1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 14፣ 2016 የዓለም ዜና

Mohammed,Negashዓርብ፣ ሰኔ 14 2016

-ለኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበዉ «ንብረት የማስመለስ ረቂቅ አዋጅ» ዉጪ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ላይ ችግር የሚፈጥር ከሆነ ከአዋጁ አርቃቂዎች ጋር እንደሚነጋገርበት የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።-ምዕራባዊ ሱዳን ዳርፉር ግዛት ዉስጥ ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ ተጨማሪ የምግብ ርዳታ ማከፋፈሉን የዓለም ምግብ ድርጅት አስታወቀ።-የእስራኤል ጦር ከደቡብ ጋዛን ከሰሜን ደቡባዊ ሊባኖስን መደብደቡን ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕም ሰሜናዊ እስራኤል በሚሳዬል መደብደቡን አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/4hNBh

አዲስ አበባ-የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ፣ ዲያስፖራና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር

በቅርቡ ለኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው "የንብረት ማስመለስ አዋጅ" ውጭ ሐገር  በሚኖረው ማሕበረሰብ ላይ የሚያሳድረዉ ችግር ካለ በጉዳዩ ላይ  አስተያየት እንደሚሰጥበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ ትናንት  በሰጡት መግለጫ "ሕጉ ገና ረቂቅ ነው፣ "እኛም አላየነውም ብለዋል። ይሁንና ሕጉ ዉጪ በሚኖሩ ወይም ዲያስፖራ ላይ  የሚያስከትላቸው ችግሮች ካሉ መስሪያ ቤታቸዉ ሕጉን ካረቀቀዉ አካል ጋር እንደሚነጋገርበት አስታዉቀዋል።"የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል" የተባለዉ "የንብረት ማስመለስ አዋጅ" በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት ቀርቦ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ እንደዘገበዉ አዋጁ "የኢኮኖሚ ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር መውጣቱ ተነግሯል።

 

ጁባ-የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ኬንያ የተያዘዉን ድርድር ተቃወሙ

 

በደቡብ ሱዳን መንግሥትና በተቃዋሚዎቹ መካከል ኬንያ ዉስጥ የሚደረገዉ ድርድር ከዚሕ ቀደም የተደረገዉን ሥምምነት አለማካተቱን የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ተቃወሙት።ምክትል ፕሬዝደንት ሪየክ ማቻር ለአደራዳሪዎች በፃፉት ደብዳቤ እንዳሉት ተቀናቃኝ ኃይላትን ለማግባባት አዲስ የተረቀቀዉ የስምምነት ሰነድ ከዚሕ ቀደም የተደረገዉን ሥምምነት የሚተካ መምሠሉ ተገቢ አይደለም።የቀድሞዉ አማፂ ቡድን መሪ ሪየክ ማቻር ከ400 ሺሕ በላይ ሰዉ ያለቀበትን የአምስት ዓመት የርስ በርሥ ጦርነት ያስቆመዉን ስምምነት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2018 ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ጋር ተፈርመዋል።አሁን የሚደረገዉ ድርድር በያኔዉ ሥምምነት ባልተካተቱ ቡድናትና በመንግሥት መካከል እንጂ የማቸር ቡድን አይካፈልም።ካለፈዉ ግንቦት መጀመሪያ ጀምሮ ኬንያ ዉስጥ የሚደደራደሩት ወገኖች የሥልጣን ክፍፍልንና የምርጫ ጊዜ ማራዘምን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባታቸዉን አስታዉቀዋል።ይሁንና ማቻር እንደሚሉት አዲሱ ረቂቅ ስምምነት በ2018 በተደረገዉ ሥምምነት ላይ ከመመሥረት ይልቅ የሚተካ መምሰሉ ተገቢ አይደለም።

 

