1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲዳማ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ጥሪ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 25 2014

በዘንድሮ የበልግ ወቅት የዘሩት የበቆሎና የቦሎቄ ማሳ በዝናብ መጥፋት የተነሳ ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን የጠቀሱት አርሶአደሮቹ ‹‹ በዚህም የተነሳ ቀደም ሲል ሃያ ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ ኪሎ በቆሎ ዋጋ አሁን ላይ አርባ ብር በመግባቱ ቤተሰቦቻችንን ሸመተን ለመመገብ እንኳን ተቸግረናል፡፡ የእርዳታ ድጋፉ ተጠቃሚም መሆን አልቻልንም ›› ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4GHgf
Äthiopien | Sidama Region sucht humanitäre Hilfe
ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

የሲዳማ ክልል ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ ጥሪ

በሲዳማ ክልል ባጋጠመው የዝናብ እጥረትና መቆራረጥ በ25 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በነበረ የበቆሎና  የቦሎቄ ማሳ ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዝናብ እጥረቱ የተነሳ በክልሉ ከሚገኙት 31 ወረዳዎች መካከል በ15 ቆላማ ወረዳዎች ላይ የድርቅ አደጋ ማጋጠሙን የቢሮ ሃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በወረዳዎቹ 426 ሺህ ነዋሪዎች በድርቅ አደጋው የተነሳ የመንግሥትና የረድኤት ድርጅቶችን እጅ ለማማተር መገደዳቸውን ነው አቶ መስፍን ለዶቼ ቬለ DW የተናገሩት ፡፡

ክልሉ ከፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ከዓለምአቀፉ የረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን የድርቁን ሥፋት ፣ የተረጂዎችን ቁጥርና የሚያስፈልገውን የድጋፍ መጠን መለየቱን ሃላፊው አስረድተዋል፡፡

እስከአሁን ለተረጂዎቹ በሁለት ዙር የምግብ አቅርቦት መደረጉን የጠቀሱት ሃላፊው የቀጣይ ዙር ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሰብላቸው በዝናብ እጥረት እንደጠፋባቸው ለዶቸ ቬለ DW የገለፁት በክልሉ በንሳ ወረዳ የሁሉቃ ቀበሌ ነዋሪ ነን ያሉ አርሶአደሮች በበኩላቸው እየቀረበ ይገኛል የተባለው እርዳታ በሁሉም ቦታ እየደረሰ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

Äthiopien | Sidama Region sucht humanitäre Hilfe
ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

በዘንድሮ የበልግ ወቅት የዘሩት  የበቆሎና የቦሎቄ ማሳ በዝናብ መጥፋት የተነሳ ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን የጠቀሱት አርሶአደሮቹ ‹‹ በዚህም የተነሳ ቀደም ሲል ሃያ ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ ኪሎ በቆሎ ዋጋ አሁን ላይ አርባ ብር በመግባቱ ቤተሰቦቻችንን ሸመተን ለመመገብ እንኳን ተቸግረናል፡፡ መንግሥት በወረዳችን የምግብ እርዳታ እያቀረበ ቢገኝም የቀረበው መጠን አነስተኛ በመሆኑ ሁላችንም የድጋፉ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ›› ብለዋል፡፡

በክልሉ የምግብ ድጋፉ በሁሉም ቦታ እየደረሰ አይደለም በሚል በተረጂዎቹ በቀረበው ቅሬታ ዙሪያ በዶቼ ቬለ DW የተጠየቁት የክልሉ ግብር ቢሮ ሃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በአንዳንድ ወረዳዎች በፌዴራሉ መንግሥት እየቀረበ የሚገኘው ድጋፍ  ለሁሉም ተረጂዎች ያልተዳረሰበት ሁኔታ እንዳጋጠመ እናውቃለን ብለዋል ፡፡

አቶ መስፍን አክለውም ‹‹ ድጋፉን ለማዳረስ የክልሉ መንግሥት ከራሱ ካዝና 50 ሚሊዮን ብር በመመደብ ክፍተቱን እየሸፈነ ይገኛል፡፡ በእኛ በኩል በክልላችን አንድም ሠው በረሀብ ምክንያት መሞት የለበትም የሚል አቋም ይዘን እየሠራን እንገኛለን፡፡ የምግብ ድጋፉ አቅርቦቱ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ድጋፉን ለማድረስ እየሠራን እንገኛለን ›› ብለዋል፡፡

በዝናብ እጥረት ለተረጂነት የተዳረጉ ነዋሪዎችን በቀጣይ በዘላቂነት ለማቋቋም ምን እየተሠራ ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም አቶ መስፍን ሲመልሱ ‹‹ አሁን ላሉት ተረጂዎች የምግብ ድጋፉ እያቀረብን የምንቀጥልበት ሁኔታ መኖር የለበትም ፡፡ ነዋሪዎች ከችግራቸው ወጥተው እንደበፊቱ ራሳቸውን እንዲመግቡ እየሠራን እንገኛለን ፡፡ ክልሉ ተረጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በክልሉ መንግሥት ካቢኔ አማካኝነት 47 ሚሊዮን ብር መድቧል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ማሳቸው ለተጎዳባቸው አርሶአደሮች የበቆሎና የቦሎቄ የማካካሻ ዘር እየተሠራጨ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