1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርሊን ግንብ ፤ ተምሳሌታዊው ድንበር 

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 11 2013

ግንቡ በቆመበት በ28 ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 140 ወንዶች ሴቶችና ህጻናት ወደ ምዕራብ ጀርመን ለመሻገር ሲሞክሩ ሕይወታቸው አልፏል።ለሰለባዎቹ መታሰቢያ በርናወር ሽትራሰ በታበለው ያኔ እንደ ኬላ በሚያገለግለው ስፍራ ላይ 200 ሜትር ርዝመት ያለው የግንቡ አካል ሳይፈርስ ቆሟል።ቦታው ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ሀገር ጎብኚዎች የሚያዘወትሩት ስፍራ ነው።

https://p.dw.com/p/3z67p
Bau der Berliner Mauer | Bernauer Straße
ምስል dpa/picture alliance

የበርሊን ግንብ ፤ ተምሳሌታዊው ድንበር

ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸንፋ ለሁለት ከተከፈለች በኋላ ፣በምሥራቅ ጀርመን መንግሥት የተገነባው የበርሊን ግንብ መሰራት የጀመረበት 60ኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት አርብ ታስቧል።የበርሊን ግንብ የዛሬ 30 ዓመት ከመፍረሱ በፊት ፣ለ28 ዓመታት ከተማይቱን ለሁለት ከፍሎ ቆይቷል። ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት የለኮሰው ከጎርጎሮሳዊው 1933 እስከ 1945  ጀርመንን ሲገዛ የነበረው ወንጀለኛው ናዚ ከተሸነፈ በኋላ፣ የተባበሩት ኃይሎች ከሚባሉት መካከል በዩናይትድ ስቴትስ ሶቭየት ኅብረት ብሪታንያና ፈረንሳይና እጅ የወደቀችው የጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ለሁለት ተከፈለች፤ ምሥራቅና ምዕራብ በርሊን ተብላ። ሶቭየቶች የከተማይቱን ምሥራቃዊ ክፍል ሲይዙ፣ምዕራብ በርሊን ደግሞ የአሜሪካኖች የብሪታንያ እና የፈረንሳይ መግቢያ መውጫ ሆነች። ኮሚኒስቶች ከተማዋን አንድ ለማድረግ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም  በ1949 የተመሰረተችው የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ GDR ወይም ምስራቅ ጀርመን ከሶቭየት ኅብረት ጎን ቆመች።የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ደግሞ ወደ አሜሪካው ሰፈር ተቀላቀለች።ምሥራቅ በርሊንም የGDR ዋና ከተማዋ ሆነች። በርሊን ከሽንፈቱ በኋላ ለሁለት ተከፍላ በሁለት መንግሥታት ስር ብትሆንም ነዋሪዎችዋ እንደልባቸው ይንቀሳቀሱ ነበር። አልነበረም። ይሁንና ከጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 13 ቀን 1961 ዓ.ም. በኋላ ይህ አልዘለቀም።በዚያን እለት በርሊንን ለሁለት የሚከፍል የሽቦ አጥር ድንገት መሰራት ሲጀምር መገንባት ሲጀመር፣ ከምዕራብ በርሊን ወደ ወደ ምሥራቅ በርሊን እንደ ልብ መሻገር ቀረ።ወደ ምዕራብ በርሊን ለሚጓዙም ሆነ ከምዕራብ ጀርመን በሚመጡ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ ጀመረ።  
ብዙም ሳይቆይ ወደ ግንብነት የተቀየረው አጥር  የጭቆናና የመከፋፈል ምልክት ሆነ።ዓላማውም በግልጽ የበርሊንን ለሁለት መከፈል ማረጋገጥ ነበር።በፍጥነት መላ ምዕራብ ጀርመንን የከበበ 3.5 ሜትር ከፍታና 155 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አጥር በብረትና በኮንክሪት ተሰራ። ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ምሥራቅ ጀርመን ከተመሰረተችበት ከ1949 አንስቶ ግንቡ እስከታጠረበት ጊዜ ድረስ 2.6 ሚሊዮን ሰዎች በፖለቲካውም ይሁን በባህሉ ረገድ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ገብተዋል። ከምሥራቅ ጀርመን ሰዉ በብዛት ወደ ምዕራብ ጀርመን መፍለሱ ምሥራቅ ጀርመንን እስከ መውደቅ አድርሷት እንደነበር ነው የሚነገረው። በፍልሰቱ ምክንያት ሐኪሞችን ጨምሮ በተለያየ ተፈላጊ ሙያዎች የሰለጠኑ ሰዎች እጥረት አጋጥሞም ነበር። ከፍተኛ ትምህርታቸውን እዚህ ጀርመን የተከታተሉትና ከዛሬ 50 ዓመት አንስቶ ጀርመን የሚኖሩት የፖለቲካ ሳይንስና እና የጋዜጠኝነት መምህር አቶ ክፍለ ማርያም ገብረወልድ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ችግሩ እንዳይባባስ ነበር የሃገሪቷ መሪዎች በምስራቅና ምዕራብ በርሊን ድንበር ላይ ግንቡን ለመገንባት የወሰኑት።ዓላማውም ሰዎች ከጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ  ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዳይሸሹ መከልከል ነበር። 
