ኢትዮጵያዊ ባለሀብት በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ጋምቤላ ክልል ተገደሉ
በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በወርቅ ማዕድን ሥራ ለመሰማራት ከአዲስ አበባ ወደ ቦታው የሄዱ አንድ ባለሀብት ከሱዳን ተሻግረው መጡ በተባሉ የሙሩሌ ታጣቂዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ። በጠቅላላው የአራት ሰዎች ህይወት አልፏል። የዲማ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የወረዳው ውኃና ማዕድን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉት ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት ሰለሞን ጋሻው የተባሉ ባለሀብት በወርቅ ልማት ለመሰማራት በወረዳው የቦታ መረጣ ለማድረግ በመጡብት ወቅት እሳቸው እና ሌላ ግለሰብ ባለፈው ሐሙስ ከደቡብ ሱዳን ተሻግረው መጡ ባሏቸው የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች “ገዱ” በተባልች ቀበሌ ላይ ተገድለዋል። የመንግስት ታጣቂዎች በወሰዱት የአፀፋ እርምጃ ደግሞ ከታጣቂዎቹ 2ቱ መገደላቸውን ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል።« እነሱ በመኪና ውስጥ ሆነው ተተኩሶባቸው ህይወታቸው አልፏል። የኛ ሚሊሺያ፣ ፖሊሶች እና ፌደራል ፖሊሶች አንድ ላይ ተጋጭተው ሄደው እነሱ ጋር ደርሰው ከእነሱ ሁለት ታጣቂ የሞቱ አሉ። አንድ መሣሪያ ተገኘ። »
አቶ ኡጁሉ አክለው እንተናገሩትም ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላ ትናንት አርብ የአኮቦ ወንዝን ተሻግረው ወደመጡበት ተመልሰዋል። አሁን በአካባቢው ሠላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የተናገሩት ምክትል አስተዳዳሪው የሙርሌ ታጣቂዎች በየጊዜው ወደ ጋምቤላ ክልል በመሻገር ዝርፊያና ግድያ በተደጋጋሚ እንደሚፈጽሙም አመልክተዋል።
የCOP16 ጉባኤ ያለ አርኪ ውጤት ተጠናቀቀ
በሳዑዲ አረቢያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የነበረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ድርቅን ለመቋቋም ከሚያስችል ስምምነት ላይ ሳይደረስ መጠናቀቁን የጉባኤው ተሳታፊዎቹ ዛሬ አስታወቁ።
በረሀማነትን እና የድርቅን ተፅዕኖ መቅረፍ ላይ ያተኮረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ በምህፃሩ UNCCD ፤ COP16 በመባልም ይታወቃል፤ ለ 12 ቀናት በሪያድ ከተካሄደ በኋላ ዛሬ ማለዳ ከታቀደለት አንድ ቀን በኋላ ያለ ጋራ ስምምነት ተጠናቋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ አፍሪካዊ ልዑክ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደተናገሩት በጉባኤው ላይ ድርቅን በተመለከተ አስገዳጅ ከሆነ ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው የአፍሪካ ሀገራት ተስፋ አድርገው ነበር።
ሌሎች ሁለት የCOP16 ተሳታፊዎች ለኤ ኤፍፒ እንደተናገሩትም የበለጸጉ ሀገራት አስገዳጅ ፕሮቶኮል አልፈለጉም። ይህ ደግሞ ለአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች በቂ አልነበረም» ብለዋል። ድርጅቱ ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ግን በዘንድሮው ጉባኤ የወደፊት ድርቅን ተፅዕኖ በተመለከተ መሰረት በመጣል ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል። ሀገራቱም በ2026 በሞንጎሊያ በሚካሄደው COP17 እቅዶቹን ያጠናቅቃሉ የሚል እምነት አለው።
ጉባኤው በጀመረ ሁለተኛው ቀን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ዘገባ « በሰው ልጆች ጥፋት ምክንያት በሚፈጠር ድርቅ” ዓለማችንን በየዓመቱ ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያስከፍላል» ።
የጀርመኑ ፕሬዚዳንት የአራት ቀናት የአፍሪቃ ጉዟቸውን አጠናቀቁ
የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የአራት ቀናት ይፋዊ የአፍሪቃ ጉብኝታቸውን ዛሬ ደቡብ አፍሪቃዊቷን ሀገር ሌሶቱ በመጎብኘት አጠናቀቁ።
ሽታይንማየር ሌሶቱን የጎበኙ የመጀመሪያው የጀርመን ፕሬዝደንት ናቸው። ሽታይንማየር በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የምትገኘውን ትንሽዬ ተራራማ ሀገር የጎበኙት በንጉስ ሌትሲ III የቀረበላቸውን ግብዣ ተከትሎ ነው። ንጉስ ሌትሲ ባለፈው ዓመት በርሊንን ጎብኝተው ነበር። እጎአ በ1966 ዓም ሌሶቱ ከዩናይትድ ኪንግደም ነፃነቷን ከተጎናፀፈች አንስቶ የፖለቲካ አለመረጋጋት በተደጋጋሚ ተከስቶባታል። የሌሶቱ ኢኮኖሚ በዋናነት በግብርና እና ወደ ውጭ በምትልከው ጨርቃ ጨርቅ እና የአልማዝ ማዕድን ላይ የተመሠረተ ነው። የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር በዚህ ሳምንት ናይጄሪያን እና ደቡብ አፍሪቃንም ጎብኝተዋል።
