1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ያቀረቡት ጥሪ

ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2016

የትግራይ ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች የህዝቡ ችግር ለመፍታት ከመጣር ይልቅ በውስጠ ፓርቲ ፍጥጫ ተጠምደዋል ሲሉ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቹ።በክልሉ ያለውን የከፋ ረሃብ መንግሥት ችላ ብሎታል የሚሉት ፓርቲዎቹ፥ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚመራው ህወሓት ደግሞ ለረሃቡ መፍትሔ ለማበጀት ከመሥራት ይልቅ ረዥም ግምገማ ላይ ነው ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4ZaPI
ፎቶ፤ ሳምሪ ከተማ ትግራይ ክልል
በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ እየነገረ ነው። ፎቶ፤ ሳምሪ ከተማ ትግራይ ክልል ምስል picture alliance / ZUMAPRESS.com

ሞት ያንዣበበበት የረሀብ አደጋ በትግራይ ክልል

ባለፈው ክረምት በትግራይ ክልል በቂ ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ በክልሉ ካሉ ሰባት ዞኖች በአምስቱ ድርቅ መከሰቱን የሚገልፀው የትግራይ አደጋ መከላከል ኮምሽን መረጃ፥ ይህ የተከሰተው ድርቅ አሁን ላይ ዜጎችን ወደሞት እየመራ ወዳለ ረሃብ እየተቀየረ መሆኑን ተነግሯል። ወጣቶች እንዲሁም በጎ ፍቃደኛ ግለሰቦች በተናጠል ከሚያደርጉት የተራቡ ወገኖችን ለመደገፍ ከሚደረግ ጥረት ውጭ፥ መንግሥት በትግራይ ክልል ተከስቶ ላለ ረሃብ አስፈላጊ ምላሽ እየሰጠ እንዳልሆነ በማንሳት በትግራይ የማገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወቅሳሉ። ለረሃቡ የትግራይ መሪዎች፣ ፖለቲከኛ፣ መፍትሔ ማበጀት ያልቻሉ ምሁራንን የተቹት የተቃዋሚዎች ፓለቲካ ፓርቲ ባይቶና መሪው አቶ ክብሮም በርኸ፥ በተለይም ሥልጣን የተቆጣጠሩት የህወሓት መሪዎች ወቅታዊውን የረሃብ ጉዳይ ለጎን በማለት በውስጠ ፓርቲ ስብሰባ እና ግምገማ ተጠምዷል በማለት ይወቅሳሉ።

የተቃዋሚዎች ትችት 

የባይቶናው መሪ አቶ ክብሮም «እየተራበ እና እየሞተ ያለ ህዝብ እርዳታ ለመስረቅ የማያፍሩ መሪዎች፣ የህዝባቸው ጉዳይ የማያሳስባቸው ፖለቲከኞች እና ምሁራን ባሉባት ትግራይጦርነትን ተጨምሮበት፥ ሁኔታው ምን ያክል እንደከፋ መረዳት አያስቸግርም» የሚሉ ሲሆን «መሪዎች በፌስቡክ ይሰሙ እንደሆነ እንጂ በውስጥ ግምገማ ተጠምደው ነው ያሉት። የትግራይ ህዝብ እየሞተ እነሱ ቤት ዘግተው እየተገማገሙ ነው። እነዚህን ይዘህ በረሃብ ላይ ሌላ ችግር መጨመር ካልሆነ የሚመጣ ለውጥ የለም። የህወሓት ግምገማ ለትግራይ ህዝብ ጉዳዩ አይደለም። ግምገማ ኋላቀር ኮምኒስታዊ ባህል ከመሆን አልፎ ፍርድ ቤት የሚተካ አይደለም» ሲሉም አክለዋል።

የህወሓት ግምገማ አልያም ስብሰባ 

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበላይነት የሚመራው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ እናየትግራይ ወታደራዊ አመራሮች እንዲሁም ነባር የፓርቲው መሪዎች ዝግ ሰብሰባ ከተቀመጡ ዛሬ 18 ቀናት ሆንዋቸዋል። ይህን ሰብሰባ ተከትሎ የአብዛኛው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራ ሐላፊዎች በሥራ ሰዓት በሥራ ገበታቸው የሉም። የትግራይ ፖለቲከኞች «የህወሓት ረዣዥም ግምገማና ስብሰባዎች የህዝብ አጀንዳ የሌላቸው፣ መፍትሔ ሲወልዱ የማይታዩ» በማለት ይገልጿቸዋል። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ (ውናት) ከፍተኛ አመራር ዶክተር ገብረመድህን ሮምሃ «የህወሓት ግምገማ እና ስብሰባ ካለፈው እንዳየነው፥ የትግራይ ህዝብ ችግር መፍቻ መንገድ ሳይሆን ቡድናዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የሚደረግ ፍልሚያ መሆኑ ግልፅ ሀቅ ነው። የትግራይ ህዝብ ጊዜ በማይሰጥ ችግር ላይ እያለ፣ ስደት ረሃብ ከፍቶ በሚገኝበት፥ እነሱ ግድ የላቸውም ለሁለት ሳምንት ስብሰባ ላይ ናቸው» ብለዋል።

ትግራይ ክልል መቀl ከተማ የሚገኘው የተፈናቃዮች መጠለያ
ትግራይ ክልል መቀl ከተማ የሚገኘው የተፈናቃዮች መጠለያ ምስል Million Haileselassie/DW

ረሀብ በትግራይ ክልል 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል ተፈጥሮ ያለውን ረሃብ ለመከላከል እና መፍትሔ ለማበጀት ገዢው ፓርቲ አልያም አስተዳደር ከመጠበቅ ይልቅ ሁሉንም አካላት ያካተተ አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ የተቃዋሚው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገቡ ናቸው። ዶክተር ደጀን «አንደኛ ህወሓትን መጠበቅ እናቁም ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የትግራይ ህዝብ የምግብ ዋስትና በሚያረጋግጥ መልኩ የሚሰራ፣ ተፈጥሮ ያለው ጊዜ የማይሰጥ ረሃብ ለመታገል የሚረዳ፣ ዓለም ዓቀፋዊ መልክ ያለው፣ ከመንግሥት ይሁን የፖለቲካ ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነ ኮምሽን ወይ ሌላ አይነት አደረጃጀት ይቋቋም። በዚሁ መሰረት ደግሞ ለተራበው ህዝባችን የሚውል እርዳታ ለማሰባሰብ ቴሌቶን እንዲካሄድ ነው ጥሪ የምናቀርበው» ይላሉ። የተቃዋሚዎቹን አስተያየት እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር እና ህወሓት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት «ሰብሰባ ላይ ናቸው» በሚል ምክንያት ለጊዜው አልተሳካም።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