1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሰኞ፣ ሰኔ 24 2016

አርዕስተ ዜና ቱርክ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የወደብ ስምምነት ሰበብ የተቃቃሩትን ኢትዮጵያንና ሶማሊያን እየሸመገለች መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በመጀመሪያ ዙር የፈረንሳይ የፓርላማ አባላት ምርጫ National Rally በምህጻሩ RN የተባለው የማሪ ለፐን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ታሪካዊ የተባለ ድል ተጎናፀፈ። ውጤቱ ፓርላማውን በትነው ምርጫ ለጠሩት ለፕሬዝዳንት ማክሮ ትልቅ ሽንፈት ሆኗል። የዩንይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግል በወሰዷቸው እርምጃዎች እንጂ እንደ ፕሬዝዳንት በይፋ በወሰዷቸው እርምጃዎች ሊከሰሱ አይችሉም ሲል ወሰነ።

https://p.dw.com/p/4hkZH

ሮይተርስ    ቱርክ ኢትዮጵያንና ሶማሊያን እየሸመገለች ነው ተባለ

 

ቱርክ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የወደብ ስምምነት ሰበብ የተቃቃሩትን ኢትዮጵያንና ሶማሊያን እያሸማገለች መሆኑን አራት ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ካላቸው ሰዎች መስማቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። እንደሮይተርስ ሽምግልናው የሁለቱ ጎረቤት የምስራቅ አፍሪቃ አገራትን የሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጠገን የሚደረግ የቅርብ ጊዜ ጥረት ነው።ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በታህሳስ መጨረሻ ላይ  ከሶማሌንድ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የባህር ጠረፍ በሊዝ መገልገል የሚያስችላት የመግባባቢያ ሰነድ ከሶማሌላንድ ጋር መፈራረሟ  ሶማሊያን እንዳስቆጣ ነው። በምትኩም ኢትዮጵያ ሶማልያ የግዛቴ አካል ናት ለምትላት ለሶማሌላንድ እውቅና ትሰጣለች መባሉ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አሻክሯል።በዚህ ሰበብም ስምምነቱን ሕገ ወጥ ያለችው መቅዲሾ በሀገርዋ የኢትዮጵያን አምባሳደር አባራ ሀገርዋ የዘመቱ  በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደምታስወጣ ዝታለች። ስለሽምግልናው ጥረት ሮይተርስ አስተያየት የጠየቃቸው የሶማሊያ መንግሥት ቃል አቀባይ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወዲያውኑ መልስ አልሰጡም ።ሮይተርስ ስለ ሽምግልናው ጥረት ካነጋገራቸው ሁለቱ እንዳሉት የድርድሩ ዓላማ ግልጽ አይደለም። ከንግግሩ  ምክረ ሀሳብ የመጠበቁም ሁኔታ ዝቅተኛ ነው ብለዋል። ከመካከላቸው አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለሥልጣን ጥረቱ መግፋቱ  እንደማይታያቸው ከንግግሩም ብዙ እንደማይጠብቁ ገልጸዋል።

ናይሮቢ የኬንያ የፖለቲካ አራማጆች ለነገ የአደባባይ ሰልፍ ጥሪ አስተላለፉ።

 

