1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 28፣2016 የዓለም ዜና

Mohammed,Negashዓርብ፣ ሰኔ 28 2016

-የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገዉን ግጭት ለማስቆም ጠንካራ ርምጃ ይወስድ ዘንድ የኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን የሲቪል ማሕበራት ምክር ቤት አባላት ጠየቁ።-የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ)ን ላለፉት አምስት ዓመታት የመሩት ዶክተር ዳንኤል በቀለ ዛሬ ተሰናበቱ።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ትናንት በሥም ያልጠቀሷቸዉን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ወቅሰዉ ነበር።-ትናንት ብሪታንያ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ያሸነፈዉ የሐገሪቱ የሠራተኛ ወይም ሌበር ፓርቲ መሪ ዛሬ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ያዙ።

https://p.dw.com/p/4hwjH

አትላንታ-የኢትዮጵያን ግጭት ለማስቆም ዩናይትድ ስቴትስ እርምጃ እንድትወስድ ተጠየቀች

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገዉን ግጭት ለማስቆም ዩናይትድ ስቴትስ ሁነኛ እርምጃ እንድትወስድ የኢትዮጵያዉያን-አሜሪካዉያን የሲቢክ ማሕበራት ምክር ቤት ጠየቀ።ሰባት ማሕበራትን የሚያስተናብረዉ ምክር ቤት መሪዎች ጥያቄዉን ያቀረቡት ከዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች (ሴናተርስ) ጋር ሲወያዩ ነዉ።ዋሽግተን ዉስጥ በተደረገዉ ዉይይት የሰባቱ የሲቢክ ማሕበራት ተወካዮችና ስድስት ሴናተሮች ተካፍለዋል።የሲቢክ ማሕበራቱ ምክር ቤት ሊቀመንበር መስፍን መኮንን እንዳሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረገዉን ግጭት ለማስቆም የአሜሪካ መንግስት ማዕቀብ መጣልን ጨምሮ የተለያዩ ርምጃዎችን እንዲወስድ የማሕበራቱ ተወካዮች ጠይቀዋል።የሲቢክ ማሕበራቱ ወደፊትም ከሴኔቱ ንዑስ ኮሚቴና ከሕግ አዉጪ ምክር ቤት አባላት ጋር ለመነጋገር ማቀዱን አቶ መስፍን አስታዉቀዋል።የአትላንታዉ ዘጋቢያችን ታሪኩ ኃይሉ እንደዘገበዉ በሲቢክ ማሕበራቱና በሴናተሮቹ መካከል ሥለ,ደረገዉ ዉይይት በዋሽግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየትን ለማካተት ሞክሮ ነበር።ግን አልተሳካለትም። 

አዲስ አበባ-የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዘመነ ሥልጣን አበቃ

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ዘመነ ሥልጣን ዛሬ አበቃ።ዶክተር ዳንኤል በቀለ ዛሬ እንዳሉት የኮሚሽኑን የመሪነት ሥልጣን የተረከቡት በኃላፊነት የሚሠሩት ለአምስት ዓመታት ብቻ እንደሆነ ተስማምተዉ ነዉ።የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪዉ ኃምሌ ዶክተር ዳንኤልን የሚተካ ዋና ኮሚሽነር እስኪሾም ድረስ ኮሚሽኑ በምክትል ዋና ኮሚሽነር ይመራል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ትናንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸዉ ጥያቄ መልስና ማብራሪያ ሲሰጡ በስም ያልጠቀሷቸዉን ነገር ግን «ደሞዝ የምንከፍላቸዉ» ያሏቸዉን የመብት ተሟጋች ተቋማትን አጥብቀዉ ወቅሰዉ ነበር።ጠቅላይ ሚንስትሩ «ደሞዛቸዉን እኛ እየከፈልን፣ የሚያስፈፅሙት የዉጪዎችን አጀንዳ ነዉ» በማለት ነቅፈዋል።በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣዉ ዘገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ታጣቂዎችና የመንግሥት የጸጥታ ኃይላት በሚወሰዱት እርምጃዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሰው የሞት እና የአካል ጉዳት ፣በሕይወት የመኖር መብትን አሳሳቢ አድርጎት መቀጠሉን አስታዉቋል።ኮሚሽኑ ያለፈውን አንድ ዓመት የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ በገመገመበት ዘገባዉ ከአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ጋር በተገናኘ በርካቶች ለተራዘመ እሥር፣ እንግልት፣ ዘለፋ ፣ ድብደባና ለሌሎች የመብት ጥሰቶች ተጋልጠዋል ማለቱን የአዲስ አበባዉ ዘጋቢያችን ሰለሞን ሙጬ ጠቅሷል።

