1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክአፍሪቃ

ዮሃና ኤርሚያስ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መጋቢት 23 2014

ዮሃና ኤርሚያስ እቁብ የተባለው አፕሊኬሽን ወይም መተግበሪያን ከሰሩት አንዷ ናት። ዮሃና እና ባልደረባዋ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ይኼን እቁብ ጣዮችን የሚገናኘውን መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች ያስተዋወቁት። ዮሃና የህክምና ሙያ ትምህርቷን ሙሉ ለሙሉ ሳታጠናቅቅ የሶፍትዌር ባለሙያ ለመሆን ለምን ወሰነች? ዕቅዷስ ተሳክቶ ይሆን?

https://p.dw.com/p/49Ggr
Äthiopien Addis Abeba eQUB financial technologies
ምስል eQUB financial technologies

ዮሃና ኤርሚያስ ለቴክኖሎጂ ልዩ ፍቅር አላት። ያለፉትን አምስት አመታት ያሳለፈችው ቴክኖሎጂያዊ መፍትሄዎችን በማፈላለግ ነው። ለምሳሌ ከአንድ ዓመት በፊት እርሷ እና አሌክሳንደር ይሳቅ የተባለው ባልደተባዋ በጋራ ፤ ሰዎች በልዩ አፕሊኬሽን ወይም መተግበሪያ አማካይነት እቁብ መጣል የሚችሉበትን መንገድ አመቻችተዋል። ብዙዎች ዮሃናን የሚያውቋት የእቁብ መተግበሪያ ተባባሪ መስራች እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ሆና ስትሰራ ነው።ከዚህም ሌላ ወጣቷ ሶፍትዌር ላይ ተጠቃሚዎች የሚያዩትን የፊት ለፊት ገፅ ዲዛይን ማድረግ ይበልጥ ያስደስታታል። «የሚገርመው» ትላለች «ኮድ ማድረግ ራሴን ነው ያስተማርኩት። ኦንላይን ነው የተማርኩት። መጀመሪያ ላይ የፕሪ ሜዲሲን ተማሪ ነበርኩ። ዶክተር ልሆን ነበር። » ይህ ግን ሳይሆን ቀረ።  ዮሃና የህክምና ትምህርቷን ለአራት ዓመት ያህል ከተከታተለች እና የመጀመሪያውን ክፍል ከአጠናቀቀች በኋላ ነው አቅጣጫዋን ሙሉ በሙሉ ለውጣ ወደ ቴክኖሎጂው ሙያ የገባችው። ሀሳቧን ምን አስቀየራት? « ሜዲሲን ስማር መጀመሪያ ላይ አስቤበት አልነበረም። ዶክተር መሆን፣ ኢንጂነር መሆን በቤተሰብም የሚበረታታ ነው። እና የሶስተኛ አመት ተማሪ እያለሁ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የስራ ላይ ልምምድ እያደረኩ ነበር።» እዛም የድንገተኛ ክፍል ውስጥ የነበራት ተሞክሮ ሀሳቧን እንዳስቀየራት ዮሃና ገልፃልናለች። 

Äthiopien Addis Abeba eQUB financial technologies
ምስል eQUB financial technologies

ኢትዮጵያ ውስጥ እቁብ በተለምዶ የሚጣለው ሰዎች በአካል ተገናኝተው ነው። ይህ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ የሆነው መተግበሪያ ደግሞ የእቁብ ተሳታፊዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በቴክኖሎጂ አማካኝነት አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል። ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉ መተግበሪያ ላይ ማግኘታቸው ዋና አላማዋ ለሆነው ዮሃና በእቁብ መተግበሪያ ልታሳምናቸው ችላ ይሆን?  ለዚህም ከተጠቃሚዎቻችን ብዙ አስተያየቶች አሰባስበናል የሚትለው ዮሃና «ለምሳሌ በተለያዩ ቋንቋዎች ማቅረብ እንዳለብን ተረድተናል። ይህም ከሁለት ወራት በኋላ ይፋ የምናደርገው ይሆናል። ከዚህም ሌላ የአከፋፈሉ ሁኔታ ላይ ማሻሻያ አድርገናል» ለዚህም ከተለያዩ ባንኮች ጋር እቁብ እየሰራ እንደሆነ ዮሃና ትናገራለች። 

Äthiopien Addis Abeba eQUB financial technologies
ምስል eQUB financial technologies

የእቁብ መተግበሪያ ላይ ባለፈው አንድ ዓመት «የተለያዩ ማሻሻዮችን አድርገናል» የምትለው ዮሃና እስካሁን መተግበሪያው 10 ሺ ጊዜ ዳውንሎድ መደረጉን እና 7000 ያህል ሰዎች በመደበኛ ሁኔታ አገልግሎቱን በየወሩ እየተጠቀሙ እንደሆነ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊዋ ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች።  ይህ ቁጥር ግን ሲጀምሩ ተስፋ ካደረጉት ቁጥር በ 20 000 ያነሰ ነው። 

ዮሃና የምትሰራውን ስራ ትወደዋለች። እንደእርሷ ሙያ ለመቀየር የሚፈልጉ ሰዎችን ለማደፋፈር የምትሞክረው የራሷን ተሞክሮ በማካፈል ነው። « ከአንድ ሙያ ወደሌላ ለመቀየር ስንፈልግ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል ነው ወይስ አይደለም ፤ ምን ያስፈልገዋል ብሎ ማጤን ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ ትግዕስት ነው። ረዥም ጊዜ ሊፈጅ ይችላል።» ትላለች ዮሃና።

ወጣቷ ከሀይስኩል ጀምሮ ትምህርቷን የተከታተለችው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነው። በተለያየ ጊዜም ለስራዋ የሚረዳትን ነገር ለመፈፀም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ትጓዛለች። መኖር የምትፈልገው ግን ኢትዮጵያ ነው።
ከእቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ ተባባሪ መስራች እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ዮሃና ኤርሚያስ ጋር የነበረንን ቆይታ በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