1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብዙ ሴቶችን ሕይወት ያጨለመው ጾታዊ ጥቃት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 11 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ወራት ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሴቶች ላይ የተፈጸመው ጾታዊ ጥቃት በሰለባዎቹ ላይ ብቻ ያበቃል ተብሎ እንደማይታሰብ ችግሩን በቅርበት ያስተዋሉ እየገለጹ ነው።

https://p.dw.com/p/4A78p

ጤና እና አካባቢ

Äthiopien I Konflikt in Tigray
ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture allianc

ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን እጅግ በርካታ ሴቶች በቅርበት እየረዱ የሚገኙት ለሴቶች መብት የሚሟገቱት የሕግ ባለሙያ ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር ለወራት በስፍራው ተገኝተው የተመለከቱትን ባለፈው ሳምንት አጋርተውናል። ሲስተር መዲና ወርቅነህ የደሴ አጠቃላይ ሆስፒታል የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጠው ዋን ስቶፕ ሴንተር አስተባባሪ ናቸው። ወደ እዚህ ማዕከል በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የጥቃት ሰለባ ሴቶች ይመጣሉ። እነዚህ ወገኖች ተገቢውን የህክምናም ሆነ ሌሎች በተቀናጀው አገልግሎት ዘርፍ አስፈላጊውን ርዳታ እንዲያገኙ ሲስተር መዲና ከባልደረቦቻቸው ጋር ከንጋት እስከ ምሽት ይሠራሉ። እኔ ለዚሁ ጉዳይ ከሥራ ሰዓት ውጪ ስደውልላቸው የተለያየ ርዳታ ሲያገኙ የዋሉትን እህቶች እና እናቶች የሴቶች መብት ተሟጋቿ የሕግ ባለሙያ ማሪያ ሙኒር ያቋቋሙት ለጥቃት ሰለባ ሴቶች መጠጊያ ወደሆነው የደሴው «የሴቶች ማረፊያ» እየወሰዱ ነበር። ወይዘሮ ማሪያ እንደገለጹልን ደሴ እና ወልደያ በሚገኙት በእነዚህ ማረፊያ ቤቶች እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ ሴቶች ይገኛሉ። በጦርነት አካባቢዎችም ባይሆን ግን የጥቃት ሰለባለሆኑት ሴቶች ማረፊያነት የተዘጋጁት ቤቶች ከአቅማቸው በላይ ተገልጋዮች እንዳሏቸው ነው ወይዘሮ ማሪያ የሚናገሩት።

ጦርነት በተካሄደባቸው የአማራ ክልል ከተሞች እና መንደሮች ተገድደው የተደፈሩ እናቶች እና እህቶች ከየጓዳው ወጥተው ተገቢውን የአካልም ሆነ የስነልቡና ህክምና ርዳታ እንዳያገኙ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚኖረው የመገለል ዕዳ ሌላው ስጋት እንደሆነ ነው የሚነገረው። ሲስተር መዲና እንደሚሉት ለህክምና ወደ እነሱ የመጡት ደግሞ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋልጠዋል። እነዚህ ወገኖች ሲስተር መዲና ወደሚያስተባብሩት ዋን ስቶፕ ሴንተር ሲሄዱ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ያገኛሉ። ሲስተር መዲና እንደገለጹልን በአሁኑ ወቅት ወደ እነሱ ለህክምና መጥቶ ርዳታ ሳያገኝ የሚሄድ የለም፤ ቀጣይነቱ እስከምን ድረስ ነው የሚለው ግን ያሳስባቸዋል። ከምንም በላይ የጤና ጉዳይ።

እነዚህ የጥቃት ሰለባዎች ተገቢውን የአካልም ሆነ የስነልቡና ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረጉ ጥረት እንዳለ ሆኖ በፍትህ በኩል የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተጠያቂ የማድረጉ ሥራን አስመልክተው የሕግ ባለሞያው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ በእነሱ በኩል ክትትል እየተደረገ ነው ይላሉ። ይኽን በሚመለከት ከሚሠራው የመንግሥት ተቋምም ጋር በቅርበት ጉዳዩን በማንሳት እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል። በሌላ በኩል የጥቃት ሰለባዎቹ ከሚያስፈልጋቸው የህክምና ርዳታ ጎን ለጎን ኑሯቸው ወደነበረበት እንዲመለስ የሚደረግ ድጋፍ ሌላው ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ ነው ተጎጂዎቹን በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች የሚናገሩት። እስካሁን ከ40 ለማይበልጡት የሚቻለው ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በዚህ በኩል ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ወይዘሮ ማሪያ ነግረውናል። ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡት ወገኖች አስፈላጊውን አካላዊም ሆነ ስለልቡናዊ ህክምና እንዲያገኙ የሚደረገውን ጥረት በምትችሉት እንድትደግፉ ያስተላለፉትን ጥሪ በማቅረብ በተከታታይ ያቀረብነውን ዝግጅት አበቃን።

 ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