1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሌ ክልል ፖለቲካዊ ቀዉስ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17 2010

በምሥራቃዊ የኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል በኅብረተሰቡ እና በአስተዳደሩ መካከል አለመግባባቱ መባባሱን የአካባቢው ተወላጆች ይናገራሉ። ትናንት በክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ ተደረገ የሚሉት የተቃውሞ ሠልፍም የዚሁ ነፀብራቅ ነው። በወቅቱም የክልሉ ልዩ ፖሊስ ሠልፈኞችን ለመበተን በወሰደው ርምጃ የተጎዱ ጥቂት አይደሉም።

https://p.dw.com/p/321dg
Somali Äthiopien Shinile-Zone Dürre erschwert Lebensbedingungen
ምስል J. Jeffrey

የክልሉ ነዋሪዎች እና ባለስልጣናቱ የሚገልፁት ይለያያል፤

  
 የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ በበኩላቸው ትናንት ተፈጠረ የተባለውን ግጭትም ሆነ የተቃውሞ ሠልፍ ከማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያነት የዘለለ እውነት አይደለም ይላሉ።

የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንደሚሉት ሰሚ አላገኙም እንጂ በክልሉ አስተዳደር ያደረባቸውን ቅሬታ ለፌደራል መንግሥት ሳይቀር ለማሰማት ዋና ከተማ አዲስ አበባ ድረስ ሄደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማግኘት ለወራት ያደረጉት ደጅ ጥናት አለመሳካቱ ደግሞ ችላ ተብለን የሚል ስሜትን ፈጥሮባቸዋል። በመቶዎች ከሚቆጠሩ የአካባቢው ሽማግሌዎች፤ ምሁራን እና ወጣቶች ጋር አዲስ አበባ እንደነበሩ የገለፁልን አንዱ ትናንት ጅግጅጋ ላይ ነበረ የሚሉት ተቃውሞም የዚያው ነፀብራቅ ነው ይላሉ።

«ጂግጂጋ ትናንት ከትናንት ወዲያ ሕዝቡ ተቃውሞ አደረገና መቶ ምናምን ወጣቶች የታሠሩትን ሕዝቡ ኡኡ ብሎ አስወጣቸው። ዛሬ ደግሞ ችግር አለ፤ ይሄ ችግር ሌላ አይደለም ሰውየውን ለመጣል ነው። ሕዝቡ ትልቅ ተቃውሞ ለማሳየት እየሞከረ ነው።»

እኝህኛው የሶማሌ ክልል ነዋሪ ደግሞ ጅግጅጋ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸውን ገልፀው ትናንት ተደረገ የሚሉትን እንዲህ ያስረዳሉ።

«ትናንት ሰው ሰልፍ ወጥቶ በልዩ ፖሊስ በትኖ ነበር፤ የታሰሩ ልጆችም አሉ፤ ስማቸውን ራሱ መጥቀስ ይቻላል። አብረን የተማርን ናቸው ሦስቱም የክልሉ ምሁራን ናቸው። የእስረኞቹን መፍታት ጥያቄ ይዞ ነው ሕዝቡ ሰልፍ የወጣው።»

ትናንት ተካሄደ ባሉት ሰልፍ እና ግጭት የታሠሩም የተደበደቡም ሰዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። ጉዳዩን ለማጣራት የደወልንላቸው የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኢድሪስ ሰኢድ የተባለው ሁሉ «ሃሰት ነው» ባይ ናቸው።

«ኮምፕሊትሊ ውሸት ነው፤ ውሸት ነው ምንም የተከሰተ ነገር የለም። የታሰረም እኮ የለም።» «ፕሬዝደንቱን የሚቃወም ምንም አይነት እንቅስቃሴ በጅጅጋ የለም?» «እየነገርኩሽ ያለሁት እውነቱን ነው። ምንም አይነት ነገር የለም።»

አቶ ኢንድሪስ አያይዘውም በሶማሌ ክልል ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ የፊታችን ሐምሌ 29 ቀን በክልሉ በሚካሄድ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን ማጋራት እንደሚችሉም ገልጸዋል። (ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ)

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