1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምግብ ዋጋ መናር በአፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 23 2014

የምግብ ዋጋ በመላው ዓለም ላለፉት ሁለት ዓመታት እየጨመረ መሄዱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይኽ ደግሞ በተለይ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲንር ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው። የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ ድርቅ እና መሰል ምክንያት ይቀርባሉ። የኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ፈተና ላይ ወድቋል።

https://p.dw.com/p/4C6Nb
Libyen I Bunter Markt in Tripolis
ምስል McPhotoStr/Bildagentur-online/picture alliance

የምግብ ዋጋ መናር በአፍሪቃ

በኬንያዋ ዋና መዲና ናይሮቢ ውስጥ የሚገኘው አነስተኛ ኪዮስክ በየቀኑ ማለዳ ትኩስ ቻፓቲ ማለትም ቂጣ አዘጋጅቶ በማቅረብ ይታወቃል። በርካታ ደንበኞችም አሉት። ለወትሮው የቻፓሪው ዋጋ 20 የኬንያ ሺልንግ ወይም 8,92 የኢትዮጵያ ብር ነበር። አሁን ግን ዋጋው በእጥፍ በመጨመሩ ደንበኞች እንደበፊቱ ሊገዙ አልቻሉም። ጎረቤት ኬንያ ውስጥ ቻፓቲ እና ዳቦ ለገበያ የሚያቀርበው መጋገሪያ ቤት ኃላፊ ሳሙኤል ሞሴ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት የስንዴ እና የሱፍ ዘይት ዋጋ ከጨመረ ቢሰነባብትም የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ችግሩን አባብሶታል።

«የጦርነቱን ሁኔታ እየተከታተልን ነው፤ ምክንያቱም ምን እንደሚሆን ማወቅ አለብን። ከምንጠቀምባቸው ምርቶች አንዳንዶቹ ከእነዚህ ሃገራት የሚመጡ ናቸው፤ መላው ዓለም ስጋት ላይ ነው።»

ኬንያ ውስጥ ለሕዝብ ፍጆታ ከሚውለው ስንዴ አንድ ሦስተኛው እጅ የሚመጣው ከሩሲያ እና ዩክሬን ነው። በዓለም ገበያ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ለገበያ አዳራሾች ዳቦ በሚያቀርበው ኬናፍሪክ ዳቤ ቤት አገልግሎት ላይም ጫናውን አሳርፏል።

Serbien l Landwirtschaft in der Krise
ምስል Jelena Djukic Pejic/DW

«ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ነው፤ ምክንያቱም ዋጋው ብቻም አይደለም በቀጣይ የሚያነጋግረው አቅርቦቱስ አለ ወይ የሚለውም ነው። ዋነኛ አቅራቢ የነበሩ ድርጅቶች ከዚህ በፊት ለማቅረብ የተስማሙበትን ውል ሁሉ ሲቀንሱ አስተውለናል።»

አክሽን ኤይድ በተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፖሊሲ አስተባባሪ የሆኑት ቴሬሳ አንደርሰን እንደሚሉት የአብዛኛው የአፍሪቃ ሃገራት ኤኮኖሚ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፤ በአየር ንብረት ቀውስ ፣ በሰብዓዊ ወይም በፖለቲካ እና ኤኮኖሚ አለመረጋጋቶች ከደረሰበት ጉዳት አላገገመም። በዚያ ላይ የዩክሬን ጦርነት ሲታከልበት ችግሩን እንዳባባሰውም ያስረዳሉ።

«በመሠረቱ ይኽ የዋጋ መናር አሁንም ሆነ ለረዥም ጊዜ በሚባል ደረጃ ምን ያህል ሕይወታቸው ላይ ጫና እንዳሳደረ ቤተሰቦች ሲናገሩ ማዳመጡ አሳዛኝ እና ልብን የሚሰብር ነው። ለምሳሌም ወላጆች በተለይም እናቶች አይበሉም፤ እየራባቸው ነው የሚሄዱት፤ ካላቸው ገቢ አብዛኛውንም ለምግብ መግዣ የሚያውሉት ከሆነም ብዙዎቹ ለልጆቻቸው የትምህርት ቤት መክፈል እንደማይችሉም ነው የተነገረው። በዚህም ምክንያት ልጆች ትምህርታቸውን እየተው ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ሥራ ፈልገው ማግኘት ይኖርባቸዋል። ሰዎች ብዙ ተበድረው ባለዕዳ እየሆኑ ነው።»

