1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቃዮች አቤቱታና የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምላሽ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016

ከኦሮሚያ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከትግራይ ክልሎች ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ወገኖች የሚኖሩባቸው ድንኳኖች ከዕድሜ አኳያ በማርጀታቸው እየተቀዳዱና እየወደቁ በመሆኑ ለችግር እንደተጋለጡ ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/4k13O
በአማራ ክልል ቀበሮ ሜዳ የተፈናቃዮች መጠለያ ድንኳን
በአማራ ክልል ቀበሮ ሜዳ የተፈናቃዮች መጠለያ ድንኳን ፎቶ ከማኅደርምስል A. Mekonnen/DW

የተፈናቃዮች አቤቱታና የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምላሽ

 

ከኦሮሚያ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከትግራይ ክልሎች ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው ድንኳኖች ከዕድሜ አኳያ በማርጀታቸው እየተቀዳዱና እየወደቁ በመሆኑ ለችግር እንደተጋለጡ ተናገሩ። የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ደግሞ የተናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍተታ የሚያስችል ጥናት መጀመሩን እስታውቋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በነበሩ ብሔር ተኮር ግጭቶች ምክንያት ቀያቸውን ለቅቀውበአማራ ክልል የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ተፈናቃች መካከል አንዳንዶቹ የሚኖሩባቸው የመጠለያ ድንኳኖችና ሸራዎች በፀሐይና በዝናብ መፈራረቅ እየተጎዱና እየፈረሱ በመሆኑ በውስጣቸው ተጠልሎ ለመኖር በእጅጉ መቸገራቸውን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

የተፈናቃዮች አቤቱታ

ከተፈናቃዮቹ መካከል በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ አካባቢ በተለምዶ «ቱርክ» እየተባለ ከሚጠራው መጠለያ የሚኖሩ አንድ ተፈናቃይ የተሠራው የፕላስቲክ ድንኳን ከቆይታ አንፃር ንፋስና ዝናብ ሲመጣ መቋቋም አልቻለም፣ እንደ ጣራ ሆኖ የሚያገለግለው ሸራም በቀላሉ በነፋስ እንደሚወሰድና እንደሚቀደድ ተናግረዋል፡፡ «ብዙ ተፈናቃዮች ዝናብ ላይ ነው የሚተኙት»ም ይላሉ።

በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ የሚኖሩ ሌላ ተፈናቃይም ድንኳኖችና የፕላስቲክ ቤቶች ከማርጀታቸውም በላይ አሁን እየጣለ ባለው ዝናብና ነፋስ ሰበብም እየወደቁና በድንኳን ውስጥ ያሉ ቁሳቁሶች ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ገልጠዋል። ሕፃናትና አዛውንቶችም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውንም አክለዋል።

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ አቅራቢያ ቀበሮ ሜዳ በተባለ መጠለያ ስፍራ የሚገኙ አንድ ተፈናቃይ እንዳሉት፣ ድንኳኖች በየዓመቱ እድሳት ይደረግላቸው እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህ ዓመት ግን እድሳቱ ባለመደረጉ ድንኳኖቹ የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ነው ለዶቼ ቬሌ የገለጡት።

በአማራ ክልል የተፈናቃዩች መጠለያ
በአማራ ክልል የተፈናቃዩች መጠለያ ፎቶ ከማኅደር ምስል Alamata City Youth League

በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ በቻይናና ወይንሸት በተባሉ መጠለያዎች ከሚኖሩ ተፈናቃች መካከል አንዱ መጠለያዎቹ ለመኖር በማያስችል ሁኔታ በፀሐይና በዝናብ መጎዳታቸውን አመልክተዋል።

የመንግሥት ምላሽ

የአማራ ክልል አደጋመከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል የመጠለያ ድንኳኖች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ አሁን በመፍረስ ላይ ያሉትን በተመለከተ አስቸኳይ ጥገና እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የመደረግ ጥናት

የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቻው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር ጥናት መጀመሩን ጠቁመው ጥናቱ ሲጠናቀቅ ወደ ቀደመ ቀያቸው የሚሄዱት ወደዚያው ሄዳሉ፣ መሄድ የማይችሉት ደግሞ ራሳቸው ሠርተው የሚለወጡበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል። በአማራ ክልል ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ የዕለት እርዳታ ፋላጊዎች በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው አመልከተዋል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋየ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