1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሰላም ጥሪ አደባባይ የወጣው የሰላሌ ህዝብ

ዓርብ፣ ነሐሴ 17 2016

በሰላም እጦት የተማረሩ የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ ከተማ ነዋሪዎች በባህላዊ መንገድ ለሰላም ጥሪ ለማድረግ አደባባይ ወጣ፡፡ በዚህም የሰላም ጥሪ ስነ ሥርዓት ላይ በግራም በቀኝም ያሉ ወደ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲገቡ ጥሪ ተላልፏል።

https://p.dw.com/p/4jjcb
Infografik GRAPHIC Karte Amuru Woreda, Äthiopien
ምስል DW

በባህላዊ መንገድ የሰላም ጥሪ

ይህ ስለ ሰላም የሚጣራው የሰላሌ ህዝብ ድምጽ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በአንድ ጊዜ ተስተጋብቷል፡፡ በተለይም በወተት ምርቱና በድልብ ባህላዊ እሴቱ የሚታወቅ ይህ አከባቢ ሰላም ርቆት የችግር ቋጥኝ መሸከም እንደሰለቸው ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።
በዚህ ምሬታቸው ገደብ ያጣው የዞኑ ነዋሪዎች በተለያዩ ወረዳዎች በባህሉ ክብር የሚሰጣቸው ባህላዊ መሣሪያዎችን ይዘው ከሰሞኑ አደባባይ ወጥተው ልመናቸውን ሲያቀርቡ፤ የሰላም ጥሪያቸውንም ሲያስተጋቡ ነው የተስተዋሉት፡፡ 

የማህበረሰቡ ጥሪ፤ ለሰውም ለፈጣሪም…

ይህ እንኳ ምን እንደሚያመጣብን አናውቅም ብለው አስተያየታቸውን እንጂ ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት የደብረሊባኖስ ወረዳ የአገር ሽማግሌና አባገዳ፤ የልመናችን ዋናው ዓለማ ‘ከፈጣሪያችን ምህረት ለማግኘት ነው’ ብለዋል፡፡
“ሰላም ናፈቀን፤ ሰው በየቦታው ይገደላል፡፡ መታሰር፤ መዘረፉም ከፋ፡፡ ነጋዴ ገበያ ለመሄድ ፈራ፡፡ ያለው ተኝቶ አያድርም በየቦታው ስቃይ ነው፡፡ በጫካ ያሉ ልጆቻችን ያንን ትተው እንዲገቡ፤ ሲገቡም መንግስት እንዳያስፈራራና ይቅር ብሎ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቅላቸው ጠይቀናል፡፡ ከታጣቂዎቹ ጋር የተመሳሰሉ ዘራፊዎችም በመበራከት ሌሊት እንቅልፍ ነስተውን  እየዘረፉን ስለሆነ ያ አስገድዶን አደባባይ ለተማጽእኖ ወጣን” ብለዋል፡፡

የተከበሩ ባህላዊ ቁሳቁስና የሚቀርብ ተማጽእኖ

በሰሞነኛው ክስተቱ ህዝቡ ጫጩና ጦር ጋሻ ይዘው፤ ልጅ እንደ በሬ በቀንበር ተጠምደው ህብረተሰቡ ተማጽኖውን ሲያስተጋባ ታይቷል፡፡ የአገር ሽማግሌው በአስተያየታቸው ይህ ሁለት ዓለማ ያለው ነው ይላሉ፡፡  
“አንድም ፈጣሪን ምህረትህን ላክልን ብለን ስንማጸን፤ በሌላም ታጥቀው በጫካ ያሉ ልጆቻችን መከራው በቃን በሰላም ግቡና ሰላም ስጡን ብለን መልእክት ለማስተላለፍ ስለፈለግን ነው” ብለዋል፡፡ “እንደ ወትሮው ዝናብ ሲጠፋ ቦና ስሆን ጫጩና ከሌቻ ተይዞ ልጅም እንደ በሬ ተጠምዶ፤ ፈረስ ተለጉሞ፣ እናቶች እሺህን ለብሰው ነበር ለልመና የምንወጣው” ያሉት አስተያየት ሰጪው የአገር ሽማግሌ “አሁን ግን ፍቅር ሲጠፋ፣ እናት ስትደፈር፣ አባቶች ሲገዳደሉ አላባራ ያለው ስቃይ ሁል ጊዜ የማይደረግ ነገር ግን በጭንቅ ወቅት የሚደረግ ነገርን ለማድረግ አስገደደን” በማለትም ሃሳባቻውን አከሉ፡፡ የሰላም ጥሪው የተላለፈም “ታጥቀው በበረሃው ላሉ ልጆቻችን እና በሰላምም ስፍራ ተቀምጠው ሰላም ለሚነሱን ነው” ሲሉ የአገር ሽማግሌው የደብረሊባኖስ ወረዳ ነዋሪ አስረድተዋል፡፡

በኦሮምያ ክልሉ ግጭት የሲቪል ዜጎች ፈተና


ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ሃዳ ሲንቄ በበኩላቸው “እኛ አገር ተጎድታለች፡ ሰው ተገደለ ተፈናቀለ  እርቅ ቢወርድልን ብለን ማንም ቤት አልቀረም ሁሉም ሰልፍ ወጣ፡፡ ህጻን ጠምደን፤ ባልቴት እሺህ አሸክመን ያለንን ሁሉ ወግ ተጠቅመን ለጥሪ አደባባይ ወጥተናል፡፡ ሰው  እየተያዘም ብር ይጠየቃል፤ ጎጆ ሁሉ ባዶ ቀርቷልና ከዚህ ምን ቀረን ብለን ወጣን” ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡ ተስፋ- እርቅ፤ አሊያም ቁጣን ከፈጣሪ..

ጥሪው ለፈጣሪም፤ ሰላም ለነሳን ሰውም ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ባህሉን ወጉን የሚያውቅ ካለ ጥሪውን ይቀበላል የሚል እምነታቸውንም አንጸባርቀዋል፡፡ በዚህ ሰላም ካልወረደም ቁጣውን ከፈጣሪያቸው እንደሚጠብቁ በማስረዳት፡፡ የደገም ወረዳ አንድ አስተያየት ሰጪ የአገር ሽማግሌም አስተያየታቸውን አከሉ፡፡ “ጥሪያችን ሰላም ይውረድ ነው፡፡ ሰማይና ምድር ሆይ የተጣሉትን አስታርቅልን ነው ያልነው” ብለዋል፡፡ 
ዶይቼ ቬለ ስለ ህብረተሰቡ ምሬትና መልእክት በማስመልከት ለዞኑ ባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች እንዲሁም ለዞኑ ጸጥታ አስተዳደር በመደወል ተጨማሪ መረጃዎችን ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡  
ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንግስት ሸነ ያላቸውና እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች በስፋት ከሚንቀሳቀሱበት ዞኖች ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ዞን እንደ ኩዩ፣ ደገም፣ ሂደቡ አቦቴ፣ ወራጃርሶ፣ ግራር ጃርሶ፣ ዳራ እና ያያ ህብረተሰቡ በዚህ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ከወደቀም ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ በነዚህ አከባቢዎች፣ ዞኑን በሚያቋርጠው አውራ መንገድ እና በመላው ዞን ሰዎች ታግተው ገንዘብ መጠየቅም የተለመደ ተግባር መሆኑ ተደጋግሞ የተዘገበ ጉዳይ ነው፡፡


ሥዩም ጌቱ 
ልደት አበበ
ዮሃንስ ገብረእግዚዓብሄር