የኬንያ የፖለቲካ አራማጆች ለነገ የአደባባይ ሰልፍ ጥሪ አስተላለፉ። ሰዉ የኬንያ ዋና ከተማ የናይሮቢን የንግድ ማዕከል እንዲቆጣጠር በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ሲማጸኑ ነበር።ተቃውሞ ያስነሳውን የታክስ ጭማሪን ያካተተውን ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ ከመፈረም የተቆጠቡት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ያቀረቡትን የእንነጋገር ጥሪ ወጣቶች የሚያመዝኑባቸው ተቃዋሚዎች ወደ ጎን ገፍተዋል። ባለፉት ሳምንታት በፖሊስና በሰልፈኞች መካከል በተካሄደ ግጭት ቢያንስ የ24 ሰዎች ሕይወት አልፏል።  ተቃዋሚዎቹ መነሻ ያደረጉት የታክስ ጭማሪ ቢታገድም በሀገሪቱ ተንሰራፍቷል የሚሉት ሙስና ከስር መሠረቱ እንዲወገድ እና ሩቶም ከሥልጣናት እንዲወርዱ እየጠየቁ ነው። ሩቶ ትናንት ከአንድ የኬንያ ቴሌቪዥን ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ በተቃውሞው ወቅት ፖሊስና መንግሥታቸው የወሰደውን እርምጃ ተከላክለዋል። ፖሊስ በነበበረው ሁኔታ ማድረግ የሚችለውን የተሻለ ነገር አድርጓል ያሉት ሩቶ ለደረሰው ጥፋት ሰላማዊውን ተቃውሞ አግተዋል ያሏቸውን ወንጀለኞች ተጠያቂ አድርገዋል።   ሆኖም እርምጃዎቹ የተቃዋሚዎቹን አቋም እንዲጠናከር ያደረጉ ይመስላል።  አሁንም ያላበቃው የዚህ ተቃውሞ ይፋ መሪ የለም። ህዝቡም አሁን ለቀረበለት ጥሪ እስከ ምን ድረስ ምላሽ እንደሚሰጥም ግልጽ አይደለም።ረቂቅ የፋይናንስ ሕጉን ከስራ ውጭ የማድረግ አስቸኳይ ዓላማ ከተሳካ በኋላ በዚሁ ኃይል እንዴት መቀጠል እንዳለባቸው ወጣቶቹ እየተነጋገሩ ነው። በእሁዱ ቃለ መጠይቅ ላይ ሩቶ እንደከዚህ ቀደም ከወጣቶች ጋር ለመነጋገር በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል። እርሳቸው እንዳሉት ንግግሩን በቀድሞ መጠሪያው ትዊተርን በአሁኑ መጠሪያው ኤክስን  ጨምሮ ወጣቶቹ በሚፈልጉት ማንኛውም መድረክ ለማካሄድ ዝግጁ ናቸው። ከተቃዋሚዎቹ አብዛኛዎቹ ግን የእንንነጋገሩን  ጥሪ አልተቀበሉም። መነጋገሩ እንቅስቃሴያቸውን የሚያዳክም አድርገው ነው የሚያዩት።

ፓሪስ    ቀኝ ጽንፈኞች በፈረንሳዩ የፓርላማ አባላት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ታሪካዊ ድል አገኙ

 

ትናንት በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የፈረንሳይ የፓርላማ አባላት ምርጫ National Rally በምህጻሩ RN የተባለው የማሪ ለፐን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ታሪካዊ የተባለ ድል ተጎናፀፈ። የለፔን ፓርቲና  አጋሮቹ እከዛሬ  በምርጫ አግኝተውት የማያውቀውን  33.1 በመቶ ድምጽ አሸንፈዋል። የግራ ክንፍ ፓርቲዎች ደግሞ 28 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ይዘዋል። ሀገሪቱን የሚመራው የመሀል አቋም የሚያራምደው የፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ፓርቲ ደግሞ 20 በመቶ ድምጽ ብቻ ማግኘቱን የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትቴር ዛሬ ይፋ ባደረገው ውጤት ተረጋግጧል። ውጤቱ ባለፈው ወር በተካሄደው የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ  ፓርቲያቸው በRN ሲበለጥ ፓርላማውን በትነው ምርጫ ለጠሩት ለፕሬዝዳንት ማክሮ ትልቅ ሽንፈት ሆኗል።ይሁንና ፀረ-የውጭ ዜጎች አቋም የሚያራምደው RN መንግሥት መመስረት መቻል አለመቻሉ በሁለተኛ ዙር ምርጫ ውጤት የሚወሰን ይሆናል። ከዚህ ሌላ በመላ ፈረንሳይ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ሌሎች  የፓርቲው ተቀናቃኝ እጩ ተወዳዳሪዎች የለፔንን ዘመቻ  ማሰናከል መቻል አለመቻላቸውም ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው ተብሏል።  ማሪ ለፔን ከድሉ በኋላ እንደተናገሩት ትናንት በፈረንሳይ የሆነው እስከዛሬ ታይቆ የማይታወቅ ነው። ለፈረንሳይ ህዝብም ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።

