1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባሕርዳር ከተማ የፀጥታ ሁኔታ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2015

አማር ክልል ባህር ዳር ከተማ አንዳንድ የንግድ ተቋማት ዛሬም እንደተዘጉ ናቸው ። ትናንት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ አንዳንድ የንግድ መደብሮች በተለይ ደግሞ የግል ባንኮች ዝግ ሆነው አርፍደው እንደነበር ተዘግቧል ። በከተማዪቱ ሥጋት ነበረም ተብሏል ። ዛሬ ያልተከፈቱ መደብሮች መታሸጋቸውን የክልልሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4QXo0
Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አንዳንድ የንግድ ተቋማት ዛሬም እንደተዘጉ ናቸው

አማር ክልል ባህር ዳር ከተማ አንዳንድ የንግድ ተቋማት ዛሬም እንደተዘጉ ናቸው ። ትናንት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ አንዳንድ የንግድ መደብሮች በተለይ ደግሞ የግል ባንኮች ዝግ ሆነው አርፍደው እንደነበር ተዘግቧል ።  በከተማዪቱ ሥጋት ነበረም ተብሏል ። ዛሬ ያልተከፈቱ መደብሮች መታሸጋቸውን የክልልሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል ።  በደብረብርሀን ከተማ የታመቀ ቅሬታ እንዳለ አንድ ነዋሪ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ከትንሳኤ በዓል በፊት በነበሩ ጥቂት ቀናት በባህርዳርና በሌሎችም የአማራ ክልል ከተሞች ከአዲሱ የልዩ ኃይል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ አለመረጋጋቶች እንደነበሩ ይታወሳል ።

ትናንት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ አንዳንድ የንግድ መደብሮች በተለይ ደግሞ የግል ባንኮች ዝግ ሆነው አርፍደዋል ።  ከሰዓት በኋላ ደግሞ አብዛኞቹ ባንኮቹ አገልግሎት ሲሰጡ የባሕር ዳር ወኪላችን መመልከቱን ዘግቧል ። ዛሬ ደግሞ አብዛኛዎቹ ንግድ ቤቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዐስታወቋል ። አንዳንድ የንግድ ተቋማት አሁንም እንደተዘጉ ናቸው ። ይሁን አንጂ በተለምዶ አዴት ተራ ወይም የኮንስትራክሽን መሳጫ መደብሮች አገልግሎት ባለመስጠታቸው በመንግስት ታሽገው ተመልክተናል ።

የአንድ ባንክ ስራ አስኪያጅ ትናንት ክፍለ ምንም እንኳ ሥጋት የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎችን አስተናግደናል፣ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ሙሉ አገልግሎት ሰጥተናል ብለዋል ። በተማዋ በተለይ ትናንት በጠዋት የትራፊክ ፍሰቱ ሙሉ የነበረ ሲሆን ከሰዓት በኋዋላ ደግሞ በብዛት ይታዩ የነበሩት የህዝብ ማመላለሻ ታክሲዎችና የባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች ነበሩ፣ ዛሬ እንደተመለከትነው ያለው ፍሰት ወደ ተለመደ እንቅስቃሴው ተመልሷል ፡፡

አንድ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት የሥራ ኃላፊ ያልከፈቱ ሱቆች መታሸጋቸውን አረጋግጠውልናል ፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት አብዛኛዎቹ የንግድ ተቋማት ዛሬ ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ፣ የዘጉትን የንግድ መደብር ከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ተነግሯቸው ፈቃደኛ ያልሆኑትን አሽገናል ነው ያሉት፣ ቀጣይ ርምጃ በተመለከተ በቅርብ ይፋ ይደረጋል ነው ያሉት ፡፡

በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች የተለመደው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ከየቦታው የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል ። ከትንሣኤ በዓል በፊት በነበሩ ጥቂት ቀናት በባህርዳርና በሌሎችም የአማራ ክልል ከተሞች ከአዲሱ የልዩኃይል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ አለመረጋጋቶች እንደነበሩ ይታወሳል ።

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