1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታጠቁ ኃይሎች የሰገን ከተማን መቆጣጠራቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገለፁ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2016

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን የታጠቁ ኃይሎች የሰገን ከተማን መቆጣጠራቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡ ታጣቂዎቹ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ አካባቢውን ለመቆጣጠር ፈጸሙት በተባለው ጥቃት የፓሊስ አባላትን ጨምሮ በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸውን የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4jjpq
የፈረሰ ቤት
ታጣቂዎቹ አካባቢውን ለመቆጣጠር ፈጸሙት በተባለው ጥቃት ንብረትም አውድመዋልምስል Privat

በኮንሶ ዞን በታጣቂዎች ቢያንስ 12 ሰዎች ተገደሉ

ዳግም ያገረሸው የኮንሶ አካባቢ ግጭት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ መረጋጋት እንደራቀው ይገኛል ፡፡ የታጠቁ ቡድኖች ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ሰገን በመግባት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል ፡፡ በጥቃቱ 7 ፖሊሶችን ጨምሮ 12 ሰዎች መገደላቸውን ለዶቼ ቬለ የገለጹት ሁለት የከተማው ነዋሪዎች አካባቢው አሁን ድረስ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
በታጣቂዎች በተያዘችው የሰገን ከተማ የከባድ መሣሪያ የሚመስል ድምፅ መስማታቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ “ በጥቃቱ ሰባት የወረዳው ፖሊስ አባላት ተገድለዋል ፡፡ ከነዋሪዎች አምስት ሰዎች ሞተዋል ፡፡  የፖሊስ አባላት የተገደሉት ቅዳሜ እና እሁድ ከታጣቂዎቹ ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ነው ፡፡ የነዋሪዎቹ ህይወት ያለፈው በተኩስ ልውውጥ መኻል በተባራሪ ጥይት ተመተው ነው ” ብለዋል ፡፡

በታጣቂዎች የተያዘችው የሰገን ከተማ

የኮንሶ ዞን አካል የሆነችው የሰገን ከተማ ካባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እስከአሁን በታጣቂዎች እጅ እንደምትገኝ ዶቼ ቬለ ከሥፍራው ከሚገኙ ታማኝ ምንጮች አረጋግጧል ፡፡ በጥቃቱ የፖሊስ አባላቱ ከተገደሉ በኋላ የወረዳው አመራሮች ወደ ካራት ከተማ መሸሻቸውን የጠቀሱ አንድ የከተማው ነዋሪ “ በአሁኑ ወቅት ከታጣቂዎቹ በስተቀር በአካባቢው የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎችም ሆኑ በሥራ ላይ የሚገኝ የመንግሥት ተቋማት የሉም ፡፡ በእርግጥ ትናንትናና ዛሬ በከተማዋ ዙሪያ መለስተኛ የተኩስ ድምጽ ተሰምቷል ፡፡ ጋቶ በሚባል አካባቢ ከሚገኘው ካምብ የመከላካያ ሠራዊት እየገባ ቢባልም እስከአሁን ግን አልደረሰም “ ብለዋል ፡፡

የተቃጠለ መኪና
በጥቃቱ 7 ፖሊሶችን ጨምሮ 12 ሰዎች መገደላቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገልፀዋልምስል Basire Balcha /DW

የማረጋጋት ሥራዎች

ዶቼ ቬለ በጥቃቱ ዙሪያ ያነጋገራቸው የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ ኀሃዛዊ መረጃ ለመቀስ ቢቸገሩም በከተማው በተፈጸመ ጥቃት የፖሊስ አባላት እና ሲቪሎች መገደላቸውን ግን ተናግረዋል ፡፡ ጥቃቱን ያደረሱት በአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ሥም የአካባቢውን ሠላም ለማደፍረስ የሚፈልጉ “ ፀረ ሰላም ሐይሎች “ ናቸው ያሉት የኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊው “ የጥፋት ኃይሉ አሁን ድረስ በከተማው በመዘዋወር የንብረት ዝርፊያና ውድመት እየፈጸመ ይገኛል ፡፡ በእኛ በኩል ወደ ከተማው የፀጥታ ኃይል በማስገባት አካባቢውን ለማረጋጋት ከክልልና ከፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ጋር እየሠራን እንገኛለን “ ብለዋል  ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች  በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው  ፡፡ በአካባቢው የተደራጁ ቡድኖች የሰገን ዙሪያ ወረዳን ከኮንሶ ዞን በመነጠል የራሳቸውን አስተዳደር ለመመሥረት አንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ይታወቃል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ልደት አበበ
ዮሃንስ ገብረእግዚዓብሄር