Malawi Markt Preissteigerung
ምስል Reuters/M. Hutchings

ከዚህም ሌላ በጋዝ ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ ያስከተለው የዋጋ ንረት ከሌላው ዓለም ይልቅ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ተጽዕኖው ከፍ ብሎ እየታየ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። ለምሳሌ ዚምባብዌ ላይ የታየው የጋዝ ዋጋ ጭማሪ ከሦስት እጅ እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑንም አንስተዋል። የፓስታ እና መኮሮኒ ዋጋም በእጥፍ መጨመሩንም ገልጸዋል። አንደርሰን እንደሚሉትም ከአሁኑ አፍሪቃ ውስጥ የአቅርቦት ቀውስ መታየት ጀምሯል። በዚህ ላይ ለውጥ የማይኖር ከሆነም ርሃብ ሊያሰጋ እንደሚችልም ጠቁመዋል። በተለይም በአፍሪቃው ቀንድ ሃገራት አካባቢ በቀጠለው ድርቅ ምክንያት ወደ 20 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ከወዲሁ ከከባድ ርሃብ አደጋ ጋር መፋጠጡንም አመልክተዋል። በተመድ የዓለም የምግብ መርሃግብር በእንግሊዝኛ ምህጻሩ WFP ም ተመሳሳይ ግምገማና ስጋቱን ይፋ አድርጓል። በሶማሊያ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ፔትሮክ ዊልተን እንደሚሉት በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት በድርቅ ምክንያት ከብቶች በመሞታቸው እና ከእርሻም የተገኘው ምርት ከተለመደው በአማካኝ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ የምግብ ዋጋ በጣም ጨምሯል። በዚህ ላይ በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት ከውጪ የሚገባው የስንዴ ምርት እንዲቀንስ በማድረጉ የምግብ ዋጋው ቀውስ እንዲባባስ ተጨማሪ መንስኤ መሆኑንም አመልክተዋል።

Symbolbild I Indien Weizen
ምስል abaca/picture alliance

WFP እንደሚለው ሶማሊያ ውስጥ ሰብዓዊ ቀውስን ሊያስከትል የሚችለው ሁኔታ ተባብሷል። 6 ሚሊየን ሕዝብ ለከፋ የምግብ ዋስትና ስጋት ተጋልጧል። ከዚህ ውስጥ 1,6 ሚሊየን የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው። እነዚህን ለመርዳት የረድኤት ድርጅቶች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ባስቸኳይ ካላገኙ በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ ሶማሊያ ውስጥ የከፋ ርሃብ ሊከሰት እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

ሺሪሲዮ ኢዶሎ መሀመድ ከወዲሁ የርሀብ ቀውሱን ሙሉ ኃይል ቀምሳዋለች። ሶማሊያዊቱ እናት ከሦስት ልጆቿ ጋር በመሆን የተጎሳቆለውን መንደሯን ለቅቃ ለ15 ቀናት በዚያ በረሃ በእግሯ ትንሽ ውኃ እና ምግብ ብቻ ይዛ በመጓዝ ተሰቃይታለች። ነገር ግን ሁለቱ ልጆቿ በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተጉዘው ደቡብ ሱማሊያ ጌዶ ግዛት ዶሎው ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው አዲስ ለተፈናቃዮች ከተዘጋጀው መጠለያ መድረስ አልቻሉም።  

Somalia | Hungersnot
ምስል Mariel Müller/DW

«ብዙ ተጓዝን፤ ልጄ በጣም ውኃ ጠምቶች ደከመ። ደጋግሞ እማዬ ውኃ ፤ እማዬ ውኃ ሲል ጠየቀኝ። ያለከልክ ጀመር፤ ሆኖም ልሰጠው የምችለው ጠብታ ውኃ እንኳ አልነበረኝም።»

የስምንት አመቱ ሕጻን ከመጠለያ ጣቢያው ሲደርስ አረፈ። በረዥሙ ጉዞ የተዳከመ ሲሆን ከባድ ሳልም ሲያሰቃየው ነበር። በWFP መረጃ መሠረት ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በድርቁ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ትተው ተሰደዋል።

