1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና ጡንቻ-የኃያላን ፍጥጫ

ሰኞ፣ የካቲት 27 2015

ትናንት የተሰየመዉ የቻይና ብሔራዊ ሕዝባዊ ጉባኤ (NPC) የሐገሪቱን ጦር ኃይል ይበልጥ ለማጠናከርና ዘመናይ ጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ የጦሩ በጀት በ7.2 ከመቶ እንዲጨምር ወስኗል።የጉባኤዉ ቃል አቀባይ ዋንግ ቻኦ እንደሚሉት ቻይና ጦር ኃይሏን ለማዘመን መወስኗ ለዓለም ሰላም ጠቃሚ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4OK4V
China | Eröffnung vom 14. Nationalen Volkskongress
ምስል Lintao Zhang/Getty Images

የቻይና እና የዩናይትድ ስቴትስ ሽኩቻ

ዩክሬንን የሚያወድመዉ ጦርነት ከኪየቭ-ሞስኮዎች ጠብ ይልቅ የዋሽግተን-ሞስኮዎች ሽኩቻ ንረት ዉጤት መሆኑን የማይናገር ታዛቢ የለም።ጦርነቱ የአሜሪካና የምዕራብ አዉሮጳ መንግስታትን አንድነት ከማረጋገጥና ከማክሰር  አልፎ የሶቭየት ሕብረት ሳተላይት ይባሉ የነበሩ የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት ዋሽግተንን ሙጥኝ እንዲሉ አስገድዷል።በተቃራኒዉ ጎራ ቤሎሩስ፣ኢራን፣ሰሜን ኮሪያን ከሞስኮዎች ጎን አቁሟል።ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ዓይንና ናጫ ብትሆንም ዉጊያ-ዉዝግቡን አድፍጣ ለማለፍ  የምታድባዉ ቤጂግም ጭልጥ ብላ ከሞስኮዎች ጎን ትቆማለች የሚለዉ ሥጋት እያየለ ነዉ።የስጋቱ ክብደት-ቅለት፣የኃይል አሰላለፉ እንዴትነት፣ የዓለም ሰላም መናጋት አነጋግሮ ሳያበቃ ቻይና ጦር ኃይሏን ይበልጥ ለማጠናከር ወሰናለች።የቻይና ዉሳኔ መነሻ፣ ምክንያት-እንድምዉ ማጣቃሻ፣ የዓለም ሰላም እንዴትነት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

በ2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የካረቢያዊቱን ሐገር ሀይቲን በመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋና መዘዙ  ከ220 ሺሕ በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።የሐይቲ መንግስት እንዳስታወቀዉ አደጋዉ በቀጥታ ከገደለዉ ሕጥብ ቁጥር ያልተናነሰ ሕዝብ በሕክምና እጦት፣ በምግብ እጥረትና በበሽታ አልቋል።

የቻይና ፕሬዝደንት ወታደራዊ ሰልፍ ሲጎበኙ
የቻይና ፕሬዝደንት ወታደራዊ ሰልፍ ሲጎበኙምስል Li Tao/Xinhua/Imago Images

የአደጋዉን መጠን፣ በአደጋዉ ለተጎዳዉ ሕዝብ ፈጣን ርዳታ አለመድረሱንና የሐይቲን ሕዝብ ድሕነት የታዘበ አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ያኔ እንደዘገበዉ የዓለም ትልቅ ሐብት ከተከማቸና ከሚገላበጥባት ኒዮርክ  ሐይቲ ርዕሰ ከተማ ፖርት ኦ ፕሪንስ ለመድረስ የሚፈጀዉ 3 ሰዓት ተኩል በረራ ነዉ።«የመጀመሪያዉ የዩናይትድ ስቴትስ ርዳታ ፖርት ኦ ፕሪንስ የደረሰዉ ግን ከ3 ቀን  በኋላ ነዉ።አንድ ቢል ጌት የአንድ ወር ገቢዉን ለሐይቲ ቢሰጥ 70 ከመቶ የሚሆነዉ የሐይቲ ሕዝብ አስተማማኝ መኖሪያ ያገኝ ነበር---» እያለ ፃፈ።

