1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳፋሪኮም ኤም-ፔሳ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ግንቦት 9 2015

ሳፋሪኮም በአፍሪቃ በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት ስኬታማ የሆነውን ኤም-ፔሳ በኢትዮጵያ ሥራ ለማስጀመር ተዘጋጅቷል። የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተቀጥላ ሆኖ የተቋቋመው ኤም-ፔሳ ሞባይል ፋይናንሺያል ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቷል። ሳፋሪኮም ፈቃዱን እጁ ለማስገባት 150 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል።

https://p.dw.com/p/4RVy2
Äthiopien Safaricom Dire Dawa
ምስል Messay Teklu/DW

የሳፋሪኮም ኤም-ፔሳ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ነው

የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፒተር ንዴግዋ ባለፈው ሣምንት የኩባንያቸውን የአንድ ዓመት የፋይናንስ ሪፖርት ከማቅረባቸው በፊት ለተሳታፊዎቹ የሚነግሩት የምሥራች ነበራቸው። በዕለቱ ማለትም ግንቦት 3 ቀን 2015 የፋይናንስ ሪፖርቱን ለማዳመጥ ከታደሙት መካከል የቦርድ አመራሮች፣ ባለወረቶች፣ የሳፋሪኮም ባለድርሻዎች ይገኙበታል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው “ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ሳፋሪኮም ቴሌኮምዩንኬሽን ኢትዮጵያ በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት ለመስጠት በይፋ ፈቃድ አግኝቷል” ሲሉ ታዳሚዎቹ ደስታቸውን በጭብጨባ ገለጹ። 

በናይሮቢ የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይፋ ያደረጉትን የምሥራች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተመሳሳይ ቀን ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል። ከሰባት ወራት በፊት የቴሌኮም አገልግሎት በኢትዮጵያ መስጠት የጀመረው ሳፋሪኮም ይኸን ፈቃድ እንደሚያገኝ በብዙዎች ዘንድ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም በተጨባጭ ተግባራዊ ሲሆን ግን ፒተር ንዴግዋ እና ባልደረቦቻቸው ለባለወረቶች እና ባለድርሻዎች በኩራት የሚያቀርቡት ትልቅ የምሥራች ነበር። 

ሳፋሪኮም የኢትዮጵያ መንግሥት ለቴሌኮም ኩባንያዎች ያወጣውን ጨረታ በግንቦት 2013 ሲያሸንፍ ለፈቃድ 850 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል። ኩባንያው በኢትዮጵያ በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት የሚሰጥበትን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ለማግኘት 150 ሚሊዮን ዶላር እንደከፈለ ፒተር ንዴግዋ ተናግረዋል። ተቋሙ ከዚህ በኋላ ለፈቃድ ተጨማሪ ክፍያ ይፈጽማል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቁጥጥሩም በኬንያ ካለው ጋር ተመሣሣይ እንደሚሆን አስረድተዋል።

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዴት እንደምንሰራ ዝርዝር መመሪያ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ነገር ግን እስካሁን ከተመለከትንው ቁጥጥሩ በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት ከምንሰጥባቸው ሌሎች ገበያዎች ጋር ተመሳሳይ ነው” ሲሉ ፒተር ንዴግዋ ተናግረዋል። 

ከብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ፈቃድ በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ኤም-ፔሳ ከአስራ ስድስት ዓመታት በፊት በየካቲት 1999 የተቋቋመ ነው። ከ40 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን በየወሩ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር ይካሔድበታል። ከኬንያ በተጨማሪ በታንዛኒያ፣ በሌሴቶ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በጋና፣ በሞዛምቢክ እና በግብጽ በሥራ ላይ ይገኛል። 

በተባበሩት መንግሥታት ካፒታል ደቨለፕመንት ፈንድ (UNCDF) የዲጂታል የገንዘብ አገልግሎት ባለሙያው አቶ እንዳሻው ተስፋዬ ኤም-ፔሳ ኬንያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ያዳበረውን ልምድ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲያመራ ከባንክ የራቀውን የሕብረተሰብ ክፍል ለማገልገል ለተወጠነው ብሔራዊ ዕቅድ ስኬት የራሱን ሚና እንደሚጫወት ተስፋ አላቸው።

“ቴሌ-ብር በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት ከጀመረ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የመነቃቃት ሁኔታ አይተናል” የሚሉት አቶ እንደሻው ሳፋሪኮም ኤም-ፔሳን ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ሲያስጀምር በዘርፉ “ሕብረተሰቡ በመረጃ፣ በአጠቃቀም ይበልጥ እውቀቱ እየዳበረ የሚሔድበት” ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

“በ2022 የወጣው የዓለም ባንክ ኢንዴክስ 46 በመቶ የባንክ ደብተር ባለቤትነት እንዳለ ያሳያል” የሚሉት ባለሙያው ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በኋላ የፋይናንስ አገልግሎት አካታችነት 70 በመቶ ለማድረስ ለያዘችው ዕቅድ የሳፋሪኮም ኤም-ፔሳ “ትልቅ ሚና ሊጫወት” እንደሚችል ይጠብቃሉ። 

