1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህል አልባሳት ገበያ እና የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ

ረቡዕ፣ መስከረም 22 2017

አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች ሊባል በሚችል መልኩ ገበያውን እያጥለቀለቀ የመጣው የባህል አልባሳት የየብሄሩን ባህል ከማሳደግ እና ከገጽታ ግንባታ ባሻገር የስራ ዕድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት በኤኮኖሚ ውስጥ የራሱን ጠጠር በመወርወር ላይ እንደሚገኝ ይነገርለታል።

https://p.dw.com/p/4lL8S
Ashenda cultural celebration in Mekelle, Tigray region, Ethiopia
ምስል Million Hailesilassie /DW

የባህል አልባሳት ግብይት መድራት እና ኤኮኖሚው ላይ የሚኖረው አንድምታ

የባህል አልባሳት እና ኢትዮጵያዉያን ክብረ በዓላት ትስስር 

እንዲህ በዓላት ተደጋግመው በሚመጡበት እና የተለየ ድባብ በሚፈጥሩበት እንደ መስከረም ባሉ ወራት ሰዎች በበዓላቱ ስለሚዘጋጁ ምግብ እና መጠጦች ብሎም በዕለቱ ስለሚለብሷቸው አልባሳት መጨነቃቸው አይቀርም ። አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች ሊባል በሚችል መልኩ ገበያውን እያጥለቀለቀ የመጣው የባህል አልባሳት የየብሄሩን ባህል ከማሳደግ እና ከገጽታ ግንባታ ባሻገር የስራ ዕድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት በኤኮኖሚ ውስጥ የራሱን ጠጠር በመወርወር ላይ እንደሚገኝ ይነገርለታል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ ብሎም ከኢትዮጵያ ውጭ ኢትዮጵያዉያን በርከት ብለው በሚኖሩባቸው ሃገራት  ለባህል አልባሳት ያለው  ፍላጎት ከፍ ብሎ ይታያል።  ይህ ደግሞ የባህል አልባሳት ዝግጅት በአይነት እና በመጠን እንዲጨምር እና ለበርካቶች  የስራ ዕድል እንዲፈጠር ምክንያት ስለመሆኑ ይነገራል። 

የሀገር ባህል አልባሳት
አሸንዳ ፣ ሻደይ ፣ በደቡብ ፣ ደቡም ምዕራብ እና  ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በተለያዩ ብሄረሰቦች በተናጥል የሚከበሩ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓላት ፣ የኢትዮጵያዉያን የጋራ አዲስ ዓመት ፤ የዳመራ እና የመስቀል በዓላት ሁሉ ከባህል አልባሳት ውጭ የሚታሰቡ አይደሉም ።  ዓመት ጠብቀው የሚከበሩት በዓላቱ እንደደመቁ እና እንዳሸበረቁ የየራሳቸውን ትዝታ ጥለው ያልፋሉ። 

የባህል አልባሳት ለስራ ዕድል ፈጠራ ያበረከተው አስተዋጽዖ
ፌኔት እንዳለ የባህል አልባሳት ዲዛይነር ወይም አዘጋጅ  ናት ። በባህል አልባሳት ዝግጅት እና ንግድ ከተሰማራች አራት ያህል ዓመታት ተቆጥረዋል። የኦሮሞ የባህል አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ የባህል አልባሳትን እያዘጋጀች ለገበያ ታቀርባለች ። የባህል አልባሳት ዝግጅት እና ግብይት እንደማንኛውም ንግድ ልፋት እንደሚጠይቅ የምትገልጸው ፌኔት በስራዋ ውጤታማ ለመሆን ለማስታወቂያ እና ጥራት ትኩረት እንደምትሰጥ ትናገራለች። 
« ከየትኛውም ቢዝነስ የተለየ ነገር የለውም። የትኛውም ቢዝነስ ልፋት ስለሚጠይቅ በጣም መጣርን ሁሌ መቀጠልን ሁሌ ፕሮሞሽን መስራት፤ እና ስራህን በየጊዜው ማሳደግ ፤ ስራህን መከታተል ፤ ኳሊቲ መጨመር ፤ የመጣውን ሰው ማስደሰት ፤ እነዚህ በየትኛውም ቢዝነስ ላይ ያለ ነው ።  »
ፌኔት ጉዳዬ ብላ ቅድሚያ የሰጠችው የማስታወቂያ እና የጥራት ስራ በእርግጥ አላከሰራትም ። ከአራት ዓመታት በፊት ስራውን ስትጀምር በጥቂት ገንዘብ ለዚያውም ብቻዋን ነበር  ። ዛሬ ግን ትናንት ስራዉን በጀመረችበት ስፍራ አይደለችም ። 
«ስጀምረው በሰው ብር ነው የጀመርኩት ። አሁን ግን በኢንቨስትመንት ደረጃ እየሰራን ነው ማለት ነው ። ወደ ኢንቨስትመንት እያዞርን በትልቅ ካምፓኒ እያደራጀን ነው ያለነው አሁን ። ብቻዬን ነው የጀመርኩት ፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ወደ 39 ሰዎች ከእኔ ጋር አሉ። በቀጣዩ ዓመት ወደ 400 ሰዎች እናስገባለን ብለን በኢንቨስትመንት እየሰራን ነው ያለነው ።»