ካይሮ-ለዳርፉር ችግረኞች ተጨማሪ ርዳታ ተላከ

በሱዳኑ የርስበርስ ጦርነት ለረሐብ ለተጋለጡ በተለይም ለዳርፉር ችግረኞች ተጨማሪ የምግብ ርዳታ መላኩን የዓለም ምግብ ድርጅት አስታወቀ።ዓለም አቀፉ የምግብ መርጃ ድርጅት እንደሚለዉ በርካታ ምግብ ጭነዉ ከቻድ የተጓዙ 10 ካሚዮኖች ዳርፉር ዉስጥ ለሚኖሩና ለተጠለሉ ችግረኞች እስከ ትናንት ድረስ እሕል ሲከፋፍሉ ሰንብተዋል።በተጋመሰዉ የግሪጎሪያኑ 2024 በቻድ በኩል ዳርፉር የገባዉ የርዳታ እሕል 5 ሺሕ ቶን መድረሱን ድርጅቱ አስታዉቋል።ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሚሉት በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ከቤት ንብረቱ ለተፈናቀለዉና በየቤቱ ለተቸገረዉ ሕዝብ የሚላከዉ የርዳታ መጠን አሁንም በቂ አይደለም።የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ዛሬ እንዳሉት ከርዳታዉ ማነስ በተጨማሪ ተፋላሚ ኃይላት በርዳታ አቅራቢዎች ላይ የሚያደርሱት ጫና አሳሳቢ ነዉ።

«የሰብአዊ ርዳታ ሠራተኞች ርዳታ ፈላጊዎችጋ ይደርሱ ዘንድ ሁሉም ወገኖች እንዲፈቅዱ ከልብ እንጠይቃለን።የተቸገሩትን ለመርዳት በተለይም ለሕዝቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ምግብና መሰል  ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ብዙ አካባቢ መድረስ አልቻልንም።ርዳታዉ ግን ፈጥኖ ካልደረሰ ግን ሕዝቡ በረሐብ ይጎዳል።መጀመሪያ ላይ እንደ አብዛኛዉ ሱዳናዊ ግጭቱ ባጭር ጊዜ ያበቃል የሚል ተስፋ ነበረኝ።አሁን ግን በጣም አሳሳቢ ሆኗል።»

የዓለም ምግብ ድርጅት እንደሚለዉ ለዳርፉር ችግረኛ ሕዝብ ሰሞኑን አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ መድረሱ አስጊዉን ረሐብ ለመቀነስ ጠቃሚ ነዉ።ድርጅቱ ባለፈዉ ግንቦት ባወጣዉ መግለጫ ዳርፉር ዉስጥ ብቻ በትንሽ ግምት 1.7 ሚሊዮን ሕዝብ ተርቧል።  

 

በርሊን-ጀርመን ሶስት ተጠርጣሪ ሰላዮችን አሰረች

የጀርመን አቃቤ ሕግ በሥም  ላልጠቀሰዉ ለዉጪ ሐገር የሥለላ ድርጅት ይሰልላሉ ብሎ የጠረጠሯቸዉን ሶስት ሰዎች አሰረ።የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ በመጀመሪያ ስማቸዉ የጠቀሳቸዉ ተጠርጣሪዎች የዩክሬን፣ የአርሜኒያና የሩሲያ ዜጎች ናቸዉ።ቢሮዉ አክሎ እንዳለዉ ተጠርጣሪዎቹ እዚሕ ጀርመን ሥለሚኖር አንድ የዩክሬን ዜጋ መረጃ ለማሰባሰብ ሲያደቡ ነበር።ሶስቱ ሰዎች የሚፈልጉትን ግለሰብ ለማግኘት ፍራንክፈርት ከሚገኝ ግለሰቡ በሚያዘወትረዉ አንድ ካፍቴሪያ ዉስጥ ባለፈዉ ሮብ ሲያዣብቡ ነበር።የተያዙትም የዚያኑ ቀን ነዉ።ሮብ።

 

ጋዛ-የእስራኤል ጦር ጋዛን መደብደቡ እንቀጠለ ነዉ

የእስራኤል ጦር የፍልስጤሞቹን ግዛት ጋዛ ሠርጥን መደብደቡን አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።የጋዛ የሰላማዊ ሰዎች መከላከያ ድርጅት እንዳስታወቀዉ የእስራኤል ጦር ዛሬ ከቀትር በፊት ጋዛ ከተማ ላይ በከፈተዉ ጥቃት በትንሽ ግምት አምስት የማዘጋጃ ቤት ሠራተኞችን ገድሏል።ጦሩ ትናንት ማምሻ ደቡባዊ ጋዛ ካሕንዮኖስ ከተማ ላይ በጣለዉ ቦምብና ሚሳዬል ቤቶችና ሕንፃዎችን አዉድሟል።በሰዉ ሕይወት ላይ ሥለደረሰዉ ጉዳት በአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በኩል የደረሰን ዘገባ አልጠቀሰም።የእስራኤል ጦር አዛዦች ጋዛ ዉስጥ ሁለት ተጨማሪ ወታደሮች እንደተገደሉባቸዉ ዛሬ አስታዉቀዋል።እስራኤል የሐማስን ጥቃት ለመበቀል ጋዛ ሠርጥ ላይ መጠነ-ሠፊ ጥቃት ከከፈተች ካለፈዉ መስከረም 26 ወዲሕ የተገደሉባት ወታደሮች ቁጥር 310 ደርሷል።እስራኤል፣ዩናይትድ ስቴትስ፣የአዉሮጳ ሕብረትና ብሪታንያ በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26 በደቡባዊ ስራኤል ላይ በከፈተዉ ጥቃት 1190 ሰዎች ገድሏል።ካገታቸዉ ሰዎች መካከል 160ዉ እስካሁን አልተለቀቁም።የእስራኤል ጦር ባንፃሩ ጋዛ ዉስጥ የገደላቸዉ ፍልስጤማዉያን ቁጥር ከ37 ሺሕ 400 በልጧል።ከ80 ሺሕ በላይ አቁስሏል።

