1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ሐሙስ፣ ሰኔ 27 2016

https://p.dw.com/p/4hsy2

አርዕስተ ዜና

*ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት አይሳካም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናገሩ ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፦ 16 የምክር ቤት አባላት ላቀረቡላቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡት ወቅት ነው ።  

*የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ግብር ለመጨመር ማቀዳቸውን በሀገሪቱ ወጣቶች አመጽ አስገዳጅነት ከዘሰረዙ በኋላ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF)ኃላፊ ጋ ተነጋገሩ ።

*የሊባኖሱ ሒዝቦላህ ከ‘200 በላይ ሮኬቶችን’ ወደ እሥራኤል  ማስወንጨፉን ገለጠ ። ሒዝቦላህ ከድንበር ባሻገር የሚገኙ አምስት የእሥራኤል ወታደራዊ ዒላማዎችን ዒላማ ማድረጉንም ዐሳውቋል ። ሒዝቦላሕ 160 ሮኬቶችን አስወንጭፎ 15 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ያሰማራ ቢሆንም አብዛኛዎቹን የእሥራኤል መከላከያ ተኩሶ እንደጣላቸው ተዘግቧል ።

ዜናው በዝርዝር

አ.አ፥አየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያ

ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት አይሳካም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናገሩ ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም እና የት እንደተደረገ ባይጠቅሱም በኢትዮጵያ መንፈቅለ መንግስት ለማድረግ ውይይት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው እሳቤው የማይሳካ መሆኑን ገልፀዋል ።

«በቅርቡ አንዳንድ ቦታ ላይ መፈንቅለ መንግሥት እናደርጋለን ብለው አንዳንድ አባቶቻችን ውይይት ያደርጋሉ   መፈንቅለ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይሳካም ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት አንዴ ተሳካ የዛሬ አምሳ ዓመት ከአምሳ ዓመት በኋላ ብዙ የሚረቡ እና የማይረቡ ሙከራዎች ነበሩ አልተሳኩም አሁን ጭራሽ አይሳካም ለተከበረው ምክር ቤት ማረጋገጥ የምፈልገው፤ ዛሬ ሰላም እንዲሁን ነው እኛም የምፈልገው ለሰላም የሚከፈለውን ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁዎች ነን »

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህን ዛሬ የተናገሩት፦ 16 የምክር ቤት አባላት ላቀረቡላቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡት ወቅት ነው ። 

ካርቱም፦ በትግራዩ ጦርነት ሱዳን የገቡ ስደተኞች የከፋ ችግር ላይ ነን አሉ

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ተባባሪዎች ከትግራይ ኃይሎች ጋ በ2013 ዓመተ ምህረት ጦርነት ሲገቡ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገለጡ ። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአብዛኛው ከሑመራ እና ሌሎች ከሱዳን ጋ ከሚዋሰኑ አካባቢዎች ተፈናቅለው፣ ሱዳን የገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የከፋ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ተናግረዋል ።  30 ሺህ ግድም የትግራዩ ጦርነት ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ተነድባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ስደተኛ ከሆኑት አንዱ ጦርነቱ ወዳሉበት መቃረቡን ለዶይቸ ቬለ ቀጣዩን ተናግረዋል ።

«ጦርነቱ ወደ እኛ እየተቃረበ ነው እዚህ ያሉ የሱዳን ተወላጆች እና የሱዳን ዜጎች የሆኑ ሰዎች መኪናቸውን አስነስተው፦ ዕቃቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ቤተሰባቸውን ይዘው እየሸሹ ነው እና ወደ ሌላ ቦታ የምንሄድበት አቅሙም የለንም ቦታውንም ዐናውቅም፤ መሀል ላይ ነው ያለነው »

እነዚህ 60 ሺህ ገደማ የሚገመቱ እና በሱዳን ተነድባ እና ዑምራኩባ የተባሉ መጠልያዎች ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግስት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲደርሱላቸው ተማጽነዋል ሲል ሚልዮን ኃይለሥላሴ ዘግቧል።

ናይሮቢ፥ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ከኬንያ አመጽ በኋላ ከIMF ኃላፊ ጋ ተነጋገሩ

የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ግብር በመጨመር ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን በሀገሪቱ ወጣቶች አመጽ አስገዳጅነት ከዘሰረዙ በኋላ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF)ኃላፊ ጋ ተነጋገሩ ። ፕሬዚዳንቱ ዛሬ የተነጋገሩት ከድርጅቱ ኃላፊ ክሪስቲና ጂዮርጂቫ ጋ በስልክ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ሁለት የዲፕሎማት ምንጮችን ጠቅሶ ዘገግቧል ። የግብር ጭማሪን አካቶ የነበረው እና ፕሬዚደንቱ ከገዳዩ አመጽ በኋላ የሰረዙት የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ኬንያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋ የተስማማችበት የፖሊሲ ለውጥ መአከል ነው ። ስምምነቱ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከኬንያ ጋ የተስማማበት የ3,6 ቢሊዮን ዶላር ብድር መርሐ ግብር አካል ነው ።  የዊሊያም ሩቶ መንግሥት የግብር ጭማሪ እቅድን በመቃወም በኬንያ በተቀሰቀሰው ዓመጽ እስከ ሰኞ ድረስ ቢያንስ 39 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (KNCHR) ዐሳውቋል ። ለሁለት ሳምንታት በነበረው አመጽ የተቀላቀለበት ተቃውሞ 361 ሰዎች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸውም ኮሚሽኑ አክሏል ። 