የአሸንዳ በዓል ለማክበር የወጡ ልጃገረዶች
አሸንዳ ፣ ሻደይ ፣ በደቡብ ፣ ደቡም ምዕራብ እና  ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በተለያዩ ብሄረሰቦች በተናጥል የሚከበሩ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓላት ፣ የኢትዮጵያዉያን የጋራ አዲስ ዓመት ፤ የዳመራ እና የመስቀል በዓላት ሁሉ ከባህል አልባሳት ውጭ የሚታሰቡ አይደሉም ።ምስል Million Hailesillasie/DW

ሽመናን ያዘመነው ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ

የባህል አልባሳት ገበያ ውድድር በዝቶበታል
ከፊታችን  መስከረም 25  እና 26 በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተሞች የሚከበረው የእሬቻ በዓል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሳትፍ እንደመሆኑ መጠን  በየከተሞቹ የባህል አልባሳት ገበያው በከፍተኛ ደረጃ መድራቱ ይነገራል። በተመሳሳይ የባህል አልባሳት ዲዛይን እና ንግድ ስራ ላይ መሰማራቷን የነገረችን ሴና ግርማ የባህል አልባሳት ፍላጎቱ ማደግ በገበያው ላይ ከፍተኛ ውድድር አስከትሏል። 
«የገበያ ውድድሩ እንዲያውም ኢሬቻን ምሳሌ እናድርግ እና በየዓመቱ የሚታየው የፋሽን ጥበብ የሚገርም ነው ። ከአሁን በፊት የብሄሩ ተወላጆች ብቻ ነበሩ የሚሰሩት ። አሁን ግን ሌሎቹም እየሰሩት ነው ። በጣም ሰፊ ሆኗል ፤ በተለያየ ዲዛይን እየመጣ ነው ። በጣም የሚያስገርሙ ነገሮች እያየን ነው ። ከፍተኛ ውድድር አለ። »ከአገራዊው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማግስት አልረጋጋ ያለው ገበያ

ሴና ግርማ ፤ዲዛይነር
የባህል አልባሳት ዲዛይን እና ንግድ ስራ ላይ መሰማራቷን የነገረችን ሴና ግርማ የባህል አልባሳት ፍላጎቱ ማደግ በገበያው ላይ ከፍተኛ ውድድር አስከትሏል። ምስል Seyoum Getu/DW

የጎጆ ኢንደስትሪዎች ለማክሮ ኤኮኖሚ ማሻሻያ 
በእርግጥ ነው ይህ አንዳች ተስፋ ሰጭ ይመስላል። የማክሮ ኤኮኖሚዋን ላሻሻለች እና የውጭ ምንዛሪ ግብይቷን በገበያ ለወሰነች ሀገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሂደት ለምታከናውናቸው ትግበራዎች መሰረቱ የሚገኘውም መሰል የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ማሳየት ሲጀምሩ ነው። 
የኤኮኖሚ ባለሞያዉ አቶ አሸናፊ አዱኛ እንደሚሉት እንዲህ በሀገር ውስጥ ተመርተው ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙ አልባሳት በኤኮኖሚው ውስጥ የሚኖራቸው ሚናም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ነው። ይህ የገንዘብ ዝውውሩን በማሳለጥ ረገድም አዎናታዊ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። 

