1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተወሳሰበው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት

ሐሙስ፣ መስከረም 5 2015

የአውሮጳ ህብረት ባወጣዉ መግለጫ ከሰው አልባ ድሮን ጥቃቱ በተጨማሪ፤ “የኤርትራ ሰራዊት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የሚያደርገው ተሳትፎ የሰላም ሂደቱን በጉልህ ያደናቅፋል” ብሏል፡፡ በአፍሪቃ ህብረት መርህ በሂደት ላይ ያለውን የሰላም ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥል እንዳረጋገጠላቸው የኢትዮጵያ ም/ጠ/ሚ እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4GvvX
Karte Äthiopien Region Tigray DE

የተወሳሰበው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት

በሰሜን ኢትዮጵያ ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ሊቆጠሩ የአንድ ወር እድሜ ብቻ የቀረው አውዳሚ ጦርነት በመሃል ለአምስት ወራት ያህል ጋብ ያለ መስሎ ቢቆይም ነሃሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ዳግም ለሶስተኛ ዙር በማገርሸት ጉዳት ማስከተሉን ቀጥሏል፡፡ በጦርነቱ የሚሳተፉ ተፋላሚ ኃይላትን ወደ ሰላማዊ ድርድር ለማምጣት ለወራት ሲደረግ የቆየው ጥረትም ፍሬ ባለማምጣቱ ተፋላሚ ኃይላቱ ለነሃሴ 18ቱ ዳግም ጦርነት መቀስቀስ አንደኛቸው ሌላኛውን ወገን ይከሳሉ፡፡

መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከትግራይ አመራሮች በኢትዮጵያውያን አዲሱ ዓመት ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር በሚካሄድ የሠላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑንና በዚህም የሚሳተፉ ተወካዮችን መሰየሙን ማስታወቁ የወቅቱ አነጋጋሪና በበርካቶችም የተሞካሸ ሃሳብ ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ስለዚህ የህወሓት ጥሪ ወጥቶ በይፋ የተናገረው እስካሁን አልተስተዋለም፡፡

የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለዛሬ ይዞት በቆየው ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ስለ መንግስት ወቅታዊ አቋምና በህወሓት ስለቀረበው የጦርነት ማቆም ጥሪ መንግስት አቋሙን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም የጋዜጣዊ መግለጫው ፕሮግራም በመጨረሻም ተሰርዟል፡፡ ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረገው ጥረትም እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡

በርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት በከዚህ ቀደም አቋሙ ጦርነቱን በአፍሪካ ህበረት ጥላ ስር ብቻ በሚከወን የሰላም ድርድር ለመቋጨት ዝግጁ መሆኑን ከወቅታዊው ጦርነት ማገርሸት አስቀድሞ በተደጋጋሚ ሲያነሳው ቆይቷል፡፡

ምንም እንኳን ስለአሁኑ የህወሓት ጥሪ መንግስት ምላሽ ባይሰጥም፤ የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረገው ድርድር አመቺ ሁኔታን ለመፍጠርም አስቸኳይና በጋራ ስምምነት ግጭቶችን ለማቆም እንደሚስማሙና ይህንንም ተከትሎ በሚካሄድ ድርድር ተደራዳሪዎችን ሰይመው ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን በእሁዱ መግለጫቸው አትተዋል።

በትናንትናው እለት መስከረም 04 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በአውሮጳ ህብረት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት የአፍሪቃ ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂሃን ጋር በጽ/ቤታቸው የተወያዩት የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስታቸው በአፍሪቃ ህብረት መርህ በሂደት ላይ ያለውን የሰላም ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥል እንዳረጋገጡላቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ስለኢትዮጵያው አሁናዊ ግጭት ለዳይሬክተሯ ያብራሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የአውሮጳ ህብረት አስፈላጊ በሆነ ሰዓት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ድጋፍ እንደሚያደርግ” ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በአውሮጳ ህብረት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት የአፍሪቃ ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂንሃም የአውሮጳ ህብረት የአፍሪቃ ህብረት የሰላም ሂደቱ ጥረትን አስፈላጊ በሆነ ሁሉ እንደሚደግፍ ማረጋገጫ ሰጥተው የኢትዮጵያን አጋርነት ማጠናከር እንደሚፈልጉም አመልክተዋል፡፡

የትግራይ ኃይሎች እሁድ መስከረም 01 የግጭት ማቆምና የሰላም ድርድር ጥሪን ካቀረቡ በኋላ በፌዴራል መንግስት በኩል የተንጸባረቀው ይህ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መንግስት አሁንም ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይሁንና በትግራይ ኃይሎች በኩል ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ትናንት ረቡዕም ቀጥሎ በትግራይ ክልል መዲና መቐለ የ10 ሰዎች ህይወት ስለመቅጠፉ በስፋት ስለተዘገበው የሰውአልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት እስካሁንም በፌዴራል መንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡ በምዕራብ ሰሜን የአማራ ክልል አከባቢዎች ላይ አዲስ የተስፋፋ ጦርነት ስለመኖሩ ግን እየተነገረ ነው፡፡

የአውሮጳ ህብረት ትናንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ እንዳስጠነቀቀው “በመቐለ ከተማ እየተካሄደ ያለው የድሮን ጥቃት ተስፋ የተጣለበት፤ ነገር ግን የተሸራረፈውን የሰላም ሂደት የባሰ እንዳያጨልመው እሰጋለሁ” ብሏል፡፡

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በቲዊተር ባሰራጩት ጽሁፍ ትናንት በመቀሌ በሰው አልባ ድሮን የተፈጸመ የአየር ጥቃት “በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ነው” ብለዋል፡፡

የአውሮጳ ህብረት በትናንት ማምሻው መግለጫ ከሰው አልባ ድሮን ጥቃቱ በተጨማሪ፤ “የኤርትራ ሰራዊት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የሚያደርገው ተሳትፎ የሰላም ሂደቱን በጉልህ ያደናቅፋል” ብሏል፡፡  

“የተፋላሚ ኃይሎቹ ፍላጎት ጦርነቱን በሰላማዊ አማራጭ መቋጨት ነው” ያለው የአውሮጳ ህብረት መግለጫ ይህ ገቢራዊ አለመሆኑ አሳዛኝ ነው ብሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ በፊትም በጦርነት የተጎዳችን አገር ወደ ባሰ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳያመራት ስጋቱን አስቀምጧል፡፡

ያለው አማራጭ “ሰላማዊ ውይይት ማድረግ ብቻ ነው” ያለው ህበረቱ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ሰላም ይዞ እንዲመጣ ጥሪ በማቅረብ፤ በአፍሪካ ህበረት በኩል የተጀመረውን የሰላም ጥረት እንደሚደግፍም አሳውቋል፡፡

የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰራዊት በተቀናጀ መልኩ ጦርነት ከፍተውባቸው ሽራሮ እና ባድመ የተባሉ የሰሜን ትግራይ አከባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ አንስተዋል፡፡

የህወሓት ጦር አዛዡ ማክሰኞ መስከረም 03 ቀን 2015 ዓ.ም. ለክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ በአፍሪቃ ህብረቱ የሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ በሆኑበት ባሁን ወቅት ጦርነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ያነሱት፡፡

የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ያስተላለፉት የግጭት ማቆምና የሰላም ጥሪ በአፍሪቃ ህብረት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በአውሮጳ ህብረት፣ በጀርመንና በአሜሪካ መንግስታት እንዲሁም በሌሎች ዓለማቀፍ ማህበረሰብ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡

ስዩም ጌቱ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ኂሩት መለሰ