1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እና የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት

እሑድ፣ ሐምሌ 16 2015

የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለስድስት ኤጲስቆጶሳት ሹመት ሰጠች። የዛሬ ተሿሚዎች ትግራይ ክልል ውስጥ እና በውጭ ሀገር ቤተክርስቲያኒቱ እና ምእመናኑ የሚያገለግሉ ናቸው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4UHma
Äthiopien Tigray | Orthodoxe Kirche eröffnet
ምስል Million Hailesialssie/DW

የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በትግራይ

የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለስድስት ኤጲስቆጶሳት ሹመት ሰጠች። የዛሬ ተሿሚዎች ትግራይ ውስጥ እና በውጭ ሀገር ቤተክርስቲያኒቱ እና ምእመናኑ የሚያገለግሉ ናቸው ተብሏል።

ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በመለየት መንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቤተክህነት የመሰረቱት በትግራይ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ባስተላለፉት ውሳኔ መሰረት፥ ባለፈው ሳምንት በሃይማኖቱ ምእመናን በድምፅ የተመረጡት ኤጲስቆጶሳት ከትላንት ቅዳሜ እስከ ዛሬ እሁድ፥ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ማርያም ፅዮን ቤተክርስቲያን በተደረገ ስነስርዓት 'አንብሮተ ዕድ' ወይም ሹመት ተፈፅሞላቸዋል። ዛሬ በአክሱም በተደረገው ሃይማኖታዊ የሹመት ስርዓት ላይ፥ ባለፈው ሳምንት ከተመረጡት አስር ኤጲስቆጶሳት መካከል ስድስቱ በአካል ተገኝተው 'አቡነ' የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው፣ ለትግራይ ምዕራብ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ ዞኖች እንዲሁም በአሜሪካ ቨርጂንያ፣ በመቐለ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በመንበረ ሰላማ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። ከትላንት እስከ ዛሬ እሁድ ድረስ የነበረው መንፈሳዊ የቤተክርስቲያኒቱ የሹመት ስርዓት ዙርያ የጠየቅናቸው በመንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፅሕፈት ቤት ፀሓፊ መጋቤ ብርሃናት መምህር ተስፋይ ሃደራ፥ ሁሉም መንፈሳዊ ስርዓቶች ተፈፅመው የኤጲስቆጶሳቱ አንብሮተ ዕድ መፈፀሙ ገልፀውልናል።

Äthiopien Tigray | Orthodoxe Kirche eröffnet
ምስል Million Hailesialssie/DW

ብፁእ አቡነ ሊባኖስ፣ ብፁእ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁእ አቡነ አረጋዊ፣ ብፁእ አቡነ ዮሐንስ፣ ብፁእ አቡነ እምባቆም እና ብፁእ አቡነ ኣትናቴዎስ በጳጳስና እንዲያገለግሉ ዛሬ የተሾሙ ናቸው። በሹመቱ ስነስርዓት ለምእመኑ ንግግር ያደረጉት ከተሿሚዎቹ መካከል የሆኑት ብፁእ አቡነ ዮሐንስ " ጥላአችን ፅዮን ናት፣ መጠግያችን እግዚአብሔር ነው። ለዓለም ሁሉ ይቅርታ፣ ሰላም ይስጥ።ጠላቶች አሉን አንጠላቸውም፣ የሚያሳድዱን አሉ አናሳድድም፣ ሃይማኖታችን እንጠብቃለን፣ ህዝባችን እናስተምራለን፣ ታሪካችን እንመልሳለን፣ መንበረ ሰላማ ነበረ፣ አለ፣ ይኖራል፣ ለትውልድ ይተላለፋል። ይህ የፈቀድክልን አምላክ ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን" ብለዋል።

Äthiopien Tigray | Orthodoxe Kirche eröffnet
ምስል Million Hailesialssie/DW

ከዚሁ የትግራይ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አካሄድ ጋር በተያያዘ በሳምንቱ መጀመርያ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ፅሕፈትቤት፥ ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አህጉረ ስብከቶች ድርጊቱ እንዲያወግዙ፣ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቅ እንዲሁም ቤተክርስቲያኒቱ መብቷ በሕግ እንደምታስከብር የሚጠቁም መግለጫ አውጥቶ ነበር። በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ከመንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተያየት ጠይቀናል።

Äthiopien Tigray | Orthodoxe Kirche eröffnet
ምስል Million Hailesialssie/DW

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባት እንፈልግም፣ የራሳችን መንገድ ይዘናል፣ እነሱም ንትርክ ከሚፈጥር አካሄድ ቢቆጠቡ መልካም ነው ያሉት በመንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፅሕፈት ቤት ዋና ፀሓፊ መጋቤ ብርሃናት መምህር ተስፋይ ሃደራ፥ ይህንኑ ሁኔታ ግን የትግራይ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ጉዞ ወደኃላ እንደማይመልስ ጨምረው ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ በአክሱም በነበረ ስነስርዓት የመንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዋና ፅሕፈት ቤት እንዲሁም በቅዱስ ያሬድ የተሰየመ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለማስገንባት በከተማዋ መሰረት ድንጋይ በሊቃነ ጳጳሳቱ ተቀምጧል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ 

ታምራት ዲንሳ