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ፓርቲያቸው በዋና እጩነት መረጣቸው
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ እጎአ የካቲት 23 ቀን በሚካሄደው አዲስ ብሔራዊ ምርጫ የፓርቲያቸው ዋና እጩ ሆነው ተመረጡ። ዛሬ በፖትስዳም ከተማ በተካሄደው የሶሻል ዴሞክራቶች (SPD) ፓርቲ ጉባኤ ከ120 ተወካዮች መካከል 109ኙ ለሾልስ ድምጽ ሰጥተዋል። ስምንቱ ደግሞ ሳይደግፏቸው ቀርተዋል። በየካቲት ወር የሚካሄደው ምርጫን አስመልክቶ በተደረገ የዳሰሳ መጠይቅ በአሁኑ ሰዓት ሶሻል ዲሞክራቶች 17 በመቶ ብቻ በማግኘት በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የክርስቲያን ዴሞክራቶች እና ክርስቲያን ሶሻሊስት ኅብረት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ መጤ ጠል መሁኑ የሚነገርለት አማራጭ ለጀርመን (AFD) ፓርቲ ይገኛል። ኦላፍ ሾልስ ምንም እንኳን ዛሬ በፓርቲያቸው ዋና እጩ ሆነው ቢመረጡም እንደ የጀርመን መራኄ መንግሥትነታቸው በተወዳጅነት ደረጃ ብዙ ፈተና ገጥሟቸዋል።
ባለፈው ወር የጀርመን የሶስት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መንግሥት ከፈረሰ በኋላ በአፋጣኝ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አዲስ ሕጋዊ መንግሥት እንዲመሰረት ሲባል በጎርጎሮሲያኑ የካቲት 23 ቀን ብሔራዊ ምርጫ ይካሄዳል።
የድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን መርከብ ስራ ለማቆም ተገደደች
በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ስደተኞችን እና ተገን ጠያቂዎችን የምትታደገው እና “ጂኦ ባሬንትስ” የተሰኘችው የነፍስ አድን መርከብ ስራ ማቆሟን ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን አስታወቀ። ቡድኑ ዛሬ ከበርሊን እንዳስታወቀው የጣሊያን ሀገር ህግ በመርከቧ የነፍስ አድን ስራውን እንዳይቀጥል ፈተና ስለሆነበት ለማቆም ተገዷል።
የባህር ላይ ነፍስ አድን ሰራተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ማንኛውንም ስምሪት ካደረጉ በኋላ ወደ ወደብ የመቅዘፍ ግዴታ አለባቸው። ከዚህም በተጨማሪም ሰራተኞቹ አብዛኛውን ጊዜ ሩቅ ወደሆኑ ወደቦች እንደሚላኩ ድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን አስታውቋል። "ጂኦ ባረንትስ" በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ በጣሊያን ባለስልጣናት አራት ጊዜ ማዕቀብ ተጥሎባታል። በዚህም የተነሳ ወደብ ላይ ለ160 ቀናት መቆየት ነበረባት። የነፍስ አድን መርከቧ ሠራተኞች እ.ጎ.አ. ከሰኔ 2021 ዓም አንስቶ ባደረጉት 190 ተልዕኮዎች 12,675 ሰዎችን በባህር ላይ ከመስመጥ ታድገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ አንዲት የስደተኞች ጀልባ ሰጥሟ የ 5 ስደተኞች ህይወት ሲያል ፣ 40 ሰዎች እስካሁን አለመገኘታቸውን የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች አስታወቁ። 39 ሰዎች ደግሞ በህይወት የተረፉ መሆናቸው ተነግሯል። በግሪክ ክሬት ደሴት አቅራቢያ የሰመጠችው ጀልባ ላይ ስለነበሩት ስደተኞች ዜግነት ግን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ አልገለፀም።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ከስልጣን እንዲወርዱ የሀገሪቱ ምክር ቤት ወሰነ
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ከፕሬዚደንትነት ስልጣናቸው እንዲነሱ የሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ወሰነ። ከ300 የምክር ቤቱ የህዝብ ተወካዮች 204ቱ ፕሬዝዳንት ዩን ከስልጣን እንዲነሱ ድምጽ ሰጥተዋል። ዩን በበኩላቸው "ለተወሰነ ጊዜ ከስራቸው ገለል እንደሚሉ" ተናግሯል። የምክር ቤቱን ውጤት ተከትሎ በዋና ከተማዋ ሴኡል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደስታቸውን ለመግለፅ አደባባይ መውጣታቸውን የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘግቧል። የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ከስልጣን እንዲወርዱ የተገደዱት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጁት ወታደራዊ ህግ ምክንያት ነው። በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን ህግ ወዲያውኑ ምክር ቤቱ ውድቅ ያደረገ እና ፕሬዚዳንቱም ይቅርታ የጠየቁ ቢሆንም ስልጣን ከመልቀቅ አልዳኑም። የ63 ዓመቱ ዩን በደቡብ ኮሪያ ታሪክ በምክር ቤት የድምፅ ብልጫ ከስልጣን የተወገዱ ሶስተኛው ፕሬዝዳንት ናቸው።
ልደት አበበ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር