1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፤ የሐምሌ 9 ቀን 2016 ማክሰኞ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2016

የዓለም ዜና፤ የሐምሌ 9 ቀን 2016 ሰኞ አርዕስተ ዜና --የዩናይትድ ስቴትሱ ሪፐብሊካን ፓርቲ ዶናልድ ትራምፕን ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲፎካከሩ በይፋ መረጠ። ትራምፕ በበኩላቸዉ የአንድ ወቅት ተቃዋሚያቸውን ተጣማሪያቸው አድርገው መረጠዋል። --በኬንያ ዛሬ ፕሬዝዳንት ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ዳግም ፖሊስ በአስለቃሽ ጢስ በተነ። --በሩዋንዳዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፤ ፖል ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ባደረገዉ የቅድመ ቆጠራ ዉጤት አስታወቀ። --የሃንጋሪ ጠ/ሚ ቪክቶር ኦርባን የሚያደርጓቸውን አወዛጋቢ ጉዞዎች ተከትሎ የአዉሮጳ ህብረት ምክር ቤት እገዳ አስተላለፈ።

https://p.dw.com/p/4iNvs

ኬንያ፤ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ተቃዉሞ 

በኬንያ ፖሊስ ዛሬ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ተቃዋሚ የአደባባይ ሰልፈኞችን በአስለቃሽ ጢስ በተነ። ናይሮቢ አቅራቢያ በምትገኘው ኪተንጌላ ክፍለ ከተማ ወደ 200 የሚጠጉ  ጎማ ሲያቃጥሉ እና ፀረ-ሩቶ መፈክሮችን ሲያሰሙ የነበሩ ተቃዋሚዎችን ፖሊስ በሰለቃሽ ጢስ መበተኑንን ዶቼ ቬለ ዘግቧል። በማዕከላዊ ናይሮቢ እና በሞምባሳ ከተማም ዛሬ ተመሳሳይ የተቃዉሞ ሰልፍች እንደነበሩ ተዘግቧል።  
  ፕሬዚዳንት ሩቶ አወዛጋቢ የሆነዉን የግብር እቅድ  ተከትሎ፣ የካቢኔ ሹምሽር እና የያዙትን የግብር እቅድ ቢሰርዙም ፀረ-መንግሥት ተቃውሞው ዛሬም በኬንያ በተለዩ አካባቢች እንደቀጠለ ነዉ። ወጣት የፖለቲካ ተሟጋቾች ዛሬ ማክሰኞ በአገር አቀፍ ደረጃ ማንኛዉ አይነት ስራ "ዝግ" እንዲዉል ጥሪ ማቅረባቸዉም ተሰምቷል። አዲስ የተቋቋመው እና ጄን ዜድ የተባለዉ የኬንያዉ የተቃውሞ እንቅስቃሴ፤ ለኬንያ አስተዳደር ውድቀት፣ ለሙስና እና ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ለበርካታ ወጣት ተቃዋሚዎች ሞት ተጠያቂ ናቸዉ ሲል ፕሩዚዳንት ዊልያም ሩቶን ይከሳል። 

ሩዋንዳ ፤ ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸው ተነገረ

ትናንት  ሰኞ የተካሄደዉን የሩዋንዳን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፤ ፖል ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ባደረገዉ የቅድመ ቆጠራ ዉጤት አስታወቀ። እስካሁን ከተቆጠረው 79 በመቶ ድምጽ ካጋሜ፤ 99 ነጥብ 15 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታዉቋል።  
ዘጠኝ ሚሊዮን ነዋሪዎች በሚገኙባት ሩዋንዳ፤ የ66 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ካጋሚ ለአራተኛ ዘመነ ስልጣን  የሚያቆያቸውን ድምፅ ማግኘታቸው ከመጀመርያዉም የሚጠበቅ ነበር ተብሏል።  
በምርጫዉ የተሳተፉ  ሁለት የካጋሜ ተቀናቃኞች 0.53% ድምፅ እና 0.48% ድምፅ ማግኘታቸዉን፤ የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል። በሮይተርስ ዘገባ መሰረት፤ በሩዋንዳዉ ምርጫ ሦስት ብርቱ የካጋሚ ተቀናቃኞች፤ ቀደም ሲል ከምርጫ ፉክክሩ ውጭ መሆናቸዉን አስታዉሷል።
 የ 66 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ካጋሜ የሚደርስባቸዉን ማንኛውንም ትችት በፍጥነት ዝም በማሰኘት አምባገነን እንደሆኑም ይገለጿል።  ይሁን እና ግን ደግሞ፤ በሩዋንዳ በጎርጎረሳዉያኑ 1994 ዓም ከተፈፀመው አውዳሚ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በኋላ፤ ሩዋንዳን  ወደ መረጋጋት የመለሱ ጠንካራ መሪ መሆናቸዉ ይነገርላቸዋል። ወደ 800,000 የሚጠጉ ሰዎች፣ በአብዛኛው የቱትሲ ጎሳዎች፤ በዘር ጥላቻ ሩዋንዳ 100 ቀናት ውስጥ መገደላቸዉ የሚታወስ ነዉ። ካጋሜ ከጎርጎረሳዉያኑ 2000 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ የሩዋንዳ መሪ እና ፕሬዝዳንት ሆነው እስከዛሬ ዘልቀዋል። 

ሱዳን፤  በተፋላሚ ቡድኖች መካከል የቀጠለዉ ዉይይት  

በተባበሩት መንግሥታት መልእክተኛና በሁለቱ ሱዳን ተፋላሚ ወገን ልዑካኖች መካከል ጄኔቫ ላይ የሚካሄደዉ ዉይይት በዚህ ሳምንትም እንደቀጠለ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት አስታወቀ። ጄኔቫ ላይ የቀጠለዉ ይህ ዉይይት በተለይ  በሰብዓዊ ርዳታና ሰላማዊ ሰዎችን በመጠበቅ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመልክቷል።   
ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2023 ሚያዝያ ወር ላይ በሱዳን ጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ በአብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና በቀድሞው ምክትላቸው በሞሐመድ ሃምዳን ዳግሎ በሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል  በተቀሰቀሰዉ ጦርነት ከ 10 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ እንደተፈናቀሉ፤ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት «IOM» አስታዉቋል። 
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጉ ወይም ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሱዳናዉያን ከፍተኛ "ለምግብ እጦት"  መጋለጣቸዉ መረጋገጡን ገልጿል።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የሱዳን የግል መልዕክተኛ የቀድሞዉ የአልጀርያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራን ጨምሮ የሱዳን ጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ በአብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የቀድሞው ምክትላቸው የሞሐመድ ሃምዳን ዳግሎ ልዑኮች ዉይይታቸዉን የጀመሩት ባለፈዉ   ሐሙስ መሆኑ ይታወቃል።
 

ሴኔጋል፤  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ጉብኝት

በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ጉብኝት ላይ የሚገኙት የፌደራል  ጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በሴኔጋል መዲና ዳካር ላይ ባደረጉት ንግግር በአካባቢው ከሚገኙ ሀገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲጠናከር ጠየቁ። ዴሞክራሲን የሚያራምዱ አዉሮጳዉያን ሃገራት መዋዕለ ንዋይ በማያፈሱባቸዉ ቦታዎች ሌሎች አገሮች በመዋዕለ ንዋይ  አማካኝነት ጥገኛነትን መፍጠራቸዉ፤ ጥርጣሬ ቢፈጠርም፤ ከአውሮጳ ጋር እንደሚቃርን መሆኑን ቤርቦክ አክለዉ ተናግረዋል።
የምዕራባዉያኑ ሀገራት ፤ በአፍሪቃ የሚሰሩት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ቁርጠኝነታቸዉ በራሳቸዉ ምጣኔ ሐብታዊና የፀጥታ ጠቃሚታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርዋ አክለዋል።   
ቻይና እና ሩሲያ በአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ እንቅስቃሴያቸዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጀርመንዋ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በንግግራቸዉ ጠቅሰዋል።  ፊታቸዉን ወደ ሩስያ ያዞሩት ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር፣  ከጎርጎረሳዉያኑ 2020 ዓ.ም  ጀምሮ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸዉ እና በወታደራዊ አገዛዝ ስር የሚገኙ ሃገራት  መሆናቸዉ ይታወቃል። በምዕራብ አፍሪቃ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የጀርመንዋ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ዛሬ የሴኔጋል ጉብኝታቸዉን አጠናቀዉ ወደ ኮትዲቫር አቅንተዋል። 

