1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ጦርነት፣ የሰላማዊ ሰዎች ፍዳ፣ የኬንያ መሪዎች አንድነት ፍፃሜ

ቅዳሜ፣ መስከረም 25 2017

ባለፈዉ ሳምንት ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን መከላከያ ጦር ርዕሰ ከተማ ካርቱም ዉስጥ በከፈተዉ ጥቃት የፈጥኖ ደራሽ ጦር ይቆጣጠራቸዉ የነበሩ ሥልታዊ አካባቢዎችን መልሶ መቆጣጠሩን አስታውቋል።የካርቱም ሥልታዊ አካባቢዎችን ለመያዝና ላለማስያዝ በተደረገዉ ዉጊያ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል

https://p.dw.com/p/4lQhL
አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን ጦር ኃይል በቅርቡ የርዕሰ ከተማ ካርቱም ሥልታዊ አካባቢዎችን ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል መማረኩን አስታዉቋል
የሱዳን ወታደራዊ ገዢና የሐገሪቱ ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን።ጦራቸዉን ለተጨማሪ ዉጊያ ሲያዘጋጁምስል AFP

የሱዳን ጦርነት፣ የሰላማዊ ሰዎች ፍዳ፣ የኬንያ መሪዎች አንድነት ፍፃሜ

 

የሱዳን ጦርነት፣ የሐገሪቱ ሕዝብ ረሐብና እልቂት 

አብዛኛዉ ዓለም የጋዛ፣የዩክሬን፣በቅርቡ ደግሞ የሊባኖስ ጦርነት ላይ አተኩሮ የእስራኤል-ኢራን ቁርቁስ የሚያስከትለዉን መዘዝ ሲያወጣ-ሲያወርድ አፍሪቃዊቱ ሱዳን ከሐገርነት ወደ እልቂት ማዕከልነት እየዘቀጠች ነዉ።ሐቻምና ሚያዚያ  ርዕሰ ከተማ ካርቱም ላይ የተጀመረዉ የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት አብዛኛዉ የሐገሪቱን ክፍል አዳርሷል።ጦርነቱና ጦርነቱ ያስከተለዉ ረሐብ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ገድሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት (WHO) እንደሚለዉ ዓመት ከመንፈቅ በደፈነዉ ጦርነት የተገደለዉ ሕዝብ ከ20 ሺሕ ይበልጣል።ሌሎች የርዳታ ድርጅቶች እንደሚገምቱት ግን የሞተዉ ሕዝብ ቁጥር ከ150 ሺሕ ቢበልጥ እንጂ አያንስም።ከሱዳን ሕዝብ ከግማሽ የሚበልጠዉ ወይም ከ25 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አንድም ተሰድዷል አለያም ተፈናቅሏል።
ቻድ፣ ግብፅ፣ ዩጋንዳና በሌሎች የአካባቢዉ ሐገራት የተጠለሉ ስደተኞች በቂ ባይባልም ረሐብና በሽታን የሚያስታግሥ ርዳታ ማግኘታቸዉ አልቀረም።ወደ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ሱዳናዉያን ግን በሰፈሩትም አካባቢ ግጭትና ጥቃት አልተለያቸዉም።የርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እንደሚሉት እዚያዉ ሱዳን ዉስጥ በየሥፍራዉ የተጠለሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ርዳታ ሥለማይደርሳቸዉ ለምግብ እጥረትና ለረሐብ ተጋልጠዋል። 

የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት የምሥራቅ ሜድትራኒያን አካባቢ የበላይ ኃላፊ ሪክ ብሬናን በቅርቡ እንዳሉት ከ25 ሚሊዮን የሚበልጥ የሱዳን ሕዝብ ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጧል።
«በመላ ሐገሪቱ 25 ሚሊዮን ከግማሽ የሚሆን ሕዝብ  የከፋ የምግብ እጥረት አጋጥሞታል።በቂ ምግብ የምግብ የሚያገኝ የለም።በጣም የከፋዉ ደግሞ እንደምትገምቱት ኮርዶፋን፣ ዳርፉር፣ ካርቱም፣ ከዳርፉር ደግሞ ዘምዘም መጠለያ የሠፈረዉ ሕዝብ ነዉ።በነዚሕ አካባቢዎች የሚኖርና የሠፈረዉ ተፈናቃይ (ከምግብ እጥረት አልፎ) በረሐብ እየተሰቃየ ነዉ።»