የምሥራቅ ጀርመን መንግሥት ግን ግንቡ የተሰራው ሰዎች እንዳይወጡ ለማድረግ ሳይሆን፣በተቃራኒው «በሰላም መኖር የምንችለው የምዕራብ ጀርመኖችን እንቅስቃሴ ስንገታ ነው» በማለት፣ ፍላጎቱ ከምዕራብ ጀርመን ሰዎች እንዳይገቡ ማድረግ መሆኑን ነበር የገለጸው። በወቅቱ ልዕለ ኃያላኑ፣ኮምኒስቷ ሶቭየት ኅብረትና ካፒታሊስቷ ዩናይትድ ስቴትስ የሚከተሉት የፖለቲካና ማኅበራዊ መርኅ አንዱ ከሌላው የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት ሽኩቻ ላይ ላይ ነበሩ።የኮምኒስቷ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ታማኝ የግንባታ ሠራተኞች ወደ ምዕራብ ጀርመን የሚወስዱትን መስመሮች በሙሉ ለመዝጋት ተሰማሩ። አብዛኛዎቹን አካባቢዎች በሽቦ አጥር ዘጉ። ግንቡን በበላይ ሃላፊነት ያስገነቡት፣ የያኔው «ድንበር ማስጠበቅ» የተባለው ዘመቻ ሃላፊ፣ኋላ ላይ ደግሞ የምስራቅ ጀርመን የመጨረሻው መሪ የነበሩት  ኤሪክ ሆኒከር ናቸው። ሁለቱ ሃገራት የጦር መሣሪያ ፉክክር ውስጥ በገቡት ቀዝቃዛው ጦርነት ሲባል ይጠራ በነበረው በዚያን ወቅት ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋትና የኒዩክልየር ጦርነት ውስጥ የመገባቱ ፍራቻ ያንዣበበት ጊዜ ነበር።ምሥራቅ ጀርመን የገነባችው የበርሊኑ ግንብ ግን ሰዉ ወደ ምዕራብ ጀርመን መፍለሱን አሳስቆመም ግንቡ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ምዕራብ ጀርመን ገብተዋል።
የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት የተገነባው ግንብ ብዙ ጉዳቶችን አስከትሏል። በተጨማሪ ሌሎች ጉዳቶችንም ማስከተሉን ነው አቶ ክፍለ ማርያም ያስረዱት ።
ግንቡ በቆመበት በ28 ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 140 ወንዶች ሴቶች እና ህጻናት ወደ ምዕራብ ጀርመን ለሻገር ሲሞክሩ ሕይወታቸው አልፏል። ለነዚህ ሰለባዎች መታሰቢያ በርናወር ሽትራሰ በታበለው ያኔ እንደ ኬላ በሚያገለግለው ስፍራ ላይ 200 ሜትር ርዝነት ያለው የግንቡ አካል ሳይፈርስ ቆሟል።ቦታ  ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ሀገር ጎብኚዎች የሚያዘወትሩት ስፍራ ነው። ይህን ቦታ ከሚያውቁት የዓይን ምስክሮች አንዱ ዮአሂም ሩዶልፍ ። ምሥራቅ ጀርመን ያሉ ሰዎች ወደ ምዕራብ ጀርመን ሾልከው እንዲገቡ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ 140 ሜትር ርዝመት ያለው መሻለኪያ ቆፍረዋል።ሩዶልፍና አንድ ጓደኛቸው ድንበሩ እንደተዘጋ ነበር ይህን መሿለኪያ የመስራቱ ሃሳብ የመጣላቸው።ያኔ ቀርበው የሽቦውን አጥር ሲያዩ ጠባቂዎቹ አስደነገጧቸው።
«ያያነው በመነገድ መካከል በሽቦ የተሰራ አጥር ነበር።ፊት ለፊቱ አምስት ወይም ስድስት ድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ነበሩ።ሁሉም በትክሻቸው ክልሽንኮቮ አንግበዋል። ጭንቅላታቸውም ላይ የአደጋ መከላከያ ቆብ አጥልቀዋል።ድንገት ብዙ ጩኽት ተሰማ።ምን እየሰራችሁ ነው?አታነቡም እንዴ? ይህ የድንበር ክልል ፣ማለፍ አይቻልም! አካባቢውን ለቀን ካልወጣን ጠመንጃውን ወደኛ ማዞራቸው አይቀርም አለን ።»
ጓደኛሞቹ  እግሬ አውጭኝ ብለው ይሸሻሉ።ከዚያ በኋላ ነበር ሌሎችንም ለመርዳታ በመነሳሳት መሿለኪያውን የሰሩት። ኢትዮጵያዊው መካኒካል ኢንጅነር ወልደ ጊዮርጊስ ደምሴ  በርሊን ሲኖሩ 47 ዓመታት ተቆጥረዋል።የበርሊን ግንብ ከተገነባ ከ 13 ዓመት በኋላ ነበር ለተጨማሪ ትምሕርት  ምዕራብ በርሊን የመጡት።ከዚያ በፊት የነጻ ትምሕርት እድል አግኝተው በመጡባት በቡልጋሪያ  ለ9 ዓመታት ምህንድስና አጥንተዋል። ስለ በርሊኑ ግንብ ብዙ ትውስታዎች አሏቸው። 
የበርሊኑ ግንብ በተገነባ በ28 ዓመቱ በጎርጎሮሳዊው 1989 ሲፈርስ የቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ ሆነ። በጦርነት ሰበብ ሳይወድ በግድ የተለያየው ህዝብ ጀርመን ተዋህዳ አንድ ከሆነ እነሆ 30 ዓመት አለፈ። 
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 
 

Mauerbau
ምስል dpa/picture alliance
Deutschland Bau der Berliner Mauer 1961
ምስል Getty Images/Keystone
Mauerbau Berlin
ምስል picture alliance / akg-images