ኪቩ፥ የኮንጎ ወታደራዊ ፍርድ ቤት 25 ወታደሮች ላይ የሞት ፍርድ በየነ

የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሪፐብሊክ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሃያ ዓምስት ወታደሮች ላይ የሞት ፍርድ በየነ ። ወታደሮቹ የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ኬሴጌ እና ማቴምቤ መንደሮች ውስጥ ከM23 አማጺዎች ጋ ከነበረው የጦር አውድ በመሸሽ እና በስርቆት ተከሰው መሆኑን ጠበቆቻቸው እና የጦር ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል ።   በምሥራቃቂ የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሪፐብሊክ ግዛት የM23 አማጺዎች ካለፈው ሳምንት አንስቶ ቁልፍ ከተሞችን በመቆጣጠራቸው የአካባቢው ውጥረት መባባሱ ተገልጧል ። አማጺያኑ ካለፈው ሳምንት ዐርብ እና ቅዳሜ አንስቶ ካንያባዮንጋ እና ኪሩምባ የተሰኙትን ከተሞች እንደተቆጣጠሩ ነው ። የኮንጎ ጦር ሠራዊት በጎረቤት ርዋንዳ ከሚደገፉት የ M23 አማጺዎች ጋ ካለፉት ሁለ።ት ዓመታት አንስቶ በመዋጋት ላይ ነው ። 2,7 ሚሊዮን ግድም ሰዎችን ባፈናቀለው የሰሜን ኪቩ አውራጃ ቀውስ ሌሎች አማጺ ቡድኖችም በውጊያ ላይ ናቸው ።

የሊባኖሱ ሒዝቦላህ ከ‘200 በላይ ሮኬቶችን’ ወደ እሥራኤል  ማስወንጨፉን ገለጠ ። ሒዝቦላህ ከድንበር ባሻገር የሚገኙ አምስት የእሥራኤል ወታደራዊ ዒላማዎችን ዒላማ ማድረጉንም ዐሳውቋል ። የእሥራኤል መገናኛ አውታሮች ጦር ሠራዊቱን በመጥቀስ አንደዘገቡት ሒዝቦላሕ 160 ሮኬቶችን አስወንጭፎ 15 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አሰማርቶ ነበር ። አብዛኛዎቹን የእሥራኤል መከላከያ ተኩሶ እንደጣላቸውም ዘግበዋል።  ሒዝቦላህ በዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመን እና በርካታ የሱኒ ዐረብ ሃገራት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ሲሆን፤  በኢራን የሚደገፍ የሊባኖስ የሺዓ ፖለቲካ ፓርቲ  እና ወታደራዊ ክንፍ ነው ። የሒዝቦላህ ጥቃት የደረሰው የእሥራኤል ካቢኔ የሐማስ ተኩስ አቁም ሐሳብ ለመነጋገር በተዘጋጀበት ወቅት መሆኑ ተዘግቧል።  እሥራኤል ከጥቃቱ በኋላ የሐማስን የተኩስ አቁም ሐሳብ እያጤነችበት መሆኑ ተነግሯል ። ስለደረሰ ጉዳት በውል አልተነገረም ።

ጆሐንስበርግ፥በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ድልድል የኢትዮጵያ ምድብ ታወቀ

ደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ውስጥ ዛሬ በተደረገው የ2025 የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ድልድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 8 ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ጊኒ እና ታንዛንያ ጋር መደልደሉ ታወቀ ። እያንዳንዳቸው አራት ሃገራት ባሉበት 12 ምድቦች ከተደለደሉት የ48ሃገራት ቡድኖች ውስጥ ከእያንዳንዱ ምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ 24 ቡድኖች ለአፍሪቃ ዋናጫ ውድድር ያልፋሉ ። አሰተናጋጇ ሞሮኮ ካለችበት ምድብ 2 ሞሮኮ በቀጥታ ስታልፍ እሷን ተከትሎ የሚያልፈው አንድ ሃገር ብቻ ነው ። ምድብ ሁለት ውስጥ፦ አሰተናጋጇ ሞሮኮ፤ ጋቦን፤ መዓከላዊ የአፍሪቃ ሪፐብሊክ እና ሌሶቶ ተደልድለዋል ። የማጣሪያ ውድድሮቹ በመስከረም፤ ጥቅምት እና ህዳር ወራት ውስጥ ይካሄዳሉ ተብሏል ። ውድድሩ ሞሮኮ ውስጥ ከታኅሣስ 12 ቀን፣ 2018 እስከ ጥር 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።