«ታሪካዊ ውጤት ነው። እስከዛሬ በመጀመሪያ ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ አንድም የNATIONAL RALLY እጩ ተወዳዳሪ አሸንፎ አያውቅም ነበር።  ዛሬ ግን በመጀመሪያው ዙር ምርጫ በርካታ እጩ ተወዳዳሪዎች ተመርጠዋል። እንደሚመስለኝ ይህ በሚሊዮኖች ለሚቆጠር የፈረንሳይ ህዝብ የትልቅ ተስፋ አንድ አካል ነው።»

የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋብርየል አታ የትናንቱን ምርጫ ውጤት በፈረንሳይ የዴሞክራሲ ታሪክ እስከዛሬ ያልታሰበ ስጋት የፈጠረ ነው ያሉት ። እናም አታ ዓላማቸው  ፓርቲው ስልጣን እንዳይዝ መከላከል  ነው ብለዋል።  

የዛሬው ትምሕርት ቀኝ ጽንፈኞች ስልጣን በር ላይ መድረሳቸው ነው። በዴሞክራሲያችን ታሪክ በብሔራዊ ምክር ቤታችን የቀኝ ጽንፈኞች የመበራከት ስጋት አጋጥሞን አያውቅም። እናም ዓላማችን ግልጽ ነው። NATIONAL RALLY በሁለተኛው ዙር ምርጫ ፍጹም አብላጫ ድምጽ እንዳያገኝ ፣ አባላቱ በብሔራዊው ምክርቤትም እንዳያመዝኑ  እና አጥፊ በሆነው መርኃቸው ሀገሪቱን እንዳይመሩ መከላከል ነው።»

የፈረንሳይ ግራ ክንፉ ፓርቲ እና የማክሮን የለዘብተኞች ኅብረት መሪዎች በሚቀጥለው ሳምንቱ ምርጫ  RNንን ሊያሸንፍ የሚችል ተወዳዳሪ ከሚገኝባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እጩ ተወዳዳሪዎቻቸውንን እንደሚያስወጡ አስታውቀዋል። በአብዛኛዎቹ ፈረንሳውያን ለብዙ ጊዜያት ተገልሎ የቆየው RN ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ስልጣን ለመያዝ ተቃርቧል። የፓርቲው መሪ ለፔንም በዘረኛነት እና በፀረ ሴማዊነት የሚታወቀውን የፓርቲያቸውን ገጽታ ለመቀየር አስበዋል። ይህ የለፔን ስልትም በማክሮ የተበሳጩ ፣የኑሮ ውድነት እና የበረታው ፍልሰት የሚያሰጋቸውን ድምጽ እንዲያገኙ አግዟቸዋል።የRN ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገዝፎ መውጣት ያስደነገጣቸው የፓርቲው ተቃዋሚዎች ትናንት በተለያዩ የፈረንሳይ ከተሞች ሰልፍ አካሂደዋል።  ኑቮ ፍሮ ፖፑሌር የተባለው የግራ ክንፍ ፓሪቲ መሪዎች የተገኙበት ትልቁ ሰልፍ በፓሪሱ ፕላስ ደላ ሪፐብሊክ አደባባይ የተካሄደው ነው።

 

ጋዛ  እስራኤል 55 ፍልስጤማውያንን ከእስር ለቀቀች

 

እስራኤል አንድ ጋዛ የሚገኘውን የሺፋ ሆስፒታል ሃላፊን ጨምሮ 55 ከጋዛ የያዘቻቸውን ፍልስጤማውያን ዛሬ ከእስር ለቀቀች። አንድ የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣን እንደተናገሩት  ፍርድ ቤት ሳይቀርቡም ሆነ ክስ ሳይመሰረትባቸው የሺፋ ሆስፒታል በእስራኤል ጦር ከተወረረበት ካለፈው ህዳር አንስቶ ታስረው የቆዩት የሺፋ ሆስፒታል ሃላፊ ሞሐመድ አቡ ሰልምያ ዛሬ እስራኤል ከለቀቀቻቸው ፍልስጤማውያን መካከል አንዱ ናቸው። አቡ ከዚህ ቀደም በወጡ የቪድዮ መልዕክቶች የእስራኤል ወታደሮች አካላዊና ስለ ልቦናዊ ጥቃት እንደፈጸሙባቸው ተናግረዋል። እስራኤል ፣ሆስፒታሉ የሀማስና ሌሎች የሚሊሽያዎች ቡድኖች መሸሸጊያ ነው ስትል ትከሳለች። 

