1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስማርት ስልኮቻችንን ደህንነት እንዴት እንጠብቅ?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 6 2014

በአሁኑ ወቅት በተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን የኢሜል ግንኙነት፣የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን፣የባንክ እና ሌሎች መረጃዎችን ማስቀመጥ እየተለመደ መጥቷል።ነገር ግን ከአጠቃቀም ጉድለት መረጃዎቻችን ለመረጃ መንታፊዎች ይጋለጣሉ። ለመሆኑ በስማርት ስልኮቻችን አጠቃቀም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ምንምን ናቸው። መፍትሄዎቹስ?

https://p.dw.com/p/4E3Qu
Gmail Mailbox Interface
ምስል Thiago Prudencio/Zumapress/picture alliance

ነፃ የዋይፋይ አገልግሎቶችን ባገኘን ቁጥር ከመጠቀም መቆጠብ ችግሩን ይቀንሳል


በአሁኑ ወቅት በተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን የኢሜል ግንኙነት፣የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን፣የባንክ  እና ሌሎች መረጃዎችን ማስቀመጥ እየተለመደ መጥቷል።ነገር ግን ካለማወቅ ከሚደረግ የአጠቃቀም ጉድለት ብዙ መረጃዎቻችን  ለመረጃ መንታፊዎች የመጋለጥ ዕድል ይኖራቸዋል። ለመሆኑ የስማርት ስልኮቻችንን ደህንነት በምን መልኩ ማስጠበቅ እንችላለን?አጠቃቀም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ምንምን ናቸው። መፍትሄዎቹስ?  የዛሬውን የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ትኩረቶች ናቸው።
በዓለም ላይ በይነ-መረብ እና የስማርት ስልኮች አጠቃቀም  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም ከሌላው ዓለም ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ ይሁን እንጅ  አጠቃቀሙ እያደገ መጥቷል።
በጎርጎሪያኑ 2022 መጀመሪያ ላይ በወጣ መረጃ መሰረት የበይነ-መረብ  አገልግሎት  በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ 25 በመቶ ደርሷል። ይህም በ2021 ከነበረው  ተጠቃሚ   በ731 ሺህ (2.5 በመቶ) መጨመሩን መረጃው ያሳያል።በጎርጎሪያኑ ጥር 2021 የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በኢትዮጵያ ወደ 45 ሚሊዮን የሚጠጉ የተንቀሳቃሽ ስልክ ግንኙነትቶች አሉ።ይህም ከጠቅላላው ህዝብ 38.5% ያህሉ ነው። ይህ ቁጥር በ2020 ከነረው ወደ 710,000 ተጠቃሚዎች (ወይም 1.6%) ማደጉን መረጃው አመልክቷል። 
በዚህ ሁኔታ እያደገ በመጣው የስማርት ስልክ  አጠቃቀም ታዲያ ወዳጅ ዘመድን ከመጠየቅ ባለፈ መረጃ ለመለዋወጥ ፣ለኢሜል ግንኙነት፣ለባንክ፣ ለግብይት፣የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለመጠቀም፣ የመዝናኛ ዝግጅቶችን ለመከታተል እና  ወዘተ በማገልገል ላይ ይገኛል።

Eco Africa | 08.07.2022
ምስል DW

ከዚህ የተነሳ  ተንቀሳቃሽ ስማርት ስልኮቻችን ከአብዛኛው የዕለት ተዕለት እንቅሳቃሴ እና ህይወታችን ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ሆነዋል።በዚያው ልክ ደግሞ  ቴክኖሎጅ ከጠቀሜታው ጋር ይዞት የሚመጣው የራሱ ተግዳሮቶች  አሉት እና  አጠቃቀማችን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ  ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።ይህም መረጃዎቻችን በመረጃ መንታፊዎች እጅ የመውደቅ አጋጣሚ ከፍተኛ ያደርግዋል።የሶፍትዌር መሀንዲስ እና መምህር የሆኑት አቶ ሶሎሞን አይዳኝ እንደሚሉት ችግሩ በከፊል የሚመነጨው ሰዎች የሚጭኑትን መተግበሪያ ለምን እንደተሰራ እና በአጠቃላይ እንዴት መጠቀም እንዳለብን በትክክክል ለይቶ ካለማወቅ ነው።
ከዚህ አኳያ በስማርት ስልክ አጠቃቀማችን ላይ ስጋት የሚደቅኑ  በጥናት የተረጋገጡ አራት ተግዳሮቶች መኖራቸውን ባለሙያው  ይገልጻሉ። እነዚህ ስጋቶች ከተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አመራረጥ እና አጠቃቀም ከምንጭናቸው አውታረ-መረቦች  ከነፃ የዋይፋይ አጠቃቀምም እና የተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን  በሌላ ሰው ዕጅ መውደቅም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ናቸው። 
በመሆኑም  በግል መረጃዎቻችን ላይ ጥቃት እንዲደርስ የሚያደርጉት  ስጋቶች ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ አጠቃቀም ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ እና መረጃ ሊኖር ያስፈልጋል።ይላሉ አቶ ሰለሞን ።