አንዳድ አካባቢዎች በረሐብና የምግብ እጥረት በሚያስከትለዉ በሽታ አዛዉንቶችና ሕፃናት መሞታቸዉ ተዘግቧል።ኸሊል ግን ለጊዜዉ ተርፏል።5 ወይም 6 ዓመት ቢሆነዉ ነዉ።በሚኖርበት ቀበሌ ዉጊያ ሲጫር እናት የቻለችዉን የቤት ቁሳቁስ ተሸከማ የኸሊልን እጅ ይዛ እግሯ ወደ መራት ትሮጥ ያዘች።
«እጁን ይዤ ስሮጥ ወደቀ።ሆዱን ድንጋይ መታዉ።»

ኸሊልና እናቱ  በቅርቡ ኮርዶፋን ግዛት ከሚገኝ ባንድ ወቅት «ሆስፒታል» ይባል ከነበረ፣ሐኪምም፣ መድሐኒትም፣ መኝታም ብዙ ከሌለዉ ሐኪም ቤት ደርሰዋል።ሐኪም ቤቱ ከመድረሳቸዉ በፊት ግን ምግብ፣ መድሐኒታቸዉ ቅጠል ነበር።
«የዛፍ ቅጠል ነበር የሚመገበዉ።ለሰዉ የሚሆን ምግብ የለም።ለጤናሕ መጥፎ ቢሆንም ያገኘኸዉን ነዉ የምትበላዉ።ማድረግ የምንችለዉ ከዛፍ ላይ ቅጠሉን እንቀነጥባለን።ሆዳችን እንዲፈጨዉ ቀቅቀለን እንበላዋለን።ሰዉ የሚበላዉ ምግብ የለም።»
 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «ጭፍጨፋ» ያለዉ ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።
ሱዳን ርዕሰ ከተማ ካርቱም ዉስጥ በቅርቡ በተደረገዉ ዉጊያ በርካታ ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል።አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸዉምስል Rashed Ahmed/AP Photo/picture alliance

የርዳታ አቅርቦቱ መሻሻል፣ የዉጊያ መቀጠል

በሱዳን የዩናይትድ ስቴትስ መልዕክተኛ ቶም ፔሪሎ ባለፈዉ ሰኞ እንዳስታወቁት ለሱዳን ተፈናቃዮችና ችግረኞች የሚላከዉ ርዳታ መጠነኛ መሻሻል ታይቶበታል።ተፋላሚ ኃይላት የርዳታ ቁሳቁስ እንዳይደርስ አንዳድ አካባቢዎች ላይ የጣሉትን እገዳና ርዳታ የጫኑ ካሚዮኖችን ማጥቃት ወይም መዝረፋቸዉን ቀንሰዋል።ፔሪሎ እንደሚሉት ተፋላሚዎች ከዚሕ ቀደም እርዳታ እንዳይርሰዉ ባገዱባቸዉ አካባቢዎች በመቶ የሚቆጠሩ ርዳታ የጫኑ ካሚዮኖች ሰሞኑን መግባት ችለዋል።ይሁንና አሜሪካዊዉ ዲፕሎማት አሁንም ቢሆን «እጅግ አሳሳቢ» ያሉት የሰላማዊ ሰዎች ስቃይና ረሐብ እንዲቃለል ተፋላሚዎች ጦርነቱን ለማቆም እንዲደራደሩ አደራ ብለዋል።

ጦርነቱ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን መከላከያ ጦር ርዕሰ ከተማ ካርቱም ዉስጥ በከፈተዉ ጥቃት የፈጥኖ ደራሽ ጦር ይቆጣጠራቸዉ የነበሩ ሥልታዊ አካባቢዎችን መልሶ መቆጣጠሩን አስታውቋል።የካርቱም ሥልታዊ አካባቢዎችን ለመያዝና ላለማስያዝ በተደረገዉ ዉጊያ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «ጭፍጨፋ» ያለዉ ርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።

በምሥራቅ ሜድትራኒያን አካባቢ የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ ሪክ ብሬናን እንደሚሉት ዉጊያ በቀጠለ ቁጥር በጦርነቱ በቀጥታ ከሚያልቀዉ ሕዝብ በተጨማሪ በየመጠለያ ጣቢያዉ የሚራብና የሚሞተዉም ሰዉ ቁጥር መጨመሩ አይቀርም።