 

ዋሽንግተን    የትራምፕ ያለ መከሰስ መብት ጉዳይ ውሳኔ አገኘ

 

የዩንይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግል በወሰዷቸው እርምጃዎች እንጂ እንደ ፕሬዝዳንት በይፋ በወሰዷቸው እርምጃዎች  ሊከሰሱ አይችሉም ሲል ወሰነ። ዛሬ የተሰየሙት ዳኞች በጽሁፍ ባስተላለፉት ውሳኔ ፣የስር ፍርድ ቤት ትራምፕ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓመት ምኅረት በጆ ባይደን መሸነፋቸውን ለመቀልበስ ያደረጓቸውን ጥረቶች ጨምሮ በወንጀል ክሶች ያለ መከሰስ መብት አለኝ ያሉትን ተቃውሞ መወሰኑን ውድቅ አድርገዋል።የትራምፕ ጉዳይ ለተጨማሪ እይታ ወደ ስር ፍርድ ቤት ተመልሶ ይላካልም ተብሏል።

 

በርሊን   አንድ ታዋቂ የጀርመን ፖለቲከኛ የናዚን መፈክሮች በመጠቀም ተፈረደባቸው

 

አንድ ታዋቂ የቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን »ፓርቲ ፖለቲከኛ የናዚን መፈክር በመጠቀም ለሁለተኛ ጊዜ የገንዘብ ቅጣት ተፈረደባቸው። የሀለ ግዛት ፍርድ ቤት ብዮርን ኽከ የተባሉት የ52 ዓመቱ ፖለቲከኛ በጀርመን የታገደ የናዚ መፈክርን በንግግራቸው በማካተት ጥፋተኛ ብሎ የ16 ሺህ 900 ዩሮ ወይም የ18 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት በይኖባቸዋል።ፖለቲከኛው በምሥራቅ ጀርመንዋ በቱሪንገን ከተማ በመስከረም ወር በሚካሄድ ምርጫ ለመወዳደር አቅደዋል። በጀርመን ኢ ሕገ መንግስታዊ ምልክቶችን መጠቀም ገንዘብ ወይም የሥስት ዓመት እሥራት ያስቀጣል።ኽከ ባለፈው ግንቦትም ኢ ሕገ መንግሥታዊ ምልክቶችን በመጠቀም  13 ሺህ ዩሮ ተቀጥተው ነበር። ጠበቆቻቸው ፍርዱ እንዲነሳ አቤት ብለዋል። የመጀመሪያው ቅጣት የተፈረደባቸው ሜርስቡርግ በምትባል ከተማ በግንቦት ወር ባደረጉት ንግግር ላይ «ሁሉም ለጀርመን»የሚለውን አባባል በመጠቀማቸው ነበር። ዳየታሪክ መምህሩን ፖለቲከኛ  ይህ አባባል የናዚ ጀርመን መፈክር መሆኑን እያወቁ ነው በንግግራቸው የተጠቀሙት ሲሉ ዳኞችና አቃቤ ሕግ ተስማምተዋል።  በወቅቱ ኽከ የተከለከለውን መፈክር «ሁሉም» ሲሉ በመጀመር ታዳሚዎቸው «ለጀርመን» በማለት እንዲጨርሱት አበረታተዋል ሲሉም በዛሬው ውሳኔ ላይ ተናግረዋል። ኽከ ግን ምንም ጥፋት አልፈጸምኩም ፤ሙሉ በሙሉ ንጹህ ነኝ ሲሉ ሞግተዋል። ይህን እለት ተእለት ሰዉ የሚጠቀምበትን አባባል መናገር እንዴት ወንጀል ይሆናል ሲሉም ጠይቀዋል።  

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።