የሱዳኖች ድርድርና ዉጤቱ
ሐሙስ፣ መስከረም 10 2005
በጠብ የሚፈላለጉት የሰሜን እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንቶች የፊታችን ዕሁድ አዲስ አበባ ዉስጥ ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል።ሁለቱ ፕሬዝዳቶች ፊትለፊት ለመነጋገር መፍቀዳቸዉ ጦር ያማዘዘዉን ልዩነት ለማጥበብ በተከታታይ የተደረገዉ ድርድር አግባቢ ደረጃ የመድረሱ ምልክት ተደርጎ ነዉ የታየዉ።የድርድሩን ሒደት የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች እንዳስታወቁትም ተደራዳሪዎች በተለይ የድንበር መካለልን እና የነዳጅ ዘይት ሐብት ክፍፍልን በተመለከተ ከተጠበቀዉ በላይ ተቀራርበዋል።ያም ሆኖ አሁንም በሁለቱ ወገኖች መሐል ሙሉ መተማመን አይታይም።
ባለፈዉ ሚያዚያ ያዋጋቸዉ የሁለቱ ሱዳኖች ልዩነት ብዙ ነዉ።የድንበር ግዛት ይገባኛል፥ የነዳጅ ዘይት ሐብት፥ አንዱ የሌላዉን ተቃዋሚ ወይም አማፂ ቡድን መርዳት፥ የዜግነት--- እያለ አንዱ ሲነካ ሌላዉ አብሮ የሚመዘዝ ብዙ እና ዉጥንቅጥም ነዉ።ሱዳኖች ዉጥንቅጡን ጠብ እንዲያስወግዱ የአፍሪቃ ሕብረት ከመሸምገል፥ ምዕራባዉያን ከማስጠንቀቅ፥ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቀን ከመቁረጥ አልቦዘኑም።
አዲስ አበባ ላይ የተያዘዉን ድርድርን የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች ካለፈዉ ማክሰኞ ጀምሮ እንዳስታወቁት ግን ተደራዳዊዎች ሌላዉ ቢቀር ድንበር መካካለልንና የነዳጅ ዘይት ሐብት ክፍፍልን በሚመለከት እስከዚሕ ሳምንት ድረስ የያዙትን የተራራቀ አቋም ወደ ማቀራረቡ አዘንብለዋል።
ዛሬ ደግሞ የሁለቱ ሐገራት መሪዎች የፊታችን ዕሁድ አዲስ አበባ ዉስጥ ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ለመነጋገር መወሰናቸዉ ተሰምቷል።የፀጥታ ጥናት ተቋም-ISS በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኝ ዶክተር ጂዲ ማርቲንስ ኦኬኬ እንደሚሉት ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ፊትለፊት ለመነጋገር መወሰናቸዉ እጅግ የተወሳሰበዉን ልዩነት ለማጥበብ በጣም ጠቃሚ እርምጃ ነዉ።
«የሁለቱ ፕሬዝዳንቶች መገናኘት በጣም ጠቃሚ ነዉ።በተለይ ሁለቱን ሐገራት በጣም የሚያወዛግበዉን የድንበር ችግርን ለማቃለል በጣም ይጠቅማል።የድበሩ ዉዝግብ የተካረረዉ አወዛጋቢዉ ግዛት ነዳጅ ዘይት የሚመረትባቸዉን አንዳድ አካባቢዎችን የሚያካትት በመሆኑ ነዉ።»
ከአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ደቡብ ሱዳን ነፃነትዋን ስታዉጅ በይደር የተተወዉ የአብዬ ግዛት አንዱ ምናልባትም ትልቁ ነዉ።እስካሁን በተደረገዉ ድርድር ድንበርን በማካለሉ ረገድ መግባባት የተደረሰበት ግዛት የትነት፥ የማካለሉ ሒደት እንዴትነት ላሁኑ በሚስጥር እንደተያዘ ነዉ።
የደቡብ ሱዳን የገንዘብ ሚንስትር ኮስቲ ማኒቢ ንጋዪ እንዳስታወቁት ግን ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አል-በሽርና ፕሬዝዳት ሳል ቫኪር በመጪዉ ዕሁድ አዲስ አበባ ዉስጥ የሚያደርጉት ዉይይት ሁለቱን ሐገራት ከሁነኛ ዉል ማድረሱ አይቀርም።
ዉሉ ከተፈረመ ደግሞ ሚንስትሩ እንደሚሉት ደቡብ ሱዳን ምርትና ሽያጩን በማቆሟ የሁለቱንም ሱዳኖች በጣሙን የራስዋን የደቡብ ሱዳንን ካዝና ወና ያስቀረዉ ነዳጅ ዘይት ለሽያጭ ዳግም ይቀዳል።
«የአፍሪቃ ሕብረት አደራዳሪዎች አዲስ በቆረጡት ጊዜ መሠረት ስምምነቱን ለመፈረም መስከረም ሃያ-ሰወስት የመጨረሻ ስብሰባ ይደረጋል።ይሕ ከሆነ በሰወስትና አራት ወራት ዉስጥ ነዳጅ ዘይት ዳግም ማምረት ይጀመራል።»
የገንዘቡ ችግር፥ የዉጪዉ ግፊት፥ የአደራዳሪዎች ጥረትም ተደማምረዉ ሁለቱ ሱዳኖች አሁን ከደረሰቡበት መድረሳቸዉ ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሱዳኖች አልፎ ላካባቢዉም ሠላም ጠቃሚ ነዉ።ይሕ ማለት ግን ዶክተር ኦኬኬ እንደሚሉት ጠብ ቁርቁሱ አበቃ ማለት አይደለም።
«ታቦ ኢምቤኪ በሚመሩት የሱዳን የአደራዳሪዎች ቡድን አማካይነት ሠፊ ድርድር ቢደረግም፥ ድርድሩ ባንድ ወይም በሌላ ወገን ከስምምነት ይደርሳል ተብሎ ቢታሰብም፥ አሁንም ብዙ አጠራጣሪ ጉዳዮች አሉ።በሁለቱ ወገኖች መሐል መተማመን ገና አልሰፈነም።በዚሕም ምክንያት መሪዎቹ ለመሠረታዊ ስምምነት የሚያበቃ ዉሳኔ ማሳለፋቸዉን አጠያያቂ ያደርገዋል።»
ሁለቱ መሪዎች አዲስ አበባ ላይ የሚወያዩት ሱዳኖች ልዩነታቸዉን በድርድር እንዲያስወግዱ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ የሰጠዉ ቀነ-ገደብ ባበቃ ማግስት መሆኑ ነዉ።ዕሁድ።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