1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የሳይበር ምህዳር ጥቃትና ጥበቃ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 22 2015

ቴክኖሎጂ የሰዉ ልጆችን የዕለት ተዕለት ህይወት በማቅለል ረገድና ዓለም አቀፋዊ ትስስርና ቅርርብ በመፍጠር የሚጫወተዉ ሚና ቀላል አይደለም። ይሁን እንጅ ይህ የቴክኖሎጅ አጠቃቀምን ተከትለዉ የመጡ የጎንዮሽ ስጋቶችም የዚያኑ ያህል አሳሳቢ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/3UcSa
Cyber Security Cybersicherheit Datenschutz
ምስል picture-alliance/dpa/R. Hirschberger


 ከነዚህ ስጋቶች መካከል በመረጃ ቴክኖሎጂዉ ዘርፍ የበይነመረብ ግንኙነትን በማወክ የሚታወቀዉ  የሳይበር ጥቃት አንዱ ነዉ።
የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በአብዛኛዉ በይነ-መረብ ላይ የተመረኮዘ ሲሆን የሚደረገዉ መስተጋብርም ከምናባዊዉ  የኮምፒተር ዓለም ጋር የተገናኘ ነዉ።ይህም ምናባዊ የሳይበር ምህዳር በመባልም ይታወቃል።በኢትዮጵያ የገንዘብ ሚንስቴር የመንግስት የተቀናጀ የፋይናንስ መረጃ ስርዓት የሳይበር ደህንነት ቡድን መሪ  አቶ ከድር ዓሊ እንደሚሉት የሳይበር ምህዳር ከበርካታ ነገሮች ጋር ይያያዛል።
  
የሳይበር ምህዳር በተቋምም ይሁን በግለሰብ ደረጃ ተጠቃሚዎች መረጃዎችን ለመጋራት፣ለመዝናናት፣ለመማር፤መስተጋብር ለመፍጠር፣ሀሳብ ለመለዋወጥ ፣በማህበራዊ መድረኮች ዉይይት ለመፍጠር፣ ለንግድ ፣በቀላሉ ተደራሽ የሆኑ የመገናኛ ብዙሃንን  ዘዴዎችን ለማቋቋም ያገለግላል።
ይህ መስተጋብር  በኮምፒተር በተንቀሳቃሽ ስልኮችና በሌሎች የቴክኖሎጅ ዉጤቶች  አማካኝነት የሚደረግ ድንበር የማይገድበዉ፣ ምናባዊና ያልተማከለ ተግባቦት ነዉ።በመሆኑም በግለሰብ፣በተቋማትና በሀገር ደረጃ ለጥቃት የተጋለጠ ነዉ።
የሳይበር ጥቃት ብዙውን ጊዜ በግለሰቦችንም ይሁን በተቋማት እንዲሁም በመንግስታት ትስስሮች  በድብቅ ሰብሮ በመግባት ፣መረጃዎችን መለወጥን ፣ ማበላሸትን ወይም ከተጠቃሚዎች ገንዘብ መዉሰድን ፣መደበኛውን የንግድ ሂደት ማስተጓጎልን ያጠቃልላል።አቶ ከድር እንደሚሉት የጥቃቱ ባህሪም እንደ ጥቃት አድራሹ አካል ዓላማና ፍላጎት ይወሰናል።