ዓለም ዛሬ ከኢትዮጵያ እስከ ምያንማር፣ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እስከ የመን 340 ሚሊዮን  ሕዝብ ወይም ከ23ቱ ሰዉ አንዱ ሕይወቱ እንዲቀጥል አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ ይጠብቃል።የሶሪያ ስደተኛ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ የምያንማር በእሳት ቃጠሎ ይሞታል ወይም ዳግም ይሰደዳል።የዓለም ቱጃሮች ግን ለጦርነት ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር ይከሰክሳሉ።

የወታደራዊ ጉዳይ አጥኚዎች እንዳሉት የዓለም መንግስታት ከ2.1 ትሪዮሊዮን ዶላር በላይ ለጦር መሳሪያና ለወታደር ያወጣሉ።በየዓመቱ ለጦር ኃይል ከፍተኛዉን ገንዘብ በመመደብ፣ በጦር ኃይልና በጦር መሳሪያ ጥራትና ብዛት ዩናይትድ ስቴትስን የሚያክል የለም።ዩናይትድ ስቴትስ በግሪጎሪያኑ 2021 801 ቢሊዮን ዶላር አዉጥታለች።ቻይና ትከተላለች 293 ቢሊዮን።

ትናንት የተሰየመዉ የቻይና ብሔራዊ ሕዝባዊ ጉባኤ  (NPC) የሐገሪቱን ጦር ኃይል ይበልጥ ለማጠናከርና ዘመናይ ጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ የጦሩ በጀት በ7.2 ከመቶ እንዲጨምር ወስኗል።የጉባኤዉ ቃል አቀባይ ዋንግ ቻኦ እንደሚሉት ቻይና ጦር ኃይሏን ለማዘመን መወስኗ ለዓለም ሰላም ጠቃሚ ነዉ።

«የቻይና የወደፊት ዕጣ ከዓለም ዕጣ ጋር የተቆራኘ ነዉ።ቻይና ጦሯን ለማዘመን መወስኗ ለየትኛዉም ሐገር ሥጋት አይደለም።ይልቁንም የአካባቢዉን መረጋጋት ለማስጠበቅና ለዓለም ሰላም ጥሩ ርምጃ ነዉ።»

የቻይና ወታደራዊ ትርዒት
የቻይና ወታደራዊ ትርዒትምስል AP

ፖለቲካኛና ዕዉነት!!! ግን ሌላ ምን ይላሉ።«ሐገር ልንወር ነዉ» ይላሉ ተብሎ አይጠበቅም።ቻይና እንደ አፈንጋጭ ግዛትዋ የምትቆጥራት የታይዋን ባለስልጣናት ግን ቻይና ግዛታችንን ልትወር እየተዘጋጀች ነዉ ይላሉ።የታይዋን መከላከያ ሚንስትር ቺዩ ኩዮ-ቼንግ ዛሬ እንዳሉት ቻይና ጦር የታይዋን የባሕር ግዛትን ለመዉረር ዝግጅቱን እያጋመሰ ነዉ።

«የቻይናን እንቅስቃሴ በቅርብ እየተከታተል ነዉ።አምናም ሆነ ሐቻምና የሚያሰፍሩት ጦር ቁጥር እየጨመረ ነዉ።----ዘንድሮ ለፓራላማዉ ባቀረብኩት ዘገባም ዝግጅታቸዉን እያጋመሱ ሳይሆን እንዳልቀረ አሳዉቄያለሁ።---ወታደራዊ እርምጃ ለመዉሰድ እየተዘጋጁ ነዉ።»

ቻይና የግማደ ግዛትዋ አካል አድርጋ የምታያት ታይዋን ሶማሊላንድን ከመሳሰሉ ጥቂት ሐገራት በስተቀር በዓለም የመንግስትነት እዉቅና የላትም።የታይዋን የቅርብ ወዳጅ ዩናይትድ ስቴትስም ታይዋንን ጨምሮ የቻይናን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት እንደምታከብር የሚያረጋግጥ ዉል ከብዙ ዓመታት በፊት ከቻይና ጋር ተፈራርማለች።

