1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የረቡዕ የግንቦት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ረቡዕ፣ ግንቦት 21 2016

አማራ ክልል ውጊያ መኪያሄዱ፤ ትግራይ ክልል የምግብ ርዳታ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መቸገራቸው፤ ደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምርጫ መከናወኑ፤ የየመን ሁቲ አማጺያን ስድስት መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ማሳወቃቸው፤ ኢራን ለየመን ሁቲዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ ማረጋገጧ፤ ኒጀር የሚገኘው የጀርመን የአየር መጓጓዣ ጣቢያ አገልግሎት መስጠቱ ይቀጥላል መባሉ፤ ደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምርጫ መካሄዱ እንዲሁም ኒጀር የሚገኘው የጀርመን የአየር መጓጓዣ ጣቢያ አገልግሎት መስጠቱ ይሰኛል ።

https://p.dw.com/p/4gQqs

የረቡዕ የግንቦት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

አርዕስተ ዜና

*ሰሞኑን በአማራ ክልል አንዳንድ የጎጃም ዞን ወረዳዎች ውስጥ የነበሩ ውጊያዎች አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ገለጡ ።

*ትግራይ ክልል ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ርዳታ እንደሚሹ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮምሽን ዐስታወቀ ።

*በደቡብ አፍሪቃ ከዘር መድልዎ (አፓርታይድ) አገዛዝ ወዲህ እጅግ ፉክክር የታየበት ብሔራዊ ምርጫ ዛሬ ተካሄደ ።

*የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር፤ በሜዲቴሪያን እና ከአደን ባህረ ሠላጤ ወዲያ በአራቢያን ባሕር ላይ ስድስት የንግድ መርከቦችን ማጥቃታቸውን ዛሬ ዐስታወቁ ።  የኢራን አብዮታዊ ዘብም (IRGC) ለየመን ሁቲዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያቀርብ እንደነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ አረጋግጧል ።

ዜናው በዝርዝር

ደንበጫ፥ አማራ ክልል ውጊያ

ሰሞኑን በአማራ ክልል አንዳንድ የጎጃም ዞን ወረዳዎች ውስጥ የነበሩ ውጊያዎች አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ገለጡ ። ውጊያዎቹ ሰሞኑን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞንና ምስራቅ ጎጃም ዞን አንዳንድ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል መደረጋቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ በምስራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማ ነዋሪ፦ ባለፈው እሁድና ሰኞ በከተማዋ ሁለት አቅጣጫዎች ውጊያዎች እንደነበሩ በስልክ ተናግረዋል ።

«እሁድና ሰኞ ነው ተኩስ የነበረው፣ የተቃጠለ ቢሮም አለ ።  ሁለት ቀን ሙሉ ነበር ። ተኩሱ፤ እስከ ትናንት ምሽትም ውጊያ ነበረ ።»

በጎጃም ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን እንደገና በተቀሰቀሰው የፀጥታ መደፍረስ መንገዶች በመዘጋታቸው እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል ። የተኩስ ልውውጥ በነበረባቸው ፈረስ ቤትና ደንበጫ ከተሞች ውጥረቶች እንዳሉ አስተያየት ሰጪዎች ገልጠዋል ። የባሕር ዳር ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ስለሰሞኑ ውጊያ ተጨማሪ አስተያየት ከመንግስትም ሆነ ከፋኖ ታጣቂዎች ለማካተት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም ።

መቐለ፥ ትግራይ ክልል የምግብ ርዳታ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መቸገራቸው ተገለጠ

