1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ 'ሰላም አስከባሪዎች ቀን'

ቅዳሜ፣ ግንቦት 24 2016

ዓለም አቀፉ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ቀን ለሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ ከ4,000 የሚበልጡ የሰላም አስከባሪዎ ጓዶችን አስቦ ዉሏል። የተባበሩት መንግሥት የሰላም አስከባሪ ጓዶች ላለፉት 75 ዓመታት በአፍሪቃ፣ በእስያ፣ በአውሮጳና በመካከለኛው ምሥራቅ በግጭት በተጠቁ አካባቢዎች ሠላምን በማስከበር ሲያገለግሉ ዘልቀዋል።

https://p.dw.com/p/4gWJ5
 የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎች በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ
የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎች በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክምስል Moses Sawasawa/AP Photo/picture alliance

የተመድ 'ሰላም አስከባሪዎች ቀን'

የተመድ 'ሰላም አስከባሪዎች ቀን' የጠፋውን ህይወት አስቦ ዉሏል

ዓለም አቀፉ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ቀን ለሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ ከ4,000 የሚበልጡ የሰላም አስከባሪዎ ጓዶችን አስቦ ዉሏል። ሰማያዊ ቆብ ያደረጉ በመባል የሚታወቁት የተባበሩት መንግሥት የሰላም አስከባሪ ጓዶች ላለፉት 75 ዓመታት በአፍሪቃ፣ በእስያ፣ በአውሮጳና በመካከለኛው ምሥራቅ በግጭት በተጠቁ አካባቢዎች ሠላምን በማስከበር ሲያገለግሉ ዘልቀዋል።

 የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎች  በማሊ
የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎች በማሊምስል SIA KAMBOU/AFP

ሰማያዊ ቆብ አጥላቂዎች የመንግሥታቱ ሰላም አስከባሪዎች በተበታተኑ አገሮች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ይረዳሉ። ይሁን እንጂ ጥብቅ በሆኑ መመሪያዎች ስለሚንቀሳቀሱ ብዙውን ጊዜ በቀላሉ ከባድ ግጭቶች ላይ ሁኔታዎችን ማረጋጋት ብሎም ሰላማዊ ሰዎችን ከአደጋ መጠበቅ አይችሉም። በዚህ ሳምንት ረቡዕ ግንቦት 20 የተከበረዉ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎች መታሰቢያ ዕለት "ለወደፊት ስምምነት፤ በአብሮነትን መገንባት" የሚል መርህን የያዘ ነበር።

ለተሰዉ ወታደሮች ክብር  

በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ (UNMISS) ኃላፊ ኒኮላስ ሃይሰም በተልዕኮ የሞቱ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በማስታወስ ዕለቱን እንዳሰቡ ተናግረዋል።

"የሚያሳዝነው አንዳንድ የሥራ ባልደረቦቻችን በተልዕኮ ላይ የመጨረሻውን ዋጋ ከፍለዋል። ዉርሳቸዉ ሕያው እና የሚያነቃቃ ነዉ። የሰዎችን ሕይወት የማዳን ወሳኝ ሚና ይዘናል፤ ይሁን እና በየአካባቢው አቅምን መገንባትና ዘላቂ የሆኑ መፍትሔዎችን መፈለግ ደግሞ አስፈላጊ ነዉ።"

ከሱዳን ተገንጥላ እንደ አገር ከተመሰረተች በቅርቡ 13 ዓመት የሚሞላት ደቡብ ሱዳን ሰማያዊ ቆብ አጥላቂ ወታደሮች፣ የፖሊስ መኮንኖችና ሲቪል ሰራተኞች እንዲሁም ፈቃደኛ ሰራተኞችን ጨምሮ  14,200 የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ጓዶች የሚገኙባት ሃገር ናት። በዚህም በደቡብ ሱዳን ከፍተኛዉ ቁጥር የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች የሚገኙባት አፍሪቃዊት ሃገር ያደርጋታል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን የሚገኘዉ የሰላም አስከባሪ ጓድ እስከ ጎርጎረሳዉያኑ ሚያዝያ 30 ቀን 2025 ዓ.ም ድረስ ተልዕኮዉ እንዲቀጥል አራዝሟል። የሰላም አስከባሪ ጓዱ በቀጣይ የሚገጥሙትን የፖለቲካ፣ ደህንነትና ሰብአዊ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የኃይል ደረጃውን ጠብቆ እንደሚቀጥል ተነግሯል። 

በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ ኃላፊ ኒኮላስ ሃይሰም እንደተናገሩት፤ በሱዳን ሰላም አስከባሪ ጓዱ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ይሠራል።

"በሱዳን ሰላም አስከባሪ ጓዱ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ይሠራል፣ ይሁና አስተማማኝና ዘላቂ የሚሆነዉ ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ማግኘት ነዉ። ሰላም አስከባሪዎች፤ የቡድን ወገንተኞች ግጭቶችን ለማሸነፍ የሚጫወቱትን ፖለቲካዊ ሚና በፍጹም ሊተኩ አይችሉም"

UN Peacekeepers | Sri Lankas Armeechef General Shavendra Silva
ምስል AFP

«የደቡብ ሱዳናዉያንን ሴቶችና ወንዶች ከባድ ትግል አይተናል። በተለይ በገጠር መንደሮች። ችግሩን ለማቃለል የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጓድ እና የመንግሥታቱ ድርጅት ተባባሪዎች፤ ችግሩን ለማቃለል የተጫወቱትን ጉልህ ሚና አይተናል ሲሉ ኒኮላስ ሃይሰም አክለዋል።

በዚህ ዓመት የመታሰቢያ ሥነ ስርዓት ላይ  "የደንብ ልብስ በለበሱ ሲቪል ሠራተኞች" ስራቸውን በማጉላት እንደተከበረም ተነግሯል።  

“አብሮነትን መገንባት”

የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ በተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ የናይጀሪያ ወታደራዊ ታዛቢ ኦፊሰር ሀዎንጊ ሩዋንግ በመስኩ ላይ ያላቸዉን ወሳኝ ሚና  ጠቁመዋል።

"እኛ  የተልዕኮ ዓይኖች ነን።  ምክንያቱም ወደ ለጥበቃ ወደ ሜዳ እንወጣለን። እንቃኛለን። እንከታተላለን። በዚያ የሚደረገዉን ማንኛውንም ነገር እናያለን ። የኃይሉ አዛዥ ይህን አያዩም። ስለዚህ እኛ ለኃይሉ ዓይኖች ነን።"

የሩዋንግ ዋና ሥራ ከግጭት በኋላ የተደረሱ ስምምነቶችን መከታተልና መገምገም ነው። በወገኖች መካከል የሚደረገው ውጊያ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆም፣ በተለይም የሰላም ውይይቶችን በማቀላጠፍ  ስራ መስክም  ያገለግላሉ።   

ከሩዋንዳ የመጡት እና በደቡብ ሱዳን የተልዕኮዉ ባልደረባ የሆኑት ጀነራል አፖይኔሮ ካንያንዳ በወታደራዊ ስራዎች የሥራ ስልቶችን እና ዕቅዶችን ያዘጋጃሉ፤ መሣሪያዎችን፣ ሠራተኞችን እና ንብረቶችንም ያከፋፍላሉ።

"ደስተኛ የሚያደርገኝ እኔና አገሬ በዚህች አገር ሰላም እንዲመጣ እና ሕዝቡ የተረጋጋ ሆኖ በማየት ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከቴ ነው"  ሲሉም ተናግረዋል።   

ካንያንዳ በጎርጎረሳዉያኑ 1994 ዓ.ም  ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች በሩዋንዳ በተቀናጀ መንገድ የተገደሉበትን ሁኔታ በማስታወስ ተመሳሳይ የጅምላ ግድያ እንዳይፈፀም በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ቢሰፍን በጣም ደስተኛ እንደሚሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከባንግላዴሽ የመጡ የተመ ሰላም አስከባሪዎች በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ
ከባንግላዴሽ የመጡ የተመ ሰላም አስከባሪዎች በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክምስል AFP via Getty Images

በአንዳንድ የአፍሪቃ አገሮች ጥሩ ስም የለዉም

የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ጓዶች በሚያገለግሉባቸው አገሮች ሰላም ለማስፈን የሚጥሩ ቢሆንም በአፍሪቃ ከሚገኙ አንዳንድ አስተዳደሮች ጋር ግጭት ዉስጥ የገቡበት ጊዜም አለ።

እንደ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ (DRC)፣ ማሊ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ (CAR) ብሎም በደቡብ ሱዳን ባሉ አገሮች የተመድ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ብዙም ስኬት አላጋጠማቸውም።

ጀምስ ሺማኑላ / አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