የአሸንዳ በዓል አከባበር በትግራይ
ኢትዮጵያ ውስጥ ብሎም ከኢትዮጵያ ውጭ ኢትዮጵያዉያን በርከት ብለው በሚኖሩባቸው ሃገራት  ለባህል አልባሳት ያለው  ፍላጎት ከፍ ብሎ ይታያል።ምስል Million Hailesilassie /DW

የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ቅድ ባለሙያዎቹ እንስቶች
« በኤኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ። በተለይም ከባህል አልባሳት ጋር በተያያዘ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰዱ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የበዓል አከባበሩ ምናልባትም በዚህ ሁለት ሶስት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ዝውውር የታየበትና ለወጣቶቹም ለአካባቢ ኢንደስትሪ ወይም ለጀማሪ ኢንደስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እየወሰደ እና ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚስተናገድበት ሆኖ ነው ያገኘሁት ።»
የባህል አልባሳት አዘጋጇ ሴናም ይህኑን ሃሳብ ትጋራለች። ስራዉን ስትጀምር ቀለል አድርጋ በማስተዋወቅ የጀመረች ቢሆንም በሂደት ዉጤት አግኝታበታለች። ስራዉ ሁነት እና በዓላትን ጠብቆ ከመስራት አሁን ዓመቱን ሙሉ ወደ መስራት ተሸጋግሯል ባይ ናት ።
« የበለጠ ስራዉን ለማስተዋወቅ ብዙም ገንዘቡ ላይ ወይም ገንዘብ እንደማግኛ አልሰራሁበትም ነበር። አሁን ግን መልካም ነው። በአጠቃላይ ግን የፋሽን ዲዛይን ስራ  ሙሉውን ዓመት የሚሰራበት ነው። ከመስከረም ጀምሮ ካየህ ፤ አዲስ ዓመት ፣ ከዚያ መስቀል አለ፣ ከዚያ ኢሬቻ አለ፤ ከዚያ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ድጋሚ የገና በዓል አለ፤ ከዚያ  በኋላ ደግሞ የሰርግ ወቅት ነው። ወደ ሰኔ አካባቢ ደግሞ የተማሪዎች ምርቃት አለ። ዓመቱን በሙሉ ስራ የሚሰራበት ነው»

በኦሮሞ የባህል አልባሳት ያሸበረቁ ልጃገረዶች
ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችውን የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ገቢራዊ ለማድረግ ብሎም  ከገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመላቀቅ ያላት አንደኛው አማራጭ ወደ ኢንደስትሪ የምታደርገውን ሽግግር ማፍጠን ነውምስል Seyoum Getu/DW

«የኤኮኖሚ ማሻሻያው» የብር አቅም መዳከም ለብዙኀኑ ሕዝብ ምን ማለት ይሆን?

የጥራት ችግር ጎልቶ ይታያል 
የባህል አልባሳት ዝግጅት እና ግብይት ሲነሳ በርካቶች አብረው የሚያነሱት ጉዳይ የጥራት ችግር ጎልቶ መታየቱን ነው። የባህል አልባሳት ዝግጅቱ ውበት ላይ ብቻ ማተኮሩ እና እንደሌሎች የዘወትር ልብሶች በጥራት አለመመረታቸው ተቀባይነታቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ሴና አልሸሸገችም ። ይህ ደግሞ አልባሳቱ በመሰል የውጭ ምርቶች እንዲተኩ መንገድ እንዲከፈት እና አልባሳቱን በጥራት ለማምረት በሚሞክሩ ጥቂት አምራቾች ላይ ጫና አሳድሯል።
 « በሀገር ልጆች የተሸመነ ልብስ እና ከውጭ የሚመጣ አንደኛ ዋጋው የተለያየ ነው። እዚህ በጣም አድካሚ ሆኖ ተሸምኖ የሚመጣውን ከውች በቀላል ዋጋ ነው የሚገባው ። ይህ አንደኛ ስራዉን በሚሰሩ ሰዎች ላይ ቻና ያሳድርባቸዋል። እኛን ደግሞ በጥራት የሚሰሩ ሰዎችን ስራቸውን ይደብቅባቸዋል። እንዲህ አይነት ነገር በበዛ ቁጥር ሰዉ ዋጋ ላይ ስለሆነ ትኩረት የሚያደርገው ወደዚያው ለመሄድ ይገደዳል ማለት ነው»

የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ያለው ሚና 
እንደዚያም ሆኖ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችውን የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ገቢራዊ ለማድረግ ብሎም  ከገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመላቀቅ ያላት አንደኛው አማራጭ ወደ ኢንደስትሪ የምታደርገውን ሽግግር ማፍጠን የግድ እንደሆነ ነው የመስኩ ባለሞያዎች የሚያሳስቡት ። የኤኮኖሚ ባለሞያው አቶ አሸናፊ እንደሚሉት  ሽግግሩ ሂደት የሚጠይቅ  እንደመሆኑ መሰል ጥቃቅን ኢንደስትሪዎች መበራከታቸው ሀገሪቱ ያላትን የሰው ሃይል በስፋት እና በአግባቡ በመጠቀም የስራ ዕድል እጦት ችግርን እየቀረፈች እንድትሄድ ያግዛታል።
« ኢንደስትሪ ዕድገት ውስጥ እስክንገባ «የሌበር ኢንተንሲቭ ነው » ይህ ማለት በብዙ ሰራተኛ ብዙ ምርት የምታመርትበት ፣ ሁለተኛ የስራ አጡን ቁጥር በዚሁ ረገድ ሊቀርፍልህ ስለሚችል በዚህ አግባብ የሚታይ እና መንግስት በቀጣይ ፈጠራን የማበረታታት በፖሊሲም የተቀመጠ ስለሆነ እዚያ ላይ በደንብ የሚሰራ ከሆነ ጥሩ ስራዎች ሊኖሩ ይችላሉ »

በባህል አልባሳት ያሸበረቁ ልጃገረዶች
የባህል አልባሳት ግብይት መስኩን ለማዘመን እና ለማሳደግ ግለሰቦች ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር መንግስት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል ምስል Seyoum Getu/DW

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያጸደቀው የኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት የፖሊሲ አላባዎች የሚሳኩ ናቸው?
ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት በእርግጥ ነው ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ቀላል የማይባል ሚና መጫወቱ አይቀርም። ነገር ግን የሀገር ውስጥ በተለይ የባህል አልባሳት አምራች  እንዱስትሪዎች ገና ከጎጆ እንደስትሪ ከፍ አለማለታቸው ብሎም ከውጭ ከሚገቡ ተመሳሳይ አልባሳት አንጻር ጥራታቸው ብዙ የሚቀረው መሆኑ መስኩን ከገጠሙ ተግዳሮቶች ተጠቃሽ ናቸው ። በተጨማሪም መንግስት ለመስኩ የሚሰጠው ትኩረትም በዚያው ልክ ተጠቃሽ መሆኑን ነው ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው እና በመስኩ የተሰማሩ ባለሞያዎች የሚናገሩት ። የባህል አልባሳት አዘጋጇ ፌኔት እንደምትለው መስኩን ለማዘመን እና ለማሳደግ ግለሰቦች ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር መንግስት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል ባይም ናት ።

የባህል አልባሳት የሀገር  ሀብት 
« ትልቅ የሀገር ሀብት ነው ይሄኛው ኢንደስትሪ ማለት ነው ፤ ስለዚህ በመንግስት ደረጃ ምንም አልተሰራበትም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ሰው በግሉ ነው እየጣረ ያለው ፤ የሀገራችን ልብሶች ዓለማቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራቸው በተለያዩ ዓለማቀፍ መድረኮች ላይ ሀገራችን የሚወክሉ ሰዎች በየመድረኮቹ ሲገኙ የሀገራችንን የባህል አልባሳት ለብሰው ቢገኙ፤ አርቲስቶችም እንዲሁ ልብሶቻችንን ለብሰው እንዲገኙ ማድረግ፣ እንደዚህ እንደዚህ አይነት ዕድሎችን ማድረግ አለበት ። »
በእርግጥ ነው ተወዳጅነቱ እና ተፈላጊነቱ እያደገ የመጣው የኢትዮጵያዉያን ባህል አልባሳት  ኢንዱስትሪውም ሆነ ግብይቱ በአንዳች የድጋፍ ማዕቀፍ ውስጥ ሊካተት ይገባዋል። በግልጽ እንደታየው የስራ ዕድል ፈጠራው እና የውጭ ምንዛሪ ማስቀረቱ  ብቻም ሳይሆን የተቀሩት የአፍሪቃ ሀገራት እንደሚያደርጉት ሁሉ ሀገራዊ ባህላዊ መለያም ነውና ተገቢ ትኩረት ይሻል ።
ታምራት ዲንሳ 
አዜብ ታደሰ