ትግራይ ክልል ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ርዳታ እንደሚሹ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮምሽን ዐስታወቀ ። በክልሉ ከሚገኙ ከአጠቃላይ ርዳታ ፈላጊዎች ለ3 ሚሊዮን ዜጎች በዓለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎች አጋዦች ርዳታ እየቀረበ መሆኑ ተዘግቧል ። ሆኖም የተቀሩት 1 ነጥብ 5 ሚልዮን ነዋሪዎች ግን አሁንም ያለ ምንም ድጋፍ ችግር ላይ መሆናቸው ተገልጿል ። በሌላ በኩል ርዳታ ሊቀርብላቸው እየተገባ በበላይ አካል ውሳኔ መሰረት በተባለ፥ ወደ ትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ኦፍላ እና ዛታ አካባቢዎች የምግብ ርዳታ አቅርቦት ከቅርብ ግዜ ወዲህ እንዲቋረጥ መደረጉም በዞን አስተዳደሩ ተጠቅሷል ። የመቐለ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ እንደዘገበው፦ በአካባቢው የፀጥታ ችግር ሳይኖር እና ግለፅ ምክንያት ሳይቀመጥ የምግብ ርዳታ አቅርቦት ተቋርጧል ። በዜና መጽሄት ተጨማሪ ዘገባ ይኖረናል ።

ጆሐንስበርግ፦ ደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ምርጫ ተካሄደ

በደቡብ አፍሪቃ ከዘር መድልዎ (አፓርታይድ) አገዛዝ ወዲህ እጅግ ፉክክር የታየበት ብሔራዊ ምርጫ ዛሬ ተካሄደ ። በዘንድሮ ምርጫ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመሩት የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ANC) አብላጫ ድምፅ እንደሚያጣ ተገምቷል ። በትምሕርት ቤቶች፤ በማኅበረሰብ ማእከላት እና በሰፋፊ ድንኳኖች ውስጥ የተኪያሄደው የዛሬው ምርጫ በደቡብ አፍሪቃ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ እጅግ ወሳኝ ነው ተብሏል ። 62 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት ደቡብ አፍሪቃ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1994 የአፓርታይድ መወገድ ወዲህ አብዛኛው ወጣቱ ትውልድ በመንግሥት አስተዳደር ቅሬታ እንደገባው ይነገራል ። ሆኖም በዛሬው ምርጫ፦ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ ፓርቲያቸው አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥታቸው እንደሚቀጥል አንዳችም ጥርጥር እንደሌላቸው ተናግረዋል ።

«ይህ ደቡብ አፍሪቃውያን የሚወስኑበት ቀን ነው፤ ማን የደቡብ አፍሪቃን መንግሥት እንደሚመራ ስለ ሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑበት ። ምንም ይሁን ምን ሕዝቡ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በድጋሚ ሀገሪቱን መምራቱን እንዲቀጥል ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳማይል በልቤ አንዳችም ጥርጣሬ አይገባም ። »

የዛሬው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ከ27 ሚሊዮን በላይ ደቡብ አፍሪቃውያን መመዝገባቸውም ተጠቅሷል ። የዛሬው ምርጫ ከ23,000 በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እስከ ምሽቱ ሦስት ሰአት ድረስ እንደሚከናወን ተገልጧል ።

አደን፥ የየመን ሁቲ አማጺያን ስድስት መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ዐሳወቁ

የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር፤ በሜዲቴሪያን እና ከአደን ባህረ ሠላጤ ወዲያ በአራቢያን ባሕር ላይ ስድስት የንግድ መርከቦችን ማጥቃታቸውን ዛሬ ዐስታወቁ ።  ዛሬ ጥቃት ከደረሰባቸው መርከቦች መካከል የግሪክ ግዙፍ የንግድ መርከብም ይገኝበታል ። ከየመን የባሕር ጠረፍ አቅጣጫ በሁቲ አማጺያን በተወነጨፈ ሚሳይል ትናንት አንድ የማርሻል አይላንድ ባንዲራ የሚያውለበልብ መርከብም መጎዳቱን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ። አማጺያኑ ጥቃቱን ያደረሱት በጋዛ ሠርጥ ራፋህ ከተማ ላይ እሥራኤል ለምትወስደው ድብደባ አጸፌታ ነው ብለዋል ። የሑቲ አማጺያን በኢራን ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በተደጋጋሚ ይነገራል ።