ይሁንና እያበጠ የመጣዉን የቻይናን ምጣኔ ሐብት-ለማስተንፈስ፣የዓለምን ገበያ የመቆጣጠር ፍላጎቷንና ግስጋሴዋን ለማሰናከል ከሁለቱም በላይ በቻይና  ላለመበለጥ፣ ታይፔ ለዋሽግተኖች ጥሩ መያዢያ ናት።እንደ ጃፓን፣ደቡብ ኮሪያና ሕንድን የመሳሰሉ የአካባቢዉ መንግስታትም የዋሽግተኖችን ፍላጎት ለማስፈፀም በተጠንቀቅ ቆሞዋል።

በቅርብ ዓመታት ደግሞ ዩናንይትድ ስቴትስ ለታይዋን የምታስታጥቀዉን የዘመናይ ጦር መሳሪያ በዓይነትም በብዛትም ጨምራለች።የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲን ጨምሮ የአሜሪካ የምክር ቤት እንደራሴዎችና ሚንስትሮች ወደ ታይፔ እየተመላለሱም ነዉ።

ዋሽግተኖች ታይዋንን በጣሙን ሙሉ ነፃነት ለማወጅ የሚሹ የታይፔ ፖለቲከኞችን «እሹሩሩ» ማለታቸዉ፣ የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ በቅርቡ እንዳሉት  የቤጂንጎችን ትዕግስት እየተናነቀ ይመስላል።

 «ዩናይትድ ስቴትስ የግዛት ሉዓላዊነትን እንደምታከብር ትናገራለች።ይሁንና እስከ ጠረፍ ድረስ እየገፋች፣በታይዋን ጉዳይ የገባችዉን ቃል እየጣሰች፣ በጣም ዘመናይ ጦር መሳሪያ ሳይቀር የቻይና ግዛት ለሆነችዉ ታይዋን እየሸጠች ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ሰላም እፈልጋለሁ ትላለች።ነገር ግን በመላዉ ዓለም ጦርነት እየጫረች፣ፍጥጫን እያባባሰች ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ባንድ በኩል የዓለም ሥርዓት እንዲከበር እየጎተጎተች፣በሌላ በኩል ከዓለም ሕግ ይልቅ የራስዋን ሕግ አስቀድማ  ሕገ ወጥ የተናጥል ማዕቀብ ትጥላለች።»

የዩናይትድ ስቴትስና የቻይና ጠብ መነሻ ታይዋን ብቻ አይደለችም።ቻይና ሰሜን ኮሪያን በዲፕሎማሲና በምጣኔ ሐብት መደገፏ፣ ከኢራን ጋር ቢያንስ በንግድ መተሳሰሯም ዓለም ለመቆጣጠር ለሚሻሙት ለሁለቱ ሐብታም ሐገራት ጠብ ሌላዉ ምክንያት ነዉ።

የቻይና ከፍተኛ ዋንግ ዪ ዲፕሎማት በሙኒክ ጉባኤ
የቻይና ከፍተኛ ዋንግ ዪ ዲፕሎማት በሙኒክ ጉባኤምስል Johannes Simon/Getty Images

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር አንዴ በተንሳፋፊ ፊኛ፣ ሌላ ጊዜ በቀረጥ፣ደግሞ ሌላ ጊዜ በንግድ ዉል ጥሰት ሰበብ በቻይና ኩባንዮችና ባለስልጣናት ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀብ ጥሏል።

በዩክሬኑ ጦርነት ቻይና ከምዕራባዉያን ይልቅ ወደ ሞስኮ ማጋደሏ ደግሞ የዋሽግተን ብራስልስ\ ለንደን ተሻራኪዎችን «ፀጉር ያቆመ» መስሏል።

የቻይና ትልቅ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ በይፋ እንዳስታወቁት በቅርቡ ወደ አዉሮጳ የመጡት የዩክሬኑን ጦርነት በሰላም ለማስቆም የሚቻልበትን ብልሐት ለማፈለግ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ግን ለቻይናዊዉ ዲፕሎማት ቻይና ገና ለገና ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ታቀብል ይሆናል በማለት የማስጠንቀቂያ ዉለታ መልሰዉላቸዋል።

