የበሽር አልአሳድ መንግሥት መውደቅ
እሑድ፣ ኅዳር 29 2017የበሽር አልአሳድ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ በርካታ ሐገራት የተለያዩ መግለጫዎች አውጥቷል። የጀርመኑ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ የበሽር አልአሳድ መንግስትን መውደቅ «መልካም ዜና» ብለውታል። ሾልስ አያይዘውም በሶርያ ከምንም በላይ አሁን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሕግና ስርአት በፍጥነት እንዲከበር ማድረግ ነው ብለዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤልቦርክ በበኩላቸው የአልአሳድ መንግስት መውደቅ ለሶርያውያን እፎይታን የሚሰጥ ቢሆንም ቀጣዩ መንግሥት በጽንፈኞች እጅ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ጃካ ካላስ የበሽር አልአሳድ መንግሥት መውደቅ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ ብለውታል። አክለውም «ይህ ፍጻሜ አልአሳድን ሲደግፉ የነበሩ እንደ ሩስያና ኢራን ያሉ ሐገሮች ደካማነትን ያሳያል» ነው ያሉት።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሂደቱን በትኩረት እየተከታተለው መሆኑን ገልጾ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በፍጥነት እንደሚረጋገጥ ተስፋ እንዳለው አትቷል።
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የበሽር አልአሳድ መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር በመደራደር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር መመሪያ በመስጠት ከሀገር መውጣቱን በመግለጽ በውይይቱ ግን የሩስያ መንግስት እንዳልተሳተፈ ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ በሶሪያ ባወጣው መግለጫም «የበሽር አልአሳድ መንግስት መውደቅ በሐገሪቱ ያሉ ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት እንደመልካም አጋጣሚ ሊወሰድ ይችላል» ብሏል።
የሳዑዲ መንግሥት ደግሞ «ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገናኝቼ እየሰራሁ ነው» ማለቱን የዘገቡት አሶሽየትድ ፕረስ እና ሮይተርስ ናቸው።
ዮሀንስ ገብረ እግዚአብሄር
ልደት አበበ