 Kenia, Nairobi | Mobiles Bezahlsystem M-PESA
ኤም-ፔሳ ከአስራ ስድስት ዓመታት በፊት በየካቲት 1999 የተቋቋመ ነው። ከ40 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን በየወሩ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር ይካሔድበታል። ከኬንያ በተጨማሪ በታንዛኒያ፣ በሌሴቶ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በጋና፣ በሞዛምቢክ እና በግብጽ በሥራ ላይ ይገኛል። ምስል Simon Maina/AFP/Getty Images

ኤም-ፔሳ ከሳፋሪኮም ያለፈው ዓመት አጠቃላይ ገቢ 39 በመቶ ገደማ ድርሻ አለው። በዓመቱ የኤም-ፔሳ ገቢ በ8.8 በመቶ ጨምሮ 117.19 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም 855 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል። አገልግሎቱን በንቃት የሚጠቀሙ ደንበኞች የሚያደርጉት የገንዘብ ዝውውር ካለፈው ዓመት አኳያ በ16.2 በመቶ ከፍ ያለ ነው።

ሳፋሪኮም ከፍተኛ ተስፋ የጣለበትን ይኸን አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመጀመር “እመኑኝ በተቻለው ፍጥነት ወደ ገበያው መግባት እንፈልጋለን” ያሉት ፒተር ንዴግዋ ቅድሚያ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልገው እንደነበር ተናግረዋል። “በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት ለመስጠት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ተቀጥላ ማቋቋም ያስፈልገን ስለነበር ተቀጥላ ኩባንያውን አቋቁመናል። ከባንኮች እና ሌሎች ተቋማት ጋር ውሎች በመፈጸም ላይ የሚገኘው ይኸ ተቀጥላ ኩባንያ ነው” ሲሉ የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል። 

“ሁሉንም የዝግጅት ሥራዎች አጠናቀናል። ስለዚህ ሥራውን ለማስጀመር የሚያስፈልገው ጊዜ ወራት አይወስድም። ሣምንታት ይበቃሉ። ስለዚህ በሁለተኛው ሩብ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በኢትዮጵያ በአገልግሎት መስጠት እንጀምራለን ብዬ እገምታለሁ” ሲሉ ኤም-ፔሳ መቼ ሥራ ሊጀምር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። 

Äthiopien Safaricom Dire Dawa
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ወራት ከ3 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አፍርቷል።ምስል Messay Teklu/DW

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተቀጥላ ሆኖ የተቋቋመው ኤም-ፔሳ ሞባይል ፋይናንሺያል ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ ሲጀምር በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ከተሰማሩ እንደ ቴሌ ብር ካሉ አግልግሎች ግብግብ ይገጥማል። ከሁለት ዓመታት በፊት ማለትም በግንቦት 2013 ሥራ የጀመረው የኢትዮ-ቴሌኮም ቴሌ-ብር ከ32 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አፍርቷል። ከ375 ቢሊዮን ብር በላይ ዝውውር የተፈጸመበት ቴሌ-ብር የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች በገበያው ያለው ድርሻ ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት ላይ ይገኛል። የነዳጅ ግብይት ቴሌ-ብርን በመሳሰሉ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ መንገዶች እንዲፈጸም በቅርቡ የተላለፈው ውሳኔ ለዚህ ተጠቃሽ ነው። በሞባይል ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎችን በቅርበት የሚከታተሉት አቶ እንደሻው በገበያው የሚኖረውን የውድድር መልክ የመወሰን ኃይል አሁንም በመንግሥት እጅ እንደሚገኝ ተናግረዋል።   

ቁጥሮች፦ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሰባት ወራት 
 
ፒተር ንዴግዋ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት የሳፋሪኮም ዓመታዊ ትርፍ ባለፈው የበጀት ዓመት በአምስት እጅ ቀንሷል። በሳፋሪኮም የፋይናንስ ሪፖርት መሠረት እስከ መጋቢት 22 ቀን 2015 ባለው አንድ ዓመት ከወለድ እና ከግብር በፊት የኩባንያው ገቢ 85 ቢሊዮን ሽልንግ ወይም 623 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነበር። ይኸ ከቀደመው ዓመት በ22 በመቶ ዝቅ ያለ ነው። ለኩባንያው ገቢ መቀነስ ዋንኛው ምክንያት በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር ያወጣው ወጪ እንደሆነ ፒተር ንዴግዋ ተናግረዋል። ይኸ በተያዘው የበጀት ዓመትም የሚቀጥል ቢሆንም የሳፋሪኮም ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ በጀመሩት ሥራ ከፍተኛ ተስፋ አላቸው።  

በኩባንያው የ2022/2023 የፋይናንስ ሪፖርት መሠረት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ወራት ከ3 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አፍርቷል። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ይኸን ቁጥር በ2024 ወደ አስር ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ አለው። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሰባቱ ወራት 562.4 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝቷል። ከዚህ ገቢ ውስጥ የሞባይል ዳታ አገልግሎት 63 በመቶ፤ የድምጽ ጥሪ 24 በመቶ ድርሻ አላቸው። 

እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