ቴሕራን፥ ኢራን ለየመን ሁቲዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋገጠች

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC) ለየመን ሁቲዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያቀርብ እንደነበር ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋገጠ ። ታስኒም የተሰኘው የዜና ምንጭን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት (dpa)ዛሬ እንደዘገበው የጦር መሣሪያ አቅርቦቱ ከጦር መርከቦች ላይ የሚወነጨፍ የጋህዳር ተምዘግዛጊ ሚሳይልንም  ያካትታል ። የኢራን አብዮታዊ ዘብ፦ ሚሳይሉ 2000 ኪሎ ሜትሮች ርቀት በመምዘግዘግ የኢራን ቀንደኛ ያላቸው ጠላቶች ዩናይትድ ስቴትስ እና እሥራኤልን በቀጣናቸው አዲስ ተግዳሮትን ያጋፍጣል ብሏል ። የሑቲ አማጺያን ከእሥራኤል ጋ ግንኙነት አላቸው የሚሏቸው እና  በዋናነትም በቀይ ባሕር በሚቀዝፉ የንግድ መርከቦች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ይሰነዝራሉ ። 

ኒያሜ፥ ኒጀር የሚገኘው የጀርመን የአየር መጓጓዣ ጣቢያ አገልግሎት መስጠቱ ይቀጥላል

የጀርመን መከላከያ ኒዤር ኒያሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ የአየር መጓጓዣ ጣቢያው በአሁኑ ወቅት አገልግሎት መስጠቱ እንደሚቀጥል ዐስታወቀ ። የጀርመን ጦር በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ስለሚቆይበት የሽግግር ጊዜ ጀርመን እና ኒዤር ትናንት መስማማታቸውን የፌዴራል ጀርመን መከላከያ ሚንሥትር ይፋ አድርግል ።  በስምምነቱ መሠረት፦ የአየር መጓጓዣ ጣቢያው ለጊዜው ከዓርብ ግንቦት 23 ባሻገርም አገልግሎት መስጠቱ ይቀጥላል ተብሏል ።  ኒያሜ የሚገኘው የጀርመን የአየር መጓጓዣ ጣቢያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘርፈ-ብዙ የተቀናጀ ማሊን የማረጋጋት ተልእኮ (MINUSMA) የሰላም አስከባሪ ጓድ አካል ነው ። ኒዤር ውስጥ ወታደራዊ ኹንታ መፈንቅለ መንግሥት ካደረገ በኋላ የፈረንሣይ ወታደሮች ሀገሪቱን ለቅቀው ወጥተዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችም እስከ መስከረም መገባደጃ ድረስ ከኒዤር መውጣታቸው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ። የኒዤር ወታደራዊ ኹንታ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙምን ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ ፊቱን ወደ ሩሲያ አዙሯል ።

ኒያሜ፥ ኒጀር የሚገኘው የጀርመን የአየር መጓጓዣ ጣቢያ አገልግሎት መስጠቱ ይቀጥላል

በመጨረሻም የስፖርት ዜና፦ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ሐንሲ ዲተር ፍሊክ ከስፔኑ ግዙፍ የእግር ኳስ ቡድን ባርሴሎና የተባረሩት አሰልጣኝ ዣቪ ሔርናንዴዝን መተካታቸው ታወቀ ። የ59 ዓመቱ ጀርመናዊ አሰልጣኝ የባርሴሎና ቡድንን እንዲያሰለጥኑ የሁለት ዓመት ውል ፈርመዋል ። ዲተር ሐንሲ ፍሊክ እንደጎር ጎሪዮስ አቆጣጠር በ2023 መስከረም ወር ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው ከተሰናበቱ በኋላ የትኛውንም ቡድን አላሰለጠኑም ። የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ ዣቪ ሔርናንዴዝ መሰናበታቸው የተገለጠው ዐርብ እለት ነበር ። ያሰለጥኑት የነበረው ቡድናቸው ባርሴሎና በስፔን ላሊጋ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ያጠናቀቀው ከዋንጫ ባለድሉ ሪያል ማድሪድ በዐሥር ነጥብ ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ ነው ። አዲሱ የባርሴሎና አሰልጣኝ የጀርመኑ ባዬር ሙይንሽን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 የሻምፒዮንስ ሊግ፤ የጀርመን ቡንደስሊጋ እና የጀርመን ዋንጫዎችን እንዲያነሳ አስችለዋል ። ሆኖም በጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ቆይታቸው በተለይም በወዳጅነት ባደረጓቸው ግጥሚያዎች ለተደጋጋሚ ሽንፈት መዳረጋቸው ይታወሳል ።

ማተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።