1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተሻሻለዉ የኤክሳይዝ ታክስ ግሽበትን ያባብሳል ተባለ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2012

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ተሻሽሎ በቀረበ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ዉይይት አድርጓል።ለዝርዝር ዕይታም ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ረቂቅ አዋጁ «የቅንጦት» በሚባሉና  የማህብረሰቡን ጤና ሊጎዱ እና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ በተባሉ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ እንዲጣል ይደነግጋል።

https://p.dw.com/p/3VAIn
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle



ባለሙያዎች እንደሚሉት የኤክሳይስ ታክስ ዓላማዉ ለማህበረሰቡ ጉዳት ባላቸዉ ምርቶች ላይ ከፍ ያለ ቀረጥ በመጣል የመግዛት ፍላጎት መቀነስ ሲሆን፤በአንፃሩ ደግሞ ለማህበረሰቡ ጤናና የማህበራዊ ኑሮ ጠቀሜታ ባላቸዉ ምርቶች ላይ የሚጣለዉን ቀረጥ መቀነስ ነዉ። በዚህም መሰረት  የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በተወያየበት ረቂቅ አዋጅ የቅንጦት በሚባሉና በማህብረሰቡ ጤና ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ ባላቸዉ የተመረጡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታክስ ጥሏል።
አዋጁ ከለያቸው የምርት አይነቶች መካከል ምግብና መጠጦች፣የመዋቢያ ምርቶች፣ተሽከርካሮዎች ፣አንዳንድ ኤለክትሮኒክ መሳሪያዎች ፣ሲጋራና የአልኮል መጠጦች  ይገኙበታል።አዋጁ ቀረጥ እንዲጨመርባቸዉ ከደነገገባቸዉ የምግብና የመጠጥ አይነቶች ዝርዝር ዉስጥ ደግሞ ዱቄት፣የምግብ ዘይት ፣ጨዉና የታሸጉ ውሃዎች ተካተዋል።
በተለይ የምግብ ዘይት ላይ የቀረጥ ጭማሪው መሠረት ያደረገው  በውስጡ በያዘው ለጤና ጎጅ የሆነ ከፍተኛ የስብ መጠንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። 
ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸዉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ጌታቸዉ ተ/ማርያም እንደሚሉት ከዚህ አኳያ በረቂቅ አዋጁ የቀረበዉ የቀረጥ አጣጣል በአብዛኛዉ ተገቢ ቢሆንም በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተጣለዉ ግን የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅምና የሀገሪቱን የገበያ ሁኔታ  ያላገናዘበ ነዉ።
ከዚህ በተጨማሪም  በሀገር ዉስጥ የማምረት አቅም ባልዳበረበት ሁኔታ ጥራት ያላቸዉን ምርቶች ለማበረታታት ተብሎ የሚጣለዉ ከፍተኛ ቀረጥ በሀገሪቱ በየጊዜዉ እየጨመረ የመጣዉን የዋጋ ዉድነትንና  እጥረት ሊያባብስ እንደሚችልም ባለሙያዉ አስረድተዋል።

ይህ መሰሉ የቀረጥ አጣጣል  አዲስ በሚፈጠረዉ ፍላጎትና  በሚፈለጉት ምርቶች አቅርቦት መካከልም ክፍተት የሚፈጥር መሆኑን  ባለሙያዉ  ጨምረዉ ገልፀዋል።
ሌላዉ በረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ቀረጥ የተጣለባቸዉ ምርቶች ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ፣የእርሻ ትራክተሮችና  የሚዲያ መገልገያ መሣሪያዎች ናቸዉ። የምጣኔ ሀብት ባለሚያዉ አቶ ጌታቸዉ እንደሚሉት በነዚህ ምርቶች  ላይ የጣለው የተጋነነ ቀረጥም የኅብረተሰቡን የመግዛት ዓቅም በመገደብ በእነዚህ ዘርፎች የሚደረገዉን የልማት ዕንቅስቃሴ ሊገታ ይችላል።
ስለሆነም ለምርት ጥራት የተሰጠዉ ትኩረት እንዳለ ሆኖ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም፣በምርቶች መካከል ያለዉን የዋጋ ግንኙነት ፣በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ ሊፈጠር የሚችለዉን  ክፍተት እንዲሁም የሚጣለዉ ቀረጥ በገበያ ዉስጥ የሚያመጣዉ ተፅዕኖ በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባዉ ባለሙያዉ አሳስበዋል።

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle
Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

 

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