 

አዲስ አበባ-በጅምላ ታሠሩ የተባሉት ተለቀቁ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማና ከአካባቢዉ በጅምላ ታስረው ነበር የተባሉ በርካታ ነዋሪዎች ትናንት  መለቀቃቸው ተነግሯል፡፡የአከባቢው ነዋሪዎች እና የታሳሪ ቤተሰቦች በተለይም በጊምቢ ከተማ 04 ቀበሌ በርካቶች መታሰራቸዉን አስታዉቀዉ ነበር።ሰዎቹ የታሠሩት “ልጆቻችሁ በአከባቢው የሚንቀሳቀሰውን አማፂ ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በመቀላቀላቸው” ነው ተብለዉ መሆኑን ተናግረዉም ነበር።የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ለዶይቼ ቬለ ዛሬ በሰጡት አስተያየት ለሁለት ሳምንታት ታስረው የነበሩት  በሙሉ መለቀቃቸውን አረጋግጠዋል።ከነዋሪዎቹ አንዱ የሚከተለዉን ብለዋል።
“አስቀድሞ ልጆቻቸው በትጥቅ ውጊያው ውስጥ መሞታቸው የተረጋገጠው 12 ሰዎች ገደማ ወዲያው ተጠርተው ተለቀው ነበር፡፡ ሌሎቹ 70 ሰዎች ገደማ የሚሆኑትን ግን ትናንት ምሽት አከባቢ ልክ በታሰሩ በ14ኛ ቀናቸው ለቀቸዋል፡፡ በዚያ ውስጥ እስር ላይ እያሉ አማጺ ቡድንን ስለተቀላቀሉ ልጆቻቸው የተጠየቁት ቤተሰቦች ልጆቹ ከ18 ኣመት በላይ መሆናቸውና ከትዕዛዛቸው ውጪ የወጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እኛ ስላልላክናቸው ማስገባትም አንችልም አሉዋቸው” ብለዋል፡፡
በዚህ ላይ  ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የጊምቢ ከተማ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ክፍሉ ዋጋሪ የእጅ ስልካቸው ላይ በመደወል አስተያየታቸውን ለመጠየቅ ጥረት ያደረገው የአዲስ አበባው ዘጋቢችን ስዩም ጌቱ እንዳልተሳከለት ዘግቧል።

 

ፖርት ሱዳን-ዉጊያ ሲሸሹ 25 ሰዎች ሞቱ፣120ሺሕ ተፈናቃሉ

የሱዳን መከላከያ ሠራዊትና የሐገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ደቡብምሥራቅ ሱዳን ሴናር ግዛት ዉስጥ የገጠሙትን ዉጊያ ሲሸሹ 25 ሰዎች ዓባይ (ወይም ናይል) ወንዝ ዉስጥ ሰምጠዉ ሞቱ።አፍቃሬ ዴሞክራሲ የሚባለዉ የሱዳን የፖለቲካ አቀንቃኞች ቡድን እንዳለዉ ከዉጊያዉ ባመለጡ ሰዎች የተሞላች አንዲት ጀልባ ወንዙ ዉስጥ በመስመጧ አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ሞተዋል።ከሟቾቹ አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት ናቸዉ።RSF በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ሴናር ግዛት ዋና ከተማ ሲንጃ የሚገኘዉን የጦር ሠፈር መቆጣጠሩን ባለፈዉ ዕሁድ አስታዉቋል።ሴናር ግዛትን ላለማስያዝና ለመያዝ ለተከታታይ ቀናት በተደረገዉ ዉጊያ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በዉል አልታወቀም።እስከ ትናንት ድረስ ዉጊያን ሸሽቶ ሴናር አጎራባች ገዳሪፍ ግዛት የገባዉ ተፈናቃይ ቁጥር 120 መድረሱን የገዳሪፍ ባለሥልጣናት አስታዉቀዋል።15 ወሩን በያዘዉ የሱዳን የርስበርስ ጦርነት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አንድም ተፈናቅሏል፣ አለያም ተሰድዷል።
 