Äthiopien Ato Solomon Aydagn
ምስል privat

ከዚህ በተጨማሪ ራሳችንን ከመረጃ መንታፊዎች ለመከላከል እና የስማርት ስልካችንን ደህንነት ለማስጠበቅ መተግበሪያዎችን እንደ «ጎግል ፕሌይ ስቶር» እና «አፕ ስቶር» ካሉ ከታማኝ  የማውረጃ ምንጮች በማውረድ መጠቀም።በስማርት ስልካችን ላይ የምንጠቀምባቸው እና በሦስተኛ አካል እንዲታዩ የማንፈልጋቸውን መተግበሪያዎች በአሻራ፣ በፓተርን፣ በይለፍ ቃል፣ በይለፍ ቁጥር፣ በፊት መለያ ወዘተ መቆለፍ፣ ለማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መጠቀሚያ መተግበሪያዎች የ2 ዙር ማረጋገጫ (Two-factor authentication) መጠቀም፣ነፃ የዋይፋይ አገልግሎቶችን ባገኘን ቁጥር ከመጠቀም መቆጠብ  እንዲሁም የምንጠቀምባቸ የይለፍ ቃሎች በቀላሉ የማይገመቱና በየጊዜው መቀያየር አንዱ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።
በስማርት ስልካችን ላይ የምንጠቀምባቸውን መተግበሪያዎች እና የመርጃ ማፈላለጊያዎች(web browser) በየወቅቱ የሚለቀቁ የክፍተት መሙያና ማሻሻያ እድሳቶችን በመከታተል ማዘመን እና ከትክክለኛ ምንጭ የተገኙ ፀረ-ቫይረሶችን መጠቀምም ይመከራል።  
ያ ካልሆነ ግን ከሚሰጡት ጠቀሜታ ይልቅ በሰዎች ላይ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ባለሙያው አስረድተዋል።

Google News | kehrt nach Spanien zurück
ምስል Andre M. Chang/ZUMAPRESS/picture alliance

በሌላ በኩል የኢሜል አጠቃቀም በባህሪው ብዙ ቦታ ሊደርስ የሚችል በመሆኑ ለመረጃ በርባሪዎች  ተጋላጭ ነው።እናም የመረጃ ጠላፊወች (መንታፊዎች) የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም በኢሜል አማካኝነት ከስማርት ስልኮቻችን ላይ መረጃ ለለመንተፍ ሊሞክሩ ይችላሉ። ከዚህ አኳያ ራሳችንን ከመረጃ መንታፊዎች ለመከላከል እንደ አቶ ሰለሞን የምንቀበላቸው ኢሜሎች ከሚታወቅ ምንጭ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። 
በ ኖርተን እና በዳታ ፓርት መረጃ መሰረት በኢሜል ከሚደርስ የመረጃ ስርቆት  91 በመቶው  ተመሳስለው በተሰሩ /Email phishing/ አባሪዎች የሚመጣ ጥቃት ነው።

Symbolbild Fake News Ukraine Krieg
ምስል Andre M. Chang/ZUMA Press Wire/picture alliance

የጥቃቱ አፈፃፀምም  ኢላማ ላደረጉት ሰዉ የተለያዩ ይዘት ኖሯቸዉ ለመክፈት የሚያጓጉ አገናኞች(Links)፣ አባሪዎች (attachments) የያዙ መልዕክቶች  በመላክ እና እንዲክፍት በማድረግ የሚከናወን ነው። ቀጥሎም በከፈተው ኢ-ሜይል ላይ አጥፊ ተልእኮ ባዘሉ አገናኞች አማካኝነት ወደሚፈልጉት አደገኛ ገጽ እንዲገቡ በማድረግ የተጠቃሚውን ሚስጥራዊ መረጃ ለአደጋ ይጋለጣል።የመለያ ቁጥሮችን ፣መታወቂያዎችን፣ የክሬዲት ካርድ፣ የግል እና የገንዘብ መረጃዎችን እንዲያወጡ ሊያታልሉ ይችላሉ።ስለዚህ የሚላኩ ኢሜሎች ከማን? መቼ? ለምን ዓላማ ተላኩ የሚለውን መመርመር ከተጠቃሚዎች ይጠበቃል።
በመሆኑም አላስፈላጊ የሆኑ የኢሜይል መልዕክትን ማጣራት /Filter Spam/ የማይታወቁ ወይም  ወደ የመልዕክት ሳጥን እንዳይገቡ ማገድ፣ ሰዋሰዋዊ ስህተቶች እና የፊደል ግድፈቶች ያሉባቸው ድረ-ገፆችን  አለመጠቀም ተገቢ ነው።በአጋጣሚ መረጃዉ ቢጠፋ ወይም ቢውደም ግን መረጃዎቹን መተካት የሚያስችል የመረጃዎቻችንን መጠባበቂያ (backup) ወይም ምትክ  በማዘጋጀት ማንኛውንም ሚስጥራዊነት ያለው የግል መረጃ በጥንቃቄ መያዝ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