1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አፋር በመሬቱ፣ በእምነቱ፣ በሚስቱ እና በግመሉ አይደራደርም»

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2015

በአፋር ሕዝብ ዘንድ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት የአንድ ሰው ነፍስን ያጠፋ ግለሰብ ሲዳኝ ካሳ የሚከፍለውግመልን በመስጠት ነው። ይህ የሚያሳየውደግሞ የአፋር ማኅበረሰብ ግመልንእንደ ሰው ህይወት ማየቱ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4Om6k
በአፋር በረሀ እቃ በማጓጓዝ ላይ ያለች ግመል
በአፋር በረሀ እቃ በማጓጓዝ ላይ ያለች ግመል ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

ግመሎችን የሚያወድሱ፣ የሚያሞግሱና ከነርሱ ጋር በተያያዘ የሚገጠሙ ሥነ-ቃሎች ጋሊሳሬ ይባላሉ።

ግመልበተለያዩ የኢትዮጵያ ቆላማ  አካባቢዎች ለመጓጓዣነት ብሎም  የወተት እና የስጋምርትን  በመስጠት ይታወቃል።በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በአፋር ክልል የሚገኘው የአፋር ብሔረሰብ አባላት በአብዛኛው በአርብቶ አደርነት የሚተዳደረው የኅብረተሰብ ክፍል ግመልን በቤት እንስሳት ይጠቀማል፡፡ ለአፋር ማኅበረሰብ  ግመል ከእየለት ሕይወቱ ጋር ጋር የተሳሰረ ብሎም የበርሃው መርከብሲል በቅጽል ስም ይጠራዋል። ለቀባሪው አረዱ እንዳይሆን እንጂ ግመል ለአፋር ሰው እንደ ዓይን ብሌን የሚሳሳላት እንስሳ ነው። የአፋር ክልል የቱሪዝም ዳሬክተር  የሆኑትአቶ መሀመድ ሀሰን፤  አፋር ከማይደራደርባቸውአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ግመል ነው ይላሉ።     

«አፋር በመሬቱ፣ በእምነቱ፣ በሚስቱ እና በግመሉ አይደራደርም። እነዚህን በአራቱን የሰጠ ከፈጣሪው ጋር የተጣላ ነው»ብለዋል 

በአገራችንየተለያዩ አይነት የፍርድ የሸንጎ ስርአቶች መኖራቸዉን የሚናገሩት የአፋር ክልል የቱሪዝም ዳሬክተር  አቶ መሀመድ፤ በአፋር ሕዝብ ዘንድ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት የአንድ ሰው ነፍስን ያጠፋ ግለሰብ ሲዳኝ  ካሳ የሚከፍለውግመልን በመስጠት ነው።  ይህ የሚያሳየውደግሞ የአፋር ማኅበረሰብ ግመልንእንደ ሰው ህይወት ማየቱን ይላሉ።  

የአፋር ነዋሪና የአካባቢው ሽማግሌ እንዲሁም  የበርካታ ግመሎችባለቤት የሆኑት  ሀጂ መሀመድ አብደላም  « አፋር ላይ አንድ ሰው በሰው እጅ ከሞተ ለሟች ቤተሰብ ካሳ የሚከፈለው በግመል ነው» በአፋር ያለግመል የሰው ነፍስ ካሳ ክፍያ አይደረግም ገዳይ እስከ150 ግመል ድረስ ክፍያ እንዲከፍል ይታዘዛል ።«አፋር እንደህይወቱ ነው ግመሉን የሚጠብቀው» ይላሉ ሀጂ መሀመድ 

ታሪክን አንስተው ስለአፋር እና ግመል እንዲሁም ግመሎች ስለባንዲራ ያላቸውን የነገሩን  ሀጂ መሀመድ አፋር እና ግመል ካላቸው የጠበቀ ቁርኝት የተነሳ  የአፋር 13 ኛው ሱልጣንግመሎቻችን ባንዲራችንን ያውቁታል ብለው እንደነበር ያስታውሳሉ «እኛ ቀርቶ የኛ ግመሎች ስለኢትዮጵያ አንድነት እና ባንዲራ ያውቃሉ »ምክንያቱም « ድሮ ባንዲራ ሲሰቀል እና ሲወርድ መዝሙር ይዘመር ነበር መዝሙር እየተዘመረ ግመሎቹ ጠዋት ከቤት ሲወጡም ሆነ ወደ ቤት በሚመለሱበት ወቅት ባንዲራ ሲሰቀልም ይሁን ሲወርድ ይቆማሉ ለዚህ ነው ሱልጣናችን አሊ ሚራህ እኛ ቀርቶ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራን ያውቃሉ ያሉት»   

የግመልወተት ለአፋር አርብቶ አደር ከዋና ዋና የዕለት ተዕለት ምግቦቹ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡በአፋር  የግመል ወተትከከብት ወተት በተሻለ ተመራጭና ሰውነት ገንቢ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡በቀን በአማካኝ እስከ 12 ሊትር ወተት ከአንድ ግመል ይገኛል።  ባለፉት ግዜያት  በርካታ ሰዎችየግመል ወተትን  አይጠጡትም ነበር። አሁንላይ ግን ተፈላጊነቱ ስለጨመረ ዋጋውም ከፍ ማለቱን የገልጹት የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ዳይክሬተር  ግመሎች ተገቢውንትኩረት እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል

«ባሁኑ ወቅት አንድ ሊትር የግመል ወተት 200 ብር ገብቷል» ያሉን አቶ መሀመድ  ግመል ወተቷ ለተለያዩ በሽታዎች መድሀኒት እንደሆነ ነግረውናል«ለሆድ ድርቀት ለኮሌስትሮን እንዲሁም ለተለያየ በሽታ መድሀኒት ነው»ሲሉ ተፈላጊነቱም እንደጨመረ ተናግረዋል ።

Dürre in Somali Region
ግመል በኢትዮጵያምስል Mulugeta Ayene/UNICEF/AP/picture alliance

በአፍሪቃ የግመል ወተት ካላቸዉ አገራት መካከልሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ማሊ፣ ኢትዮጵያ፣ ኒጄር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ እና ሱዳን ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ይነገራል። አፋሮች ግመልን ሲያወድሱ ይለያሉ ያሉት የህብረተሰብ ጥናት ማለትም የፎክሎርባለሙያው አቶ አበበ ኃይሉ ‹‹ጋሊሳሬ በአፋር ብሔረሰብ የግመል ውዳሴ ግጥሞች›› በሚል ርዕስ ጥናት አካሂደዋል። አቶ አበበ በዚህ ጥናት አፋሮች ካሏቸው የተለያዩ የቃል ግጥሞችና ዘፈኖች መካከል በተለይ ግመሎችን የሚያወድሱ፣ የሚያሞግሱና ከነርሱ ጋር በተያያዘ የሚገጠሙ ሥነ-ቃሎች ጋሊሳሬ እንደሚባሉም ገልፀዋል። 

በአፋሮች ዘንድ ባህል ሞልቶ ቢተርፍም የሀብት መለኪያው ግን የግመል ቁጥር ነው።

በክልሉ ያሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግመል ሲሞት ለግመዋ ለባለቤት ትልቅ መርዶ ነው። ስለግመሉ መሞትም የሚነገረዉ በሰው  ከተሰበሰበ በኋላ ነዉ ምክንያቱም ለፋር ግመሉ ልጁ ናት ይላሉ የክልሉ የቱሪዝም ዳሬክተር  «አንዳንድ አካባቢ አንድ ግመል ሲሞት ለባለቤቱ ለመንገር ሰው ተሰብስቦ የታጠቀውም ጊሌ አስወልቀው ቁጭ አርገው ነው ምክንያቱም እንደ የአይኑ ብሌን ነው የሚያያት።» ብለዋል

በአፋሮች ባህል ግመሎችን ያለአግባብ ማንገላታት፣ መደብደብና ሌሎች ጥቃቶችን ማድረስ ርህራሄ የጎደለው ተግባር ተደርጎ ይወሰዳል። ጦርነት ሚከሰትም ግመሎቻቸውን ላለመስጠት የግመል አስተዳዳሪዎች ነፍሳቸውን እስከመስጠት ይዋጋሉ ያሉን  ሀጂ መሀመድ አብደላም የግመል እድሜዉ ትልቅ መሆኑንም ተናግረዋል  «ግመል ብዙ ግዜ ይቆያል ወደ60 አመት ይቆያል እስከ መጨረሻዋ ድረስ ትወልዳለች ምትበላበት ጥርስ እስከምታ ድረስ ትቆያለች» 

ተጀምሮ የቆመው የግመል ፌስቲቫልን ለመጀመርግመል በብዛት የሚገኝባቸው ቦታዎች እየተነጋገሩ እንደሆነ እና እቅድም እንዳላቸው ተናግረዋል።«ከዚ ቀደም የጀመርነው ፌስቲቫል ተቋርጧል። ድሮ አፋር ላይ ይደረግ ነበር እንደገና ለመጀመር ከኦሮሚያ ከሱማሌ እና ከድሬደዋዎች ጋር ተነጋግረን»ያሉት ሀላፊው የፌስቲቫሉ መደረግ «የግመሎች ባለቤቶች ግመሎቻቸውን በስነስርአት እንዲይዙ ያደርጋል » የሚል እምነት አላቸው።

ግመልእንደ አፋር ላለ በርሃማ አካባቢ የተለያየ ጥቅም ይሰጣል። በተለይ በአፋር ሞቃታማ ስፍራ በዳሎል ላይ የሚመረተውን ጨው ግመል በጀርባዉ ተሸክሞ ብዙ እርቀት ተጉዞ ለገበያ በማቅረብ ለአገሬው ህዝብ የጀርባ አጥንት በመሆን እያገለገለ የሚገን እንስሳ ነዉ። ለአፋር ግመል ቀኝ እጁ እንደማለት ነዉ። 

ማኅሌት ፋሲል 

አዜብ ታደሰ