1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ምልክት በአፋር ክልል

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 25 2017

“ተመሳሳ ፍልውሃ ያለበት ፍንዳታ ወደ አራት አምስት ቦታ ታይተዋል” ያሉት የወረዳ አስተዳዳሪው ጭስና እሳት የሚተፋው ፍንዳታ አሁን ላይ እየተበራከተ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4onUd
Äthiopien Vulkanausbruch in der Region Afar
ምስል Seyoum Getu/DW

ነዋሪዎችን ያስጨነቀው የመሬት መንቀጥቀች

እሳትና ጭስ ያፈነዳው የ መሬት መንቀጥቀጥ  የአፋር 
ከተደጋጋሚ መሬት መንቀጥቀጥ በኋላ አፋር ክልል እሳት ከመሬት ውስጥ ሲፈላ ታይቷል፡፡
ከመሬት ውስጥ እሳትና ጭስ የሚተፋው እንፋሎቱ ዛሬ ማለዳውን 11 ሰዓት ግድም ከከባድ ፍንዳታ በኋላየተስተዋለ መሆኑን የአከባቢው ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
አለት የሚያፈናጥር እሳት ነው የተባለው እንፋሎቱ በክልሉ ጋቢረሱ (ዞን 03) ዱለቻ ወረዳ ሰጋንቶ ቀበሌ መከሰቱን የገለጹት የአከባቢው የአይን እማኞች ከዋናው ፍንዳታ በተጨማሪ በዙሪያው ተጨማሪ ፍንዳታዎች መታየት ቀጥሏል ባይ ናቸው፡፡
በአፋር ክልል ዞን ሶስት አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ በተባሉ ሁለት ወረዳዎች ተደጋግሞ በመከሰት በአከባቢው ነዋሪዎች ላይ ትልቅ ስጋት የደቀነው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆም ሲሰማ ነበር፡፡
በዱለቻ ወረዳ ድሩፉሊ ቀበሌ በቀሰም ስኳር ፋብሪካ ዙሪያ ቤቶችን ያፈራረሰው ርዕደመሬቱ ከትናንት አመሻሽ ጀምሮ በወረዳው ሰጋንቶ ቀበሌ ዶፋን ተራራ አቅራቢያ ላይ ጭስ መታየት ጀምሮ ማለዳውን ልነጋጋ 11 ሰዓት ግድም ላይ ደግሞ የተፈጠረውን ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ በአከባቢው መሰማቱን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ “ከመሬት ውስጥ እሳት እየወጣ ነው፡፡ ተደናግጠናል፡፡ ከእሩቅ ሆነን እንጂ የምንቀርጸው ስንቀርብ ያቃጥላል፡፡ 10 ቦታ ይሆናል እሳቱ የወጣበት፡፡ ዛሬም መሬት መንቀትቀጡ ቀጥሏል” ብለዋል፡፡

ማለዳውን የተሰማውን ከፍተኛ ፍንዳታ ተከትሎ እሳትና ጭስ ተቀላቅሎ ጠጠር ወደ ላይ እየተፋ ነው
ማለዳውን የተሰማውን ከፍተኛ ፍንዳታ ተከትሎ እሳትና ጭስ ተቀላቅሎ ጠጠር ወደ ላይ እየተፋ ነውምስል Seyoum Getu/DW


ማለዳ የተሰማው ከፍተኛ ፍንዳታ እና በጭስ ታጀበው እሳት 
ማለዳውን የተሰማውን ከፍተኛ ፍንዳታ ተከትሎ እሳትና ጭስ ተቀላቅሎ ጠጠር ወደ ላይ እየተፋ ነው የሚሉት የአፋር ገቢረሱ ዞን ዱለቻ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ደስታ፤ ቦታውም ከፈንታሌ ተራራ ጋር የሚያያዘው ዶፋን ተራራ አቅራቢያ ነው ብለዋል፡፡ “ተመሳሳ ፍልውሃ ያለበት ፍንዳታ ወደ አራት አምስት ቦታ ታይተዋል” ያሉት የወረዳ አስተዳዳሪው ጭስና እሳት የሚተፋው ፍንዳታ አሁን ላይ እየተበራከተ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከፍንዳው ውስጥ በርግጥም ምን እየወጣ እንደሆነ ቀርቦ ለማየት ስጋት መኖሩን ያነሱት አስተዳዳሪው በትንሽ ርቀት ላይ እንደሚታየው ግን ከመሬት ፍንታው ውስጥ እሳት ከጭስ ጋር ተቀላቅሎ ሲወጣ ይታያል ነው ያሉት፡፡ ከሚወጣው እሳት መሃል እንደ ድንጋይ ፍንጣሪ እየወጣ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ትናንት ሌሊቱን በተደጋጋሚ ከባባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ነበር ያሉት አቶ አሊ፤ አደጋው እስካሁን ሰዎችን ከማፈናቀል በዘለለ በሕይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱን ገልጸዋል፡፡ ዛሬ እሳት እየፈለቀበት ነው ከተባለው ሰጋንቶ ቀበሌ በቁጥር ባይገልጹትም ሁሉም ነዋሪ ተፈናቅለው ወደ መጠለያ እየገቡ ነው ብለዋልም፡፡ ከሰሞኑ በመሬት መንቀጥቀጡ ቤቶች የፈረሱበትና ውሃ ከፈለቀበት ድሩፉሊ ቀበሌም ሰዎች መፈናቀላቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

የመሬት መንቀጥቀጡ መንገዶችን ሰነጣጥቋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ መንገዶችን ሰነጣጥቋል።ምስል Seyoum Getu/DW


ዛሬ እሳትና ጭስ ከመሬት ውስጥ ሲንፎለፎል የዋለበት ሰጋንቶ ቀበሌ ዶፋን ተራራ ከአዋሽ አርባ ቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ቀሰም ስኳር ፋብሪካ 07 ኪ.ሜ. ብቻ ይርቃል፡፡ በአከባቢው ላይ በመሬት መንቀጥቀጡ አደጋ በደርስበት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ተብሎ የተሰጋው ቀሰም ግድብ እስካሁን ደህንነቱ የተጠበቀና ምንም ጉዳት አለማስተናገዱን የቀሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስከያጅ አቶ አሊ ሀሰን ከሰሞኑ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ የዱለቻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪው አቶ አሊ ደስታም ዛሬም ድረስ ግድሙ ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም ሲሉ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡ 
ዜጎችን ለመታደግ የተደረገ ዝግጅት
የወረዳ አስተዳዳሪው አሁን ላይ የተፈናቀሉትን የሁለት ቀበሌያት ነዋሪዎች ወደ አንድ ማዕከል በመውሰድ የሚረዱበት አግባብ ላይ እየተሰራ ነው ሲሉ አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡ “በተለይም ሁለት ቀበሌያት ላይ ያሉ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል” ያሉት አቶ አሊ ደስታ፤ የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራሮችም ከቀናት በፊት ቦታው ላይ ደርሰው ሁኔታውን በማየታቸው አከባቢው ባለስልጣናት ጋር በመሆኑ ተፈናቃዮች የሚረቡበት አግባብ ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ከሰሞኑ ኦሮሚያ ክልል ፋንታሌወረዳ እና በአፋር ክልል አዋሽ ፋንታሌና ዱለቻ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ አስር ቀበሌያት በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን የመሬት መንቀጥቀጥ በመመልከት፤ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ ጥንቃቄ አደረጃጀቶች በመፍጠር ሁለንተናዊ ዝግጅት መደረጉን በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ አጋርቷል፡፡
ሥየዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