 «ሩሲያ ዩክሬን ላይ ለከፈተችዉ ጦርነት ቻይና ገዳይ መሳሪያ ለመስጠት እያሰበች ነዉ መባሉ በጣም አሳስቦናል።ጉዳዩን በጣም፣በጣም በቅርበት እየተከታተል ነዉ።ከዚሕ ቀደም እንዳልኩትና ፕሬዝደንት ባይደን ከብዙ ወራት በፊት ወረራዉ እንደተጀመረ ለፕሬዝደንት ሺ ጂፒንግ እንደነገሩት ቻይና ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ከሰጠች፣ ወይም በሩሲያ ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ የሚያፈርስ ድጋፍ ካደረገች ከፍተኛ አፀፋ ይገጥማታል።»

ለብሊከን ወቀሳና ማስጠንቀቂያ  ከቤጂንግ የተሰማዉ አፀፋ ሁለቱ ሐገራት የከበሩ፣የነሰሩ ጉልበት ያፈረጠሙበትን ዓለም ወደ ሰላም ሳይሆን ወደ ተጨማሪ ፍጥጫ እየነዱት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነዉ።የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን  ያነሱት ጥያቄ ግን ዕዉነትን ለሚሻ ደጋግሞ እንዲያሰላስል የሚገፋፋ ነዉ።

«ወደ ጦር ግንባር ጦር መሳሪያ የምታግዘዉ ዩናይትድ ስቴትስ እንጂ ቻይና አይደለችም።ዩናይትድ ስቴትስ ቻይናን የማዘዝ መብት የላትም።ስለቻይና-ሩሲያ ግንኙነትም ለማረምና ግፊት ለማድረግ ቀርቶ ጣትዋን መቀሰሯን እንኳን አንቀበልም።በዩክሬን ጉዳይ ላይ የቻይና አቋም ባንድ ዓረፍተ ነገር የሚጠቃለል ነዉ።ሰላም ለማስፈን ድርድር ማራመድ።እሳቱን የሚያቀጣጥለዉ ማነዉ? ጦር መሳሪያ የሚያቀብለዉ ግጭትን የሚያባብሰዉ ማነዉ? ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጥርት እንዳለ ቀን በግልፅ እያየዉ ነዉ።»

የዩክሬኑን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ከቻይና በፊት ቱርክና ብራዚል ያቀረቡት ሐሳብ ዓየር ላይ ቀርቷል።ቻይና ያቀረበችዉን  ሐሳብ ደግሞ የአዉሮጳ ሕብረት ባለስልጣናት መርሕ እንጂ እቅድ አይደለም በማለት አጣጥለዉታል።ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራዉና ለዩክሬን ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጠዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) በበኩሉ ቻይና ለአደራዳሪነት አትታመንም በማለት ዉድቅ አድርጎታል።

አንቶኒ ብሊንከን የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር
አንቶኒ ብሊንከን የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ምስል Michael Varaklas/REUTERS

ትናንት የተሰየመዉ የቻይና ብሔራዊ ሕዝባዊ ጉባኤ የሰፊ፣ ትልቅ፣ሐብታም የ1.2 ቢሊዮኖቹ ሐገር የመጨረሻዉ የፖለቲካ አካል ነዉ።ጉባኤዉ የሐገሪቱን ጦር ኃይል በጀት ከመጨመር ሌላ የሐገሪቱ  የምጣኔ ሐብትም በ5 ከመቶ እንደሚያድግ ተንብዩዋል።

የዩክሬኑ ጦርነት ቀጥሏል።የኮሪያ ልሳነ ምድር፣ ካሽሚር፣ የሕንድ-ቻይና ድንበር ኑክሌር ተደግኖባቸዋል።መካከለኛዉ ምስራቅና አፍሪቃ ጦርነት እየዘከሩ በጦርነት ይዳክራሉ።ድፍን ዓለም ሰላም አጥታ ስትቃትት፣ከ340 ሚሊዮን  ሕዝቧ ምፅዋት ሲማፀን ኃያላን ጦር መሳሪያ ለማጋበስ ይጣደፋሉ።ኢትዮጵያዊዉ የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅወያ ዓለም በቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የነበሯት መሪዎች ይበልጥ ጠንቃቃ ነበሩ ይላሉ።ትናንት በርግጥ ዛሬ አይደለም።ዓለም ግን ሰላሟን ለማግኘት የ1970ና 80ዎቹን ብልሆች የምትናፍቅ ትመስላለች።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