1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተተኳሽ ቁሶች አደጋ በትግራይ ክልል

ዓርብ፣ ሚያዝያ 13 2015

የተሃድሶና ልማት ድርጅት ወይም ራዶ የተባለ ግብረሰናይ ተቋም በትግራይ 13 ወረዳዎች ጥናት አድርጎ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ግኝት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተጣሉ አልያም በተዘነጉ ተተኳሽ ቁሶች በደረሰ ጉዳት በአጠቃላይ 580 ሰላማውያን ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ከእነዚህ መካከል 116ቱ ሞተዋል።

https://p.dw.com/p/4QJZz
Äthiopien Mekelle Hinweis explosive Überreste des Krieges in Tigray
ምስል Million Haileselasie/DW

በተተኳሽ ቁሶች አደጋ 116 ሰዎች ሞተዋል

ትግራይ ዉስጥ በጦርነቱ ወቅት የተቀብሩ ወይም  ተጥለው የነበሩ ቦምቦች እየፈነዱ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደል ማቆሰላቸዉን አንድ በጎ አድርጊ ድርጅት አስታወቀ።የተሃድሶና ልማት የተሰኘዉ ድርጅት እንደሚለዉ ትግራይ ከሚገኙ ከ80 በላይ ወረዳዎች በ13ቱ ብቻ ባደረገው ጥናት እንዳስታወቀዉ 116 ሰዎች በተተኳሽ ቁሶች አደጋ ሞተዋል፤ ሌሎች ከ460 የሚበልጡ ቆስለዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል 67 በመቶዎቹ ህፃናት ናቸዉ።
የ12 ዓመት ህፃን ፍርቱና መብራህቱ ያገኘናት በዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የፅኑ ሕሙማን እንክብካቤ ክፍል ውስጥ ሕክምና እየተከታተለች ነው። ከፍርቱና ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው በከባድ ፍንዳታ እጅዋ፣ እግርዋ እንዲሁም ሆድዋ ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን የግራ እጅ ጣቶችዎም እንዲሁ አጥታለች። ህፃንዋ ፍርቱና ለዚህ የተዳረገችው፤ እንደሁልጊዜው ከትላንት በስትያ ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን፣ የአባትዋ ከብቶች ይዛ ከቤት በመውጣት ውሃ እያጠጣቻቸው በነበረ ሰዓት፣ መንገድ ላይ ተጥሎ የነበረ ፈንጂ ድንገት ተነክቶ በደረሰ ፍንዳታ መሆኑ ከቤተሰቦችዎ ሰምተናል። በትግራዩ ጦርነት ወቅት ለበርካታ ወራት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦሮች መቀመጫ ሆኖ እንደቆየ በሚነገርለት ሓውዜን ወረዳ የሚገኘው ገርዓልታ ሎጅ አካባቢ የሚኖሩት ህፃንዋ ፍርቱናና ቤተሰቦችዋ፤ ከዚህ በፊት በአካባቢው ጥይቶች ጨምሮ የተለያዩ የወዳደቁ ተተኳሾች ያዩ እንደነበረ ቢገልፁም፣ ባለፈው ሰኞ ማምሻ በህፃን ልጃቸው ላይ የደረሰ አደጋ ግን ያልጠበቁት እንደነበር የፍርቱና አባት ቄስ መብራህቱ ወልደንጉስ ይናገራሉ። ቄስ መብራህቱ በልጃቸው ፍርቱና ላይ አደጋ ሲደርስ የነበረው ሁኔታ ሲያስታውሱ "እኛ ቤት ውስጥ ነበርን። ከብቶች እየጠበቀች ነበረች። ከዛ ከባድ ፍንዳታ ሰማን፥ እየሮጥን ስንሄድ እጅዋ እግርዋ እና ሆድዋ ላይ ተመትታ ቆየችን" ይላሉ። የሚኖሩበት ገርዓልታ ሎጅ አካባቢ ለረዥም ግዜ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሐይሎች 'ካምፕ' ሆኖ መቆየቱ የሚገልፁት ቄስ መብራህቱ "በተለያየ ግዜ ጥይት ይገኛል። ፍተርቱና ደግሞ ህፃን ናት። ያገኘችው ቁራጭ ብረት አነሳች። ተጎዳች" ብለዋል። 

Äthiopien Mekelle Hinweis explosive Überreste des Krieges in Tigray
ምስል Million Haileselasie/DW

ህፃንዋ ፍርቱና በፍንዳታው የደረሰባት ጉዳት ከባድ መሆኑ ተከትሎ ወድያውኑ ነበረ ወደ መቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል 'በሪፈር' የተላከችው። በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በተቀበሩ አልያም ተጥለው በነበሩ ፀረ-ሰው፣ ፀረ-ታንክ ፈንጂዎች፣ ያልመከኑ ተተኳሾችን፣ ፊዩዞች እንደ ህፃን ፍርቱና ከባድ የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው ወይም እስከወዲያኛው የሚያልፉ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ ስለመሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። የተሃድሶና ልማት ድርጅት ወይም ራዶ የተባለ ግብረሰናይ ተቋም በትግራይ 13 ወረዳዎች ጥናት አድርጎ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ግኝት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተጣሉ አልያም በተዘነጉ ተተኳሽ ቁሶች በደረሰ ጉዳት በአጠቃላይ 580 ሰላማውያን ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ከእነዚህ መካከል 116ቱ ሞተዋል። ከእነዚህ በተጣሉ ፈንጂ ቁሶች ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 67 በመቶዎቹ ህፃናት መሆናቸው የራዶ ግኝት ያመለክታል። አጥኚዎቹ እንደሚሉት በትግራይ ካሉ 80 ወረዳዎች ጥናቱ የሸፈነው 13 ብቻ በመሆኑ ጥናቱ ሲሰፋ የጉዳቱ መጠን በዛው ልክ የሰፋ እንደሚሆን ይገልፃሉ። የተሃድሶ እና ልማት ድርጅት የትግራይ ክልል አስተባባሪ አቶ ተስፋይ ገብረማርያም "ከበርካታ ችግሮች መካከል አንድ ግንዛቤ ማነስ" መሆኑ የገለፀ ሲሆን በዚህ ምክንያት በርካቶች ለጉዳት መጋለጣቸው ለዶቼቬለ አስረድተዋል። በቅርቡ ጉዳት የደረሰባት የህፃን ፍርቱና ወላጅ አባት ቄስ መብራህቱ በአካባቢያቸው ጨምሮ በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች ከተተኳሾች የማፅዳት ስራ እንዲከወን ጥሪ ያቀርባሉ። በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ከትግራይ ክልል አስተዳደር በኩል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