1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ.ክ ዉዝግብ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 18 2015

ቤተ ክርስትያኗ "በጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል ከሚገኙት ሀገረ ስብከቶች ጋር ተቋርጦ የነበረው መዋቅራዊ ችግር በውይይት እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት በማዕከላዊ አክሱም ሀገረ ስብከት በአክሱም ፅዮን ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ ያሳዘነ ድርጊት ተጽሟል ብላለች።

https://p.dw.com/p/4UNZt
Ethiopian Orthodox church press briefing in Addis Abeba Ethiopia today
ምስል Seyoum Hailu/DW

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቃዉሞ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ክልል በማዕከላዊ አክሱም ሀገረ ስብከት በአክሱም ፅዮን ቤተ ክርስትያን የትግራይ ኢጲስቆጾሳት ሲመት ተደረገ መባሉ እንዳሳዘነዉ አስታወቀ።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  "የዶግማ ፣ የቀኖና እና የአስተዳደር ጥሰት" ተፈጽሟል ባለችው ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ላይ  ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 25 ቀን 2015  አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ  ጉባኤ ጠራታለች።የትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢጲስ ቆጶሳት ሲመት ከመስጠቷ በፊት መንግስት እርምጃዉን እንዲያስቆም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠይቃ እንደነበር አስታዉቃለች።

ቤተ ክርስትያኗ "በጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል ከሚገኙት ሀገረ ስብከቶች ጋር ተቋርጦ የነበረው መዋቅራዊ ችግር በውይይት እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት በማዕከላዊ አክሱም ሀገረ ስብከት በአክሱም ፅዮን ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ ያሳዘነ ድርጊት ተጽሟል ብላለች። በተጠራው አስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤ ላይ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲገኙ ጥብቅ መልዕክት ያስተላለፈችው ቤተ ክርስትያኗ በጉባኤው ላይ አለመገኘት የቤተክርስትያንን ውድቀት ማፋጠን ነው ስትል አሳስባለች። 
በትግራይ ክልል ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳቱ ከመከናወኑ በፊት ድርጊቱን ማንግሥት እንዲያስቆም ጠይቃ የነበረቸው ቤተ ክርስትያኗ ይህ ሳይሆን ቢቀር "የመጀመርያው ተወቃሽም ፣ ተከሳሽም የፌዴራል እና የትግራይ ክልል መንግሥታት ናቸው ብላ ነበር።
በጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል ከሚገኙት ሀገረ ስብከቶች ጋር ተቋርጦ የነበረው መዋቅራዊ ችግር በውይይት እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሁም ቅዱስ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በአካል በመጓዝ ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም " ሕገ ቤተ ክርስትያንን እና ቀኖና ቤተ ክርስትያንን በመጣስ በማዕከላዊ አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ፅዮን ቤተ ክርስትያን ሐምሌ 15 እና 16 ቀን 2015 ዓ. ም ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ተከናውኗል" በማለት ትናንት በሰጡት መግለጫ የጠቀሱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አቡነ ጴጥሮስ በዚህ የዶግማ ፣ የቀኖና እና የአስተዳደር ጥሰት የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በእጅጉ አዝኗል ብለዋል።
ይህ የሀገሪቱ ችግር ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው "ምድሪቱ ከተሸከመችው መከራ ይህ ሌላ ተጨማሪ መከራ ነው" ሲሉም በሀዘን ገልፀዋል። ይህንን ተከትሎ ቤተ ክርስትያኗ በዚህ ጥሰት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ጥሪ አስተላልፋለች። በዚህ አስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤ ላይ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት እንዳይቀሩ ጥብቅ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን "በጉባኤው ላይ አለመገኘት የቤተክርስትያንን ውድቀት ማፋጠን ነው" ተብሏል። 

Äthiopien Aksum Ordination in orthodoxe Kirche von Tigray
ምስል Million Haileselasie/DW

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 "መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም" ተብሎ ተደንግጓል። ቤተ ክርስትያኗ ከዚህ በፊት ከኦሮሚያ ክልል የቤተ ክርስትያኗ መሪዎች በተነሳ ጥያቄ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን ሞት፣ የአካል መጉደል  እና ሌሎች ችግሮች በምእመኗ ላይ ደርሷል። 

ጉዳዩ የመንግሥትንም ትኩረት ስቦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የካቢኔ አባሎቻቸውን ሳይቀር ሰብስበው ተነጋግረውበት ነበር። "ቤተ ክርስትያኗ በአንድነቷ ፀንታ ትኖር ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት የተፈፀመው ስምምነት እንደ ሥርዓተ አበው፣ እንደ ቀኖና ቤተክርስቲያን እየተጠቀሰ ችግሩን ለመፍታት ተችሏል" በማለት ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የጠቀሱት የቤተ ክርስትያኗ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፅዕ አቡነ አብርሃም መንግሥት በትግራይ ክልል የተከናወነውን ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት አስቀድሞ እንዲያስቆም ጠይቀው ነበር። 

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሢመቱ ቢቀጥል "የመጀመርያው ተወቃሽም ፣ ተከሳሽም በታሪክም ትልቅ መዝገብ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ማን አፈረሳት ቢባል የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ናቸው የሚለው የማይቀር ሀቅ እና እውነታ ነው" ብለው ነበር።
በጉዳዩ ላይ የመንግሥትን ምላሽ ለማድመጥ ወደ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር የእጅ ስልክ ደጋግመን ብንደውልም ጥሪው ምላሽ አላገኘም።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