«በጣም ዝቅተኛ ርዳታ የሚደርሳቸዉና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸዉ ኮርዶፋንና ዳርፉርን የመሳሰሉት ግዛቶች ናቸዉ።15 ከመቶ የሚሆኑት ሕፃናት ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።ከነዚሕ ዉስጥ ከ30 ከመቶ የሚበልጡት ደግሞ ተርበዋል።ሊደርስባቸዉ በማይቻል ወይም ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ በሆኑት በነዚሕ ግዛቶች ከ60 እስከ 80 ከመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች ጨርሶ አይሰሩም ወይም የሚሰሩት ከግማሽ ባነሰ አቅማቸዉ ነዉ።»

የሱዳን ጦር ኃይልና ሐምዲቲ የሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ጦር የገጠሙት ዉጊያ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሱe ጦርአዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሕዲቲ)።ዳግሎ የሚመሩት ጦር ከሱዳን መከላከያ ጦር ኃይል ጋር በገጠመዉ ዉጊያ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።ሚሊዮኖች ተሰደዋል።ተፈናቅለዋልምምስል Ashraf Shazly/AFP

የሱዳንን የመንግሥትነት ሥልጣንን የያዘዉን የሐገሪቱን ጦር ኃይልና ዋና ጠላቱን የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪዎችን ለማደራደር ኢጋድ፣ የአፍሪቃ ሕብረት፣ አረቦች፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሳዑዲ አረቢያ በተደጋጋሚ ያደረጉት ሙከራ እስካሁን ለዉጤት አልበቃም።ዐለምም የሱዳንን ፋይል በይደር አስቀምጦ ባሁኑ ወቅት መካከለኛዉ ምሥራቅና ዩክሬን-ሩሲያ ላይ ሲባትል ሰፊ፣ጥንታዊ፣ የዳበረ ባሕል ባለቤቲቱ ሐገር ሱዳንን ጄኔራሎቿ በለኮሱት እሳት መጠበሷን ቀጥላለች።
 

የኬንያ መሪዎች ወዳጅነት ፈረሰ

የሱዳን ፖለቲከኞች በቦምብ-አፈሙዝ ሕዝባቸዉን ሲያስፈጁ፣ የኬንያ ፖለቲከኞች የቤተ-መንግስት ፍትጊያ ገጥመዋል።መጀመሪያ ኢትዮጵያዉያንን ቀጥሎ ሱዳኖችን ለማስታረቅ ብዙ የባተሉት የናይሮቢ ፖለቲከኞች የጎርፍ መቅሰፍት፣ ሕዝባዊ ቁጣና የአደባባይ ሰልፍ-ግድያ ያደረሱትን ኪሳራ ገና በቅጡ ሳያሰሉ የፖለቲካ ትንቅንቅ መግጠማቸዉ እንደ ጎረቤቶቻቸዉ ከመተላለቅ ቢሻልም ለብዙዎች አስገራሚ አነጋጋሪም ሆኗል።
ነገሩ እንዲሕ ነዉ።የኬንያ ምክትል ፕሬዝደንት ሪጋዚ ጋሻጉዋ የመንግሥት ደንብና ሕግን ጥሰዋል፣ በሙስና ተዘፍቀዋል፣ ሕዝብን በጎሳ የሚከፋፍል ፖለቲካ አራምደዋል እና ሌሎችም ክሶች ተዘርዝሮባቸዋል።የኬንያ ምክር ቤት የሐገሪቱን ሁለተኛ ትልቅ ፖለቲከኛን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት ሲከራከር ሰንብቷል።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በጋሻጉዋን የሥልጣን ሕልቅት ላይ መጠቅለል የጀመረዉ የሴራ ገመድ መተርተር የጀመረዉ ከፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ቢሮ ነዉ።ገመዱ የሩቶን ቢሮ፣ የሐገሪቱን ካቢኔ፣ፍርድ ቤቶች አልፎ ምክር ቤት ዉስጥ እየተሸረበ ነዉ።የሁሉም መነሻ ግን አምና ሚያዚያና ግንቦት ሕዝብን በጣሙን ወጣቱን አስቆጥቶ ናይሮቢ ላይ ደም ያስፈሰሰዉ የኑሮ ዉድነትና የግብር ጭማሪ ዕቅድ ነዉ።
«ከተቃዉሞ ሰልፉ በኋላ፣ የፖለቲካ ካራ መሐል ገብቶ ፕሬዝደንቱን ከምክትላቸዉ አቆራረጣቸዉ» ይላሉ የናይሮቢዉ የፖለቲካ ተንታኝ  ማርቲን ኦሉ።
«ያሁኑን ሙቀት ያቀጣጠሉት ፖለቲካዊዉ መሠረቶች የጂን ዚ ወይም የተቃዉሞ ሰልፎቹ  ናቸዉ።በምክትሉና በዋናዉ መካከል ሰርስሮ የገባዉ የፖለቲካ ካራ ሁለቱን ለያያቸዉ።»
የወጣቶች የሲቢል ቴክኖሎጂ የተባለዉ ተቋም የበላይ ኃላፊ ኔሪማ ዋኮ-ኦጂይዋ እንደሚሉት ደግሞ የሩቶና የጋሻጉዋ ወዳጅነት ወትሮም ዳር የሚዘልቅ አልነበረም።ኦጂይዋ እንደሚሉት ሮቶ ለፕሬዝደትነት በሚወዳደሩበት ወቅት ጋሻጉዋን በምክትልነት ያስከተሉት ሰዉዬዉ ሐብትም፣ የሕዝብ ድምፅም እንዲያመጡላቸዉ አስበዉ ነበር።
የደጋፊዎች ግጭት 