ለንደን-የብሪታንያ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር 

የብሪታንያ የሠራተኛ ወይም ሌበር ፓርቲ መሪ ኪር ስታርመር የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዉ በመመረጣቸዉ ከሐገራትና ከድርጅት መሪዎች የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት እየጎረፈላቸዉ ነዉ።የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ፣ ኢጣሊያዋ ቀኝ ፅንፈኛ ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒም፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ተሰናባች ዋና ፀሐፊ የንስ ሽቶልተንበርግና ሌሎችም እኩል ለአዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።ብሪታንያ ዉስጥ ትናንት በተደረገዉ ምርጫ ለረጅም ዓመታት በተቃዋሚ ፓርቲነት የቆየዉ ሌበር ፓርቲ በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት አሸፏል።ሌበር ከ650 የምክር ቤት መቀመጫዎች 410ሩን ተቆጣጥሯል።ብሪታንያን ላለፉት 14 ዓመታት የመራዉ የወግ አጥባቂዉ ፓርቲ ያገኘዉ መቀመጫ 118 ነዉ።የወግ አጥባቂዉ ፓርቲ መሪና የእስከ ዛሬዉ ጠቅላይ ሚንስትር ረሺ ሱናክ ሥልጣን ለቅቀዋል።በብሪታንያ ሕግ መሠረት የሐገሪቱ ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ ዛሬዉኑ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ያፀደቁላቸዉ ኪር ስታርመር ተሰናባቹን ጠቅላይ ሚንስትር አመሰግነዋል።
             
«ተሰናባቹን ጠቅላይ ሚንስትር ረሺ ሱናክን ማመስገን እወዳለሁ።የመጀመሪያዉ የብሪታንያ-ኤሺያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዉ ለሐገራችን ያስገኙት ዉጤትና ያደረጉት ተጨማሪ ጥረት በማንም በቀላሉ ሊታይ አይገባም።ዛሬ ለዚሕ አስተዋፅዖቸዉ ምስጋና እናቀርባለን።በአመራራቸዉ ላሳዩት ፅናትና ብርቱ ሥራቸዉ እዉቅና እንሰጣለንም።ይሁንና አሁን ሐገራችን በግልፅ ለለዉጥ ድምፅ ሰጥታለች።»

የ61 ዓመቱ ፖለቲከኛ ስታርመር ካቢኒያቸዉን አዋቅረዋል።የብሪታንያዉ የመሐል ግራ የፖለቲካ ፓርቲ ሌበር ታላቅ ድል ያስመዘገበዉ ኢጣሊያ፣ ፈረንሳይና ጀርመንን በመሳሰሉ የአዉሮጳ ሐገራት ቀኝ ፅንፈኞች ሥልጣን መያዛቸዉና ይይዛሉ መባሉ ብዙዎችን ባሰጋበት ወቅት ነዉ።
 

ሞስኮ-የሐጋሪ ጠቅላይ ሚንስትር የሠላም ጥረት

የሐጋሪዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባን በሚቀጥሉት ሥድስት ወራት ዉስጥ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ሰላም ሊወርድ እንደሚችል አስታወቁ።ዛሬ ሞስኮ ዉስጥ ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተነጋገሩት ኦርባን እንደሚሉት መንግስታቸዉ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም አበክሮ ይጥራል።ኦርባን ወደ ሞስኮ ከመጓዛቸዉ በፊት ኪቭ ዉስጥ የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮልድምየር ዘለንስኪን አነጋግረዉ ነበር።በአብዛኞቹ የምዕራባዉያን መንግስታት ዘንድ ለሩሲያ የሚያዳሉና ቀኝ አክራሪ ተደርገዉ የሚነቀፉት ኦርባን በቅርብ ዓመታት ዉስጥ የኪቭና የሞስኮ መሪዎችን እኩል በማነጋገር የመጀመሪያዉ የአዉሮጳ መሪ ናቸዉ።ኦርባን ተዘዋዋሪዉን የአዉሮጳ ሕብረትን የሊቀመንበርነት ሥልጣን ባለፈዉ ሰኞ ተረክበዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።