 

ቤይሩት-የእስራኤል ጦር ከሒዝቦላሕ ጋር የሚደረገዉ ዉጊያ

የእስራኤል ጦር ከሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቦላሕ ጋር የገጠመዉ የዓየርና የሚሳዬል ዉጊያም እንደቀጠለ ነዉ።የሊባኖስ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት የእስራኤል ጦር ደቡባዊ ሊባኖስን ዛሬ በተዋጊ ጄቶችና በመድፍ ሲደበድብ አርፍዷል።የእስራኤል ጦር የዛሬዉን ጥቃት የከፈተዉ ሒዝቦላሕ ትናንት በሰሜናዊ እስራኤል ግዛት ላይ የከፈተዉን የሚሳዬል ጥቃት ለመበቀል ነዉ።ሰሜናዊ እስራኤልንና ደቡባዊ ሊባኖስን ያነደደዉ ጥቃትና አፀፋ ጥቃት በሰዉ ሕይወትና አካል ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ሥለመኖር አለመኖሩ የተባለ ነገር።ከመስከረም ወዲሕ የተባባሰዉ የእስራኤልና የሒዝቦላሕ ዉጊያ 60 ሺሕ እስራኤላዉያንን ከሰሜን እስራኤል፣ 90 ሺሕ ሊባኖሳዉያንን ከደቡብ ሊባኖስ አፈናቅሏል።በእስራኤልና በሒዝቦላሕ መካከል የሚደረገዉ ዉጊያ መናሩ ያሳሰባቸዉ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ የፊታችን ሰኞ ወደ አካባቢዉ ይጓዛሉ።

በሌላ ዜና አርሜኒያ ዛሬ ለፍልስጤም በይፋ የመንግስትነት እዉቅና ሰጥታለች።እስራኤል ርምጃዉን ተቃዉማለች።ለፍልስጤም በይፋ የመንግስትነት እዉቅና የሰጡት ሐገራት ቁጥር 146 ደርሷል።ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ጀርመንን የመሳሰሉ ኃይል፣ ሐብታም ሐገራት ግን እስካሁን ለፍልስጤም የመንግስትነት እዉቅና አልሰጡም።

እግር ኳስ

ዛሬ ሳምንት በደፈነዉ በዘንድሮዉ የአዉሮጳ የእግር ኳስ ሻምፕዮን ግጥሚያ ጀርመን ከምድብ A፣ ስጳኝ  ከምድብ B፣ ለጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ማለፋቸዉን አረጋግጠዋል።የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ለቀጣዩ ግጥሚያ ማለፉን ያረጋገጠዉ ከትናንት በስቲያ የሐንጋሪን ቡድን 2-ለ-0 አሸንፎ ነዉ።ስጳኝ ትናንት ከኢጣሊያ ጋር ገጥሞ ከጨዋታ ብልጫ ጋር የኢጣሊያ ባለጋራዉን 1-ለ-0 ረትቶ ለቀጣዩ ግጥሚያ አልፏል።ትናንትናዉኑ ከምድብ C ስሎቬኒያና ክሮኤሽያ 1-ለ-1፣ ዴንማርክና ኢንግላንድም 1 እኩል ተለያይተዋል።ዛሬ የዩክሬንና የስሎቫኪያ ቡድናት ገጥመዉ ዩክሬን 2-ለ-1 አሸንፋለች።ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ደግሞ ፖላንድና ኦስትሪያ ገጥመዋል።ማታ የኔዘርላንድስ ቡድን ከፈረንሳይ ጋር ይጋጠማሉ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።