የፕሬዝደንት ሩቶና የምክትል ፕሬዝደንት ጋሻጉዋ ወዳጅነት ፈርሶ፣ ሁለቱ ፖለቲከኞች እንደ ጠላት እየተነቃቀፉ ነዉ
ነበር።ከግራ ወደ ቀኝ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶና ምክትላቸዉ ሪጋዚ ጋሻጉዋ የኬንያን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ባሸነፉ ሰሞንምስል Simon Maina/AFP

ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የሁለቱ ፖለቲከኞች ፍቅር ወደ ጠብ ተቀይሯል።ምክትል ፕሬዝደንቱ «ይከሰሱ አይከሰሱ» በሚለዉ ሐሳብ ላይ የሐገሪቱ ሕዝብ ትናንት በየአዉራጃዉ ያደረገዉ ክርክርም ወደ ግጭትና ጠብ ተለዉጧል።ናይሮቢ፣ ንያንዳሩዋ፣ ንየሪና በሌሎች አካባቢዎች በተጠራዉ ስብሰባ ላይ የተገኘዉ ሕዝብ  የሩቶና የጋሻጉዋ ደጋፊዎች በሚል ለሁለት ተከፍሎ በወንበር፣ መጥረጊያና በሌላ ቁሳቁስም ሲደባደብ ነዉ የዋለሁ።

የጋሻጉዋ ደጋፊዎች እንደሚሉት ምክትል ፕሬዝደንቱ ወንጀለኛ ከሆኑ ዋናዉም ወንጀለኛ ናቸዉ።ፕሬዝደንት ሩቶ በአርቡ ሕዝባዊ ዉይይትም ሆነ ከዚያ በፊት በተደረጉ ክርክሮች ምክትላቸዉን ባደባባይ አልነቀፉም።ዉስጥ ዉስጡን ግን፣ የፖለቲካ ተንታኝ ማርቲን ኦሉ እንደሚሉት ሩቶና ወዳጆቻቸዉ ጋሻጉዋን የማጥላላቱን ዘመቻ ሲያቀለጣጠፉ ነበር።
«ምክትሉ በጣም እየተጠናከሩ ነዉ፣ አለቃቸዉን ይንቃሉ፣ እንዳሻቸዉ ናቸዉ፣ አለቃቸዉን አያከብሩም ሲባል ነበር።»
የ59ኝ ዓመቱ ጋሻጉዋ ቱጃር ነጋዴ ናቸዉ።ነጋዴነታቸዉ ለሙስና ያጋልጣቸዋል የሚል ጥርጣሬ አለ።ካጣ-ከነጣ ቤተሰብ የተወለዱትን ሩቶን ናቅ፣ገለል ያደርጋሉ ቢባልም ያስኬድ ይሆናል።ይሁንና ሩቶም ዋዛ አይደሉም። መሰሪ ብጤ ናቸዉ።አዲሱ ስልታቸዉ ከጋሻጉዋ ጋር የበራቸዉን ያላቻ ጋብቻ አፍርሰዉ ከተቃዋሚዉ ከራይላ ኦዲንጋ ጋራ መወዳጅት ነዉ እየተባለ በሰፊዉ ይነገራል።

