1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ፍጥጫ

ሐሙስ፣ የካቲት 30 2015

«በአለማችን በተለያዩ ቦታዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ እነዚ ከባባድ ወንጀሎች በህግ የማይታዩ ከሆነ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚተላለፉ ከሆነ ህገ ወጥነት ህግ እየሆነ ይቀጥላል»

https://p.dw.com/p/4OT9d
Schweiz UN Menschenrechtsrat Tagung sitzungssaal
ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤትምስል picture-alliance/ dpa

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ፍጥጫ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመረምረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ኮሚቴ ሥራውን እንዲያቋርጥ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገው ግፊት እንዲቆም የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እየጠየቁ ነው። የሰብአዊ መብት ድርጅቶቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጄኔቭ ከተማ ለአምስት ሳምንታት በሚያካሂደው ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ኮሚሽኑ ሥራው እንዲቋረጥ ጥሪ ለማቅረብ መዘጋጀቷ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል። 63 የሚሆኑ ሲቪክ  እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ ለኮሚሽኑ በላኩት ግልጽ ደብዳቤ ያልተለመደ ያሉት የኢትዮጵያ መንግሥትን ሙከራ አባላቱ እንዳይቀበሉ አሳስበዋል።

የአምነስቲን ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ ወይዘሪት ሱአድ ኑር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አባላት እና ታዛቢዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራው ላይ የሚያደርገውን ግፊት ውድቅ እንዲያደርጉ ይጠይቃሉ።«ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ለኅብረቱ አባላት ኢትዮጵያ ኮሚሽኑ እንዲበተን የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጠይቀው ነበር » ይላሉ ወይዘሪት ሱአድ ነገሩ በጣም  አስደንጋጭ ስለሆነ ነው  የሰብአዊ መብት ተማጋቾች ፊርማ ያሰባሰብነው ብለዋል  ። «ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላትን እና ታዛቢዎች  ልታቀርብ የተዘጋጀችውን ሀሳብ  ውድቅ እንዲያደርጉ  አሁንም እንጠይቃለን  ምክንያቱም ይህ አጣሪ ኮሚቴ የሚያደርገው ምርመራ በጣም አስፈላጊነው » ሲሉ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል ።

የሕግ ባለሙያ የሆኑት መሀመድ ኑር አብዱል ከሪም በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለችው ጥያቄ  በመንግሥታት ድርጅቱ ተቀባይነት ካገኘ « ሕገወጥነት ህግ  ይሆናል»  ሲሉ። የሁኔታውን አስከፊነት እንዲ ሲሉ ገልጸዋል «በአለማችን በተለያዩ ቦታዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ እነዚ ከባባድ ወንጀሎች በህግ የማይታዩ ከሆነ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚተላለፉ ከሆነ ህገ ወጥነት ህግ እየሆነ ይቀጥላል ያደግሞ ለሰው ልጆች መኖር አዳጋች ነው የሚሆነው »ይላሉ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ መሀመድ አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን ሊያቀርብ ይችላል ነገር ግን ተቀባይነት አያገኝም ሲሉ ግምታቸውን ተናግረው ነገር ግን ይላሉ የህግ ባለሙያው «ተቀባይነት ካገኘ አለምን የሚለውጥ ተፅእኖ ይኖረዋል ምክንያቱም ወንጀል የሰራ ሰው ወንጀሉን ይዞ የሚኖር ከሆነ ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው » ብለዋል።

«ተጠያቂነትን መሸሽ አይቻልም» የሚሉት ሌላው ዶቼ ቬሌ ያነጋገራቸው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያድ አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያምን «የሚጣሩት ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚያስጠይቁ» መሆናቸውን ያመለክታሉ።« የሰብአወ መብቶች ያነሷቸው ጥያቄዎች ትክክለኛ ጥያቄ ነው» ይላሉ አቶ ያሬድ   ምክንያታቸውን ሲገልጹ «በጣም የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚፈጸም ግዜ በማንኛውም ሃገር ላይ ጥሰቶቹ በገለልተኛ በሆነ ኤክስፐርቶችን ይዞ ባለ ድርጅቶች እንዲያጣሩት ይደረጋል »ይላሉ

ኢትዮጵያ ላይም ይደረግ የተባለው ተመሳሳይ ነገር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ያሬድ ምርመራው መደረጉ ይሳካል አይሳካም የሚለው ጉዳይ የሚወሰነው በተባበሩት በመንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በሚደረገው የጫና መጠን ነው ሲሉ ። «የሚጣሩት ወንጀሎች በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚያስከስሱ ናቸው » ያሉት አቶ ያሬድ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚያስከስስ ከሆነ በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ አካላት በሙላ በመጨረሻ ላይ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል ።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀሳብን ለማካተት ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም በተሰጡት የተለያዩ ምክንያቶች የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ባለማግኘታችን ማካተት አልቻልንም። የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ኮሚቴን ከጥንስሱ ጀምሮ ተቀባይነት እንዳልሰጠው የሚታወስ ነው።

ማኅሌት ፋሲል 

ሸዋዬ ለገሠ