ ፖሊስ እያደናቸው መሆኑንም አስታውቋል።

 

ለንደን         ብሪታንያ በኮንጎ በፍጥነት በመሰራጨት ላይ ያለውን ፈንጣጣ ለመከላከል የገንዘብ እርዳታ ለመስጠት ቃል ገባች

የብሪታንያ መንግሥት በፍጥነት መስፋፋት ላይ ያለውን የፈንጣጣ በሽታን ስርጭት ለመከላከል የ3.1 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም የ4 ሚሊዮን 40 ሺህ ዶላር  እርዳታ ለመስጠት ቃል ገባ። በሽታው በተስፋፋበት በኮንጎ ዴሞክራሲያዎት ሪፐብሊክ የሚገኘውን ብሔራዊ የባዮ ሜዲካል የምርምር ተቋምን ዛሬ የጎበኙት የብሪታንያ የአፍሪቃ ጉዳዮች ሚኒስትር ሬይ ኮሊንስ  እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመባል ይታወቅ የነበረውን የዚህን በሽታ ስርጭት ለመግታት ቃል የተገባው ይህ እርዳታ ሁላችንንም ይጠቅማል ብለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2024 በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ 15 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው በሐኪም ሲረጋገጥ ከ500 በላይ ደግሞ መሞታቸው ተዘግቧል። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ባለፉት 7 ወራት በሀገሪቱ ከ20 ሺህ 770 በላይ ሰዎች በኮሌራ መያዛቸውንም እንደደረሰበት አስታውቋል። በተመሳሳይ ደረጃም ኮሌራ በኢትዮጵያ በዛምብያ እና በዚምባብዌ እንዳለም ገልጿል። የዓለም ጤና ድርጅት በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የተሰራጨውን ፈንጣጣ ባለፈው ሳምንት አሳሳቢ ብሎታል። የድርጅቱ ሃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በተለይ በዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚታየውን ፈጣኑን የበሽታውን ስርጭት አስጨናቂ ነው ያሉት።

 

እስራኤል አንድ የፋታህ ወታደራዊ ክንፍ ከፍተኛ ተዋጊን ዛሬ  ገደለች።

 

እስራኤል ዛሬ ሊባኖስ ውስጥ ባካሄደችው የአየር ድብደባ  አንድ የፋታህ ወታደራዊ ክንፍ ከፍተኛ ተዋጊን ገደለች። ይህ የአየር ድብደባ ከፍልስጤማውያን ንቅናቄ በኩል እስራኤል በአካባቢው ጦርነት ለመጫር እየሞከረች ነው የሚል ክስ አስነስቶባታል። እስራኤል እንዳለችው ጥቃቱ ያነጣጠረው የፋታህ ታጣቂ ክንፍ የሊባኖስ ቅርንጫፍን የሚመራው የሙኒር ማቅዳህ ወንድም ላይ ነው። እስራኤል ወንድማማቾቹን በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ  ጥቃት እንዲፈጸም በመምራትና የጦር መሣሪያዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በማሻገር እና ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር በመተባበር ከሳቸዋለች።  በፍልስጤማውያኑ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስና በሃማስ የሚመራው የፈታህ ንቅናቄ እስራኤልን በአካባቢው መጠነ ሰፊ ጦርነት እንዲነሳ ለማድረግ በመሞከር ከሰዋታል። የዛሬው የማግዳህ ላይ ግድያ ከ10 ወራት ወዲህ በአንድ የፈታህ አባል ላይ የተፈጸመ የመጀመሪያው ጥቃት ነው ተብሏል።

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።