የትግራይ ወርቅ በኤርትራ ይወጣል መባሉ ፤ የትግራይ ተቃዋሚዎች እና ኤርትራ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 17 2017ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ከትግራይ በኤርትራ በኩል በኮንትሮባንድ ይወጣል ተብሎ የሚቀርብ መረጃ የኤርትራ መንግስት አስተባበለ። የኤርትራ መንግስት ቃልአቀባይ የማነ ገብረመስቀል በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት ውንጀላው 'መሰረተቢስ' ብለውታል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ አደገኛ ኬሚካሎች ጭምር በመጠቀም የሚደረግ የወርቅ ምዝበራ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላል። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቅርቡ እንዳስታወቁት፣ በወርቅ ማእድን ምዝበራው የክልሉ ከፍተኛ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች እጅ አለበት ብለው ነበር።
በትግራይ በስፋት እየተከወኑ ናቸው ተብለው በክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር፣ የህወሓት ሁለቱ ቡድኖች እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ሌሎች አካላት የሚገለፀው ሕገወጥ የማዕድናት ምዝበራ አሁን ላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በሁሉም አካላት ይታመናል።
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህወሓትን ከሰሱ
በቅርቡ ለክልሉ መንግስት ሚድያዎች ማብራርያ ሰጥተው የነበሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከአራት ወራት ባነሰ ግዜ ውስጥ 28 ኩንታል ወርቅ ከትግራይ ለፌደራል መንግስቱ ገቢ መደረጉ አንስተው የነበሩ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ሕገወጥ የማዕድናት ምዝበራ እና ኮንትሮባንድ መበራከቱም ጠቁመው ነበር። ይህ የወርቅ ማዕድን ምዝበራ አጀንዳ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጉዳት እያስከተለ ስለመሆኑም በጉዳዩ ዙርያ ዳሰሳ አደረግን ያሉ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገልፃሉ።
በትግራይ ተባብሷል የተባለው የፖለቲካ ቀውስና የማዕድን ምዝበራ
የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ "የውጭ ሀገር ዜጎች ኬሚካል ይዘው በድርጅት ስም በመግባት ከአካባቢ እስከ ክልል ባሉ አመራሮች ደግሞ ሕጋዊነት እየተሰጣቸው ምዝበራው ቀጥሏል። በወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ስም በተደራጁ ማሕበራት ካድሬ ተመዝቦባቸው ወርቅ እየመዘበሩ ነው። አደገኛ ኬሚካሎች እየተረጨ ከብቶች ውሃ ሲጠጡ እያለቁ ነው። ለምሳሌ ማይአባይ በሚባል አካባቢ ጠቅላላ ሕብረተሰቡ የሚጠጣው ውሃ አጥቶ ነው የሚገኘው" ብለዋል።
በሕጋዊ መንገድ ለባንኮች ከሚሸጠው ወርቅ በተጨማሪ ከትግራይ ሰሜን ምዕራብ እና ማእከላዊ ዞኖች በሕገወጥ መንገድ የሚመዘር ወርቅ፥ በኤርትራ በኩል እንደሚወጣም በተደጋጋሚ በግዚያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት እና ሌሎች ይነገራል።
ስለዚህ በኤርትራ በኩል ይደረጋል የሚባለው ሕገወጥ የማእድናት ዝውውር፥ የኤርትራ መንግስት ውሸት በማለት አጣጥሎታል። የኤርትራ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገፃቸው በኩል እንዳሉት የህወሓት ሰዎች ብለው የገለፅዋቸው አካላት፥ መነሻው ከትግራይ ያደረገ ወርቅ በኤርትራ በኩል በሕገወጥ መንገድ እየተሸጠ ይገኛል በማለት የሚቀርበው ውንጀላ መሰረት የሌለው ብለውታል። ይህ ውሸት ያሉት ውንጀላም በእነ ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ እንደሚነሳም የኤርትራው ቃልአቀባይ የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል።
የመስፍን ስንብት፤ የፖሊስ ሰልፍ፤ የመቐለና አዲስ አበባ ፍጥጫ
በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ፓርቲ ባይቶና በዚህ የወርቅ ምዝበራ የባለስልጣን ተሳትፎ እንዳለበት በቅርቡ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ተሰጥቶት በነበረ መግለጫ አንስቶ ነበር። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