Symbolbild Cyberangriff
ምስል Colourbox

ይህ መሰሉ ጥቃት ያለፈዉ ሳምንት መጨረሻ  በሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተሞክሮ እንደነበር  የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታዉቆ ነበር።
ኤጀንሲዉ በኢትዮጵያ  የሚገኙ ቁልፍ  መሰረተ ልማቶችና የፋይናንስ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የሳይበር ጥቃት የመከታተል እና ለሚፈጠሩ ጥቃቶች ምላሽ የመስጠት ስራዎችን እያከናወነ በሚገኘዉ በብሄራዊ የሳይበር ጥቃት የአደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ማዕከል አማካኝነት ጥቃቱ ጉዳት ሳያደርስ  መከላከል መቻሉንም ጠቅሷል።
በፋይናንስ ተቋሞች ላይ የተሰነዘረውን የሳይበር ጥቃት ለማክሸፍም  የበይነ-መረብ (የኢንተርኔት) አገልግሎትን በመላ ሀገሪቱ  ለ20 ደቂቃዎች ያህል ለማቋረጥ ተገድዶ እንደነበር ኤጀንሲዉ አመልክቷል።
 ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን በጦር መሳሪያ ከሚደረገዉ ጦርነት ይልቅ የሳይበር ጥቃቶች እና ዲጂታል የስለላ ስራዎች በሀገራት ብሔራዊ ደህንነት ላይ ትልቅ ስጋት እያሳደሩ ነዉ።ለዚህም ነዉ የሳይበር ጥቃት ጥይት የማይጮህበት ጦርነት ነዉ የሚባለዉ።
በመሆኑም ግለሰቦች፣ መንግስታት ፣ ወታደራዊ ተቋማት ፣ የጤና፣ የገንዘብ፣ የህክምናና  የማምረቻ ድርጅቶች በኮምፒዩተሮቻቸዉና በሌሎች መሳሪያዎቻቸዉ ላይ የሚያከማቹትን በርካታ መረጃዎች  ከጥቃት ለመጠበቅ የሳይበር ደህንነት አስፈላጊ  ነው።ምንም እንኳ የሳይበር ምህዳር በባህሪዉ ተለዋዋጭና በቦታ ያልተወሰነ በመሆኑ ጥቃቱን የመከላከሉ ስራ ቀላል ባይሆንም።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት  አሁን አሁን የኃይል ማመንጫዎችን ሆስፒታሎችንና የገንዘብ ተቋማትንና የማምረቻ ድርጅቶችን በመሳሰሉ ወሳኝ ተቋማትን  ዒላማ ያደረጉ አዳዲስ የአደጋ ተጋላጭነቶችና የጥቃት ስልቶች ብቅብቅ እያሉ ነዉ።በመሆኑም የበይነ መረብ ስርዓቶችን ፣ አውታረ መረቦችን እና ፕሮግራሞችን ከዲጂታል ጥቃቶች መከላከል ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ነዉ።የእነዚህን ድርጅቶች ደህንነት ማረጋገጥ የማኅበረሰቡን ደህንነት ማረጋገጥ ጭምር ነዉና። ከዚህ በተጨማሪም ኅብረተሰቡን ስለ ሳይበር ደህንነት እንዲያዉቅ  በማድረግ  ደህንነቱ የተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀም እንዲኖር ያግዛል።
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን  የሳይበር ጥቃቶች መጠን እና መወሳሰብ እየጨመረ በመምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።ስለሆነም ኩባንያዎች እና ድርጅቶች በተለይም ከብሔራዊ ደህንነት ፣ ከጤና ወይም ከገንዘብ ነክ መዛግብቶች ጋር በተያያዘ መረጃ እንዲይዙ ኃላፊነት የተጣለባቸዉ ሰዎች የተሳካ  የንግድ ሥራ ለማካሄድ እንዲሁም የደንበኞቻቸዉንና የሰራተኞቻቸውን መረጃ ለመጠበቅ ጥንቃቄ ማድረግ  እንደሚጠበቅባቸዉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።ለዚህም ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ለመከላከልና ከደረሰም ለማገገም የሚያስችል በዘርፉ በማዕቀፍ የሚመራ የሰለጠነ የሰዉ ሀይል ማብቃት ወሳኝ ነዉ።
ችግሩ በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑም በትምህርት ቤቶችና በዩንቨርሲቲዎች መረጃዎችን ከነጣቂዎች እንዴት መከላከል እንደሚቻል ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የቴክኖሎጅ ትምህርት በየደረጃዉ  መስጠት እንዳለበት ባለሙያዉ ያሳስባሉ።
በሀገር ደረጃም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኤለክትሮኒክስ ግብይትን ለመጀመር በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መጥተዉ ከነበሩት ቻይናዊ ቱጃር ጃክ ማ ጋር ስምምነት አድርጋለች። በሀገሪቱ በግለሰብና በተቋማት ደረጃም  የዲጂታል ቴክኖሎጅ አጠቃቀም  ከጌዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ይነገራል።በመሆኑም ይህንን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሳይበር ደህንነት ስራ የሀገሪቱ ሌላዉ የቤትስራ ነዉ። 
የሳይበር ደህንነት ባለሙያዉ አቶ ከድር ዓሊ እንደሚሉት ተጠቃሚዎች የመረጃ ሀብቶቻቸዉን ከጥቃት ለመጠበቅ በቀላሉ ሊሰበሩ የማይችሉ ጠንካራ የይለፍ ቃሎችን መምረጥ ፣ ከማይታወቁ  የኢሜል አድራሻዎች የሚመጡ መልዕክቶቻችንና አባሪዎችን  በዘፈቀደ ከመክፈት ይልቅ  ጥንቃቄ ማድረግንና መረጃዎችን በሌላ አማራጭ ቦታ ማስቀመጥን የመሳሰሉት መሰረታዊ የመረጃ መርሆዎችን መገንዘብና ማክበር አለባቸዉ።
ያልታወቁ አዉታረ መረቦችን ከመጎብኜት መቆጠብ  ፣ነፃ የበይነ መረብ ጨዋታዎችንና የመዝናኛ ድህረ ገፆች አጠቃቀም ላይም ጥንቃቄ ማድረግ መረጃወቻችንን ከጥቃት ለመጠበቅ እንደሚያግዙ ባለሙያዉ ጨምረዉ ገልጸዋል።

Sommercamp GenCyber NSA
ምስል picture alliance/landov
Symbolbild Hacker -Cyberangriff
ምስል Imago/Reporters

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።