የዝናብ እጥረት ካስተከተለው ተጽዕኖ በተጨማሪ በጦርነት ምክንያት ያልታረሱ አካባቢዎች ባሉባት ኢትዮጵያም የምግብ ዋጋው በየሳምንቱ የሚጨምር እንደሚመስል ብዙዎች ይናገራሉ። የዋጋው ንረት ካነጋገርናቸው አንዱ በንግድ ሥራ የተሰማራ ወጣት ከጅምላ አቅራቢዎች ገንዝቶ ለተጠቃሚዎች በማቅረቡ ሂደት ያስተዋለውን ለመናገርም ይከብዳል ነው ያለው።

ሌላዋ አስተያየቷን የጠየቅናት በንግዱ ዘርፍ የተሰማራች ብትሆንም የህዝቡ የዋጋ ንረቱን ተቋቁሞ መኖር አስደናቂ ነው ትላለች። የዳቦን ዋጋ በምሳሌነት ያቀረበልን ተጠቃሚ በበኩሉ የምግብ ዋጋ በጣም ጨምሯል ባይ ነው።

በእርግጥም ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ አቅም መዳከሙን በሺህዎች የሚቆጠር ብር ይዘው ለሸመታ ገበያ የወጣ ሁሉ በፌስታል የማይሞላ ነገር ገዝቶ ሲመለስ በግልጽ ያስተውለዋል። እንደተባለው ህዝቡ ግን በይብስ አታምጣ ተመስገን እያለ ያለውን እየተካፈለ ቀኑን ይገፋል።

Niger Hungerkrise
ምስል AP

ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ደግሞ የጸጥታ ይዞታው ሁኔታ የምግብ አቅርቦትን እያደናቀፈ ነው። ለምሳሌ እንደ ኒዠር ባሉ ሃገራት ቦኮ ሃራም ባሉ የአሸባሪ ድርጅቶች ጥቃት ምክንያት ገበሬዎች ማሳዎቻቸውን ማረስ እንዳልቻሉ እየተነገረ ነው። የኦክስፋም ኒዠር ዳይሬክተር የሆኑት አሳላማ ዳዋላክ ሲዲ በአካባቢው ሰብዓዊ እልቂት ከመከሰቱ አስቀድሞ አፋጣኝ ርምጃ ያስፈልጋል እያሉ ነው።

«ይኽ ለዓለም የማስጠንቀቂያ ደወል ነው። ባለፉት አስርት ዓመታት ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ 27 ሚሊየን ሕዝብ ለከፋ የምግብ ቀውስ መጎዳቱን እየተመለከትን ነው።»

Afghanistan humanitäre Hilfe
ምስል Saifurahman Safi/Xinhua/picture alliance

አክለውም አንዳች ነገር ካልተደረገ ቁጥሩ አሁን ወደ 38 ሚሊየን ከፍ ሊል እንደሚችልም አጽንኦት ሰጥተዋል። እሳቸው እንደሚሉትም በቂ ክምችት በመኖሩ የስንዴ አቅርቦት ሊቀንስ አይገባም ነበር። ለምሳሌ የዘርፉ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ቻይና በመጋዘኗ ውስጥ የዓለም ክምችትን ግማሽ የሚሆን ስንዴ አጠራቅማ አስቀምጣለች። የኪል ኢንስትቲዩት የዓለም ኤኮኖሚ ባለሙያ ሄንድሪክ ማሀልኮቭ እንደሚሉት ከሆነም ቻይና በአቅርቦቱን ረገድ ለደሀ የአፍሪቃ ሃገራት ድጋፍ እንደምታደርግ ይጠበቃል። በዚህም በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ያላት ተጽዕኖ ይጨምራል።

ሚያዚያ ወር ላይ የዓለም ባንክ ባወጣው የምግብ ሸቀጥ ዋጋ መዘርዝር መሠረት በመላው ዓለም የምግብ ዋጋ በመጋቢት እና ሚያዝያ ወር ላይ ከቀደሙት ወራት ከነበረው በ15 በመቶ መጨመሩን ያመለክታል። ለዚህም በዋናነት የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ተጠያቂ ያደርጋል።

 ሸዋዬ ለገሠ