ሃንጋሪ፤ የአዉሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምላሽ

የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የሚያደርጓቸውን አወዛጋቢ ጉዞዎች ተከትሎ በሀንጋሪ የአዉሮጳ ህብረት ምክር ቤት አመራር ሥር የሚደረጉ ማንኛዉም ስብሰባዎችን ማገዱን አስታወቀ።
የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ለአዉሮጳ ህብረት ኮሚሽነሮች ስብሰባ ወደ ሃንጋሪ ላለመጓዝ መወሰናቸዉን ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል። በሃንጋሪ በሚካሄደዉ ስብሰባ  ላይ የህብረቱ ኮሚሽን የሚወከለው በከፍተኛ ባለሥልጣናት ብቻ እንደሚሆንም ተገልጿል። የኦርባንን እርምጃ ተከትሎ ህብረቱ ሃንጋሪን በከፊል ማገዱን ነዉ ያስታወቀዉ። ሃንጋሪ የህብረቱ ምክር ቤት በዙር የሚደርሳትን አመራርነት ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ስትጀምር፤ የሃንጋሪዉ ጠቅላይ ሚኒስትር በዩክሬን ጦርነት መፍትሄ አስገኛለሁ በሚል፤ በገዛ ፈቃዳቸዉ "የሰላም ተልዕኮ" ሲሉ ማወጃቸዉ፤ የህብሩትን አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ማስቆጣቱ ተመልክቷል።  ይህን ተከትሎ የሃንጋሪዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን፤ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤  ከቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ እንዲሁም ከቻይናዉ  መሪ ዢ ሺ ፒንግ ጋር እንደተገናኙ ተገልጿል።  

አሜሪካ፤ ትራምፕ የአንድ ወቅት ተቃዋሚያቸውን ተጣማሪያቸው አድርገው መረጡ

ከቀናት በፊት የግድያ ሙከራ የተደረገባቸዉ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናል ትራምፕ የአንድ ወቅት ተቃዋሚያቸውን ጄዲ ቫንስንን ተጣማሪያቸው አድርገው መረጡ። የ78 ዓመቱ ትራምፕ በ39 ዓመት የሚያንሳቸዉን ቫንስን መምረጣቸው በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወጣቶችን ወደፊት የማምጣት ጥሩ ጅምር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ተገልጿል። ትራምፕ ምርጫዉን ቢያሸንፉ ቫንስ ምክትላቸዉ ሆነዉ ይሾማሉ። የኦሃዮ ስዊንግ ግዛት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባሉ ጄዲ ቫንስ ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ትራምፕን በመተቸት ቢታወቁም በፓርቲያቸው ውስጥ ግን በርካታ ደጋፊ እንዳላቸው ተዘግቧል።  
የዩናይትድ ስቴትሱ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሌሊቱን ብሔራዊ ጉባኤውን ሲያካሂድ ዶናልድ ትራምፕን በህዳር ወር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲፎካከሩ በይፋ እና በድምቀት መርጧቸዋል። ከእያንዳንዱ ግዛት የተወከሉ ድምፅ ሰጪዎች ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆኑ ዘንድ ድጋፋቸውን በጋለ ስሜት ሲገልፁላቸዉም ተስተዉሏል። ትራምፕ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው ከሁለት ቀናት በኋላ ትናንት ምሽቱን በይፍ በጉባኤው ላይ ሲገኙ፤  የጋለ እና በደማቅ አቀባበል ነዉ የተደረገላቸዉ። 
የሪፑብሊካኑ ብሔራዊ ጉባዔ ለአራት ቀናት ማለት እስከ መጭዉ ሐሙስ የሚዘልቅ ነዉ። እንደ ፓርቲዉ አሰራር ጉባዔዉ አብዛኛውን ጊዜ የሚደመደመው ፓርቲዉ ለፕሬዚዳንትነት በእጩነት በመረጠዉ ግለሰብ  ታላቅ ንግግር ነው።

አፍጋኒስታን፤ ከባድ ዉሽንፍር የቀላቀለ ዝናብ ቢያንስ 40 ሰዎችን ገደለ

በምሥራቅ አፍጋኒስታን ከባድ አዉሎንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ቢያንስ 40 ሰዎችን ገደለ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ጉዳት አደረሰ። የናንጋርሃር ክፍለ ሀገር የአደጋ መከላከል ባለስልጣን ኃላፊ እንደተናገሩት፤  ከባድ አዉሎነፋስ የቀላቀለዉ ዝናብ፤ ባስከተለዉ አደጋ 350 ሰዎች ቂስለዋል  ወደ 400 የሚጠጉ ቤቶች ደግሞ ወድመዋል።
ትናንት በምሥራቅ አፍጋኒስታን የደረሰዉ ይህ ከባድ ዝናብ አዉሎንፋስ እና የመጥለቅለቅ አደጋ የታየዉ ባለፈዉ በግንቦት ወር በአፍጋኒስታን ድንገተኛ ጎርፍ ተከስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደለና 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በግብርና የሚተማመንበትን ትላልቅ የእርሻ ቦታዎች ካወደመ በኋላ ነው።
 

አዜብ ታደሰ / ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።