የሩቶ አማራጭ
አንጋፋዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ ለአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደትንት እንዲወዳደሩ ሩቶ አጭተዋቸዋል።አምና በተከታታይ ከተደረገዉ የተቃዉሞ ሰልፍ በኋላ የኦዲንጋ ፓርቲ ፖለቲከኞች የሩቶን አቋም ደግፈዉ መንግስትን ተቀይጠዋል።
የምክትል ፕሬዝደንት ጋሻጉዋን ለመክሰስ የሐገሪቱ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት እስካሁን ባደረገዉ ክርክር 191 የምክር ቤት እንደራሴዎች የጋሻጉዋን መከሰስ ደግፈዋል።ምክትል ፕሬዝደንቱን ለመክሰስ የሚያስፈልገዉ ድምፅ 171 ነዉ።የኬንያ ፍርድ ቤት ሒደቱን እንዲያስቆም ጋሻጉዋ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ጥያቄዉን አልተቀበለዉም።

የሐገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የፊታችን ማክሰኞ ድምፅ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ።ጋሻጉዋ ሥልጣን ላይ የመቆየታቸዉ ነገር ያበቃለት ይመስላል።የፖለቲካ ተንታኝ ኦሉ እንደሚሉት ሩቶ ጋሻጉዋን አስወግደዉ፣ ደጋፊዎቻቸዉን አስኮርፈዉ  ከራይላ ኦዲንጋና ከፓርቲያቸዉ ጋር አዲስ ወዳጅነት ለመመስረት የሚያደርጉት ጥረት ግን የኬንያን ፖለቲካ በነበረበት እንዲረግጥ ከማድረግ ባለፍ የሚፈይደዉ የለም።
«የሐገሪቱ የተወሰኑ ክፍሎች ለፕሬዝደንት ሩቶ የሚሰጡትን ድጋፍ ነፍገዉ ዳግም ሥልጣን ለመያዝ ትግል መግጠማቸዉ አይቀርም።ይሕ ደግሞ የኬንያን ፖለቲካ ከተመሳሳይ አዙሪት ዉስጥ ይከትተዋል።ለዚሕም ነዉ ምርጫ ለማድረግ ገና ሶስት ዓመት ሲቀረዉ፣ አስተማማኝ የምርጫ ኮሚሽን ሳይኖረን  የፖለቲካ ጠመንጃን መምዘዝ በጣም አሳሳቢ ምናልባትም ፖለቲካዊ የዋሕነት ነዉ።»
ያም ሆነ የኬንያ ፕሬዝደንቶች ከምክትሎቻቸዉ ጋር ሲቃቃሩ ያሁኑ የመጀመሪያቸዉ አይደለም።ፕሬዝደንት ዳናኤል አራፕ ሞይ እና ምዋዊ ኪባኪ ሶስት ሶስት ምክትል ፕሬዝደንቶችን ቀያይይረዋል።ሩቶ ራሳቸዉ ባንድ ወቅት እንዳሉት ከፕሬዝደትከኡሁሩ ኬንያታ ጋር እንደ ምክትል ፕሬዝደንት የቆዩት መገለል፣መንጓጠጥ፣ መገፋቱን ዋጥ አድርገዉ ችለዉ ነዉ።

ምክትል ፕሬዝደንቱን ለመክሰስ ወይም ከሥልጣን ለማዉረድ ከምክር ቤቱ አባላት የ171ዱ ድምፅ በቂ ነዉ
ከኬንያ የምክር ቤት እንደራሴዎች 191ዱ የሐገሪቱ ምክትል ፕሬዝደንት ሪጋዚ ጋሻጉዋ ያለመከሰስ መብታቸዉ እንዲገፈፍ ይፈልጋሉ።ምስል James Wakibia/ZUMAPRESS.com/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