1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜቴክ ሹማምንት ምዝበራ

ረቡዕ፣ ኅዳር 5 2011

የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ባለፈዉ ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ኃላፊዎች የተዘፈቁበትን ሙስና ደረጃ ይፋ አድርገዋል። ይህ ግዙፍ ድርጅት ላለፉት ስድስት ዓመታት የዉጭም ሆነ የአገር ዉስጥ ግዥ ሲፈፅም ያለ ምንም ጨረታ መሆኑን ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/38FpP
Police have detained Major General Kinfe Dagnew, former Director General of the state-owned Metals and Engineering Corporation
ምስል Ethiopian government communication

የሜቴክ ሹማምንት ምዝበራ

እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራርያ የዉጭ አጋር ግዥ ሲፈፀም አለማቀፍ ጫረታ ሳይወጣ፣ ለሚገዛዉ እቃ ጥራትም ሆነ ከዋጋዉም አንፃር ዉድድር ሳይደረግ የተፈፀመ ነዉ ብለዋል። ይህ የዉጭ ግዥ ያለ ጫረታ ስደረግ ከአንድ ተቋም ብቻ ከ40-50 ድግግሞሽ እንዳለበት አቶ ብራሃኑ ጠቅሰዋል።

ድርጊቱ ከፋይናንስና ኤኮኖሚ ተንታኞች እስከ ተራ ዜጋ ድረስ ትልቅ ጥያቄ አጭሯል። አንዱ ጥያቄ ይህን የሚያክል ግዙፍ ኩባንያ ለስድስት አመታት ያለ ጨረታ እንዴት ግዥ ልፈፅም ይችላል የሚል ነዉ?

የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ሰኔ 2002 በመተዳደርያ ደንብ ቁጥር 183/2002 እንደ የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ መቋቋሙን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ በመግለጫቸዉ ወቅት ተናግረዋል። ኮሮፖሬሽኑ ሲመሰረት «በ10 ብሊዮን ብር የተፈቀደና 3.1 ቢሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በአይነት የተከፈለ» ነዉም ብለዋል። ቀደም ስል በመከላክያ ስር የነበሩት እንደነ ናዝሬት የልብስ ስፌት ፋብርካና የመከላክያ እንዱስትርዮችን ምርት የሚያመርቱ፣ የሚጠግኑና የሚያድሱ ድርጅቶች በሜቴክ ስር እንድጠቃለሉ መደረጋቸዉንም አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ አብራርተዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምርታቸዉን በማናጅሜንት እየተከታተሉ የሚገኙ አቶ ታፈረ ወርቁ የሜቴክ ጥፋት የሚጀምረዉ መተዳደርያ ደንቡን ከመጣስ ነዉ ይላሉ። አቶ ታፈረ ወርቁ እንደሚሉት አንድ መስራይ ቤት ግዢ መፈፀም ካቀደ ጨራታ ማዉጣት እንዳለበት ተቋሙ የሚተዳደርበት ደንብ ያስገድደዋል። በተለየ ሁኔታ ያለ ጨረታ የቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ የዉስጥም ሆነ የዉጭ ግዢ የሚፈፀመዉ እቃዉን የሚያቀረበዉ ድርጅት ብቸኛ አቅራቢ ከሆነ ብቻ ነዉ ሲሉም አቶ ታፈረ አክሎበታል። የሜቴክ ግን ምንም « ምክንያት የለዉም፣ ለንግግርም የሚበቃ አይደለም» ባይ ናቸዉ። የመተዳደርያ ደንቡን በመጣስ የዉጭም ሆነ የዉስጥ ግዢ ሲደረግ ተከታትሎ መቆጣጠር የነበርበትም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና ፓርላማ ያለዉ የበጀት እንድሁም የፋይናንስ ቋሚ ኮምቴ መሆን እንደነበረበት አቶ ታፈረ ገልፀዋል።

Äthiopien verhaftet 63 wegen Verdachts auf Menschenrechtsverletzungen, Korruption. Der Generalstaatsanwalt Berhanu Tsegaye sagte heute (03.11.2018) lokalen Journalisten, dass die Inhaftierung nach fünf Monaten Ermittlungen erfolgt.
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

የ37 ብሊዮን ብር የዉጭ ግዥ ስፈፀም «ከኮርፖሬሽኒ የበላይ አመራሮች ጋር የጥቅም ግኑኝነት ያላቸዉ ሰዎች፣ የድለላ ስራ በመሃል እየሰሩ ኮሚሺን የሚከፈልላቸዉ፣ ሰዎቹ ለአመራሮቹ የቅርብ ዘመድ የሆኑ» ናቸዉ ሲሉም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ አጋልጠዋል። እንደእሳቸዉ ማብራርያ እነዚህ ደላሎች የዉጭ አገር ኩባንያዎችም በድለላ ለግዢ ሲያመጡ ሸቀጦቹ ከመቶ እስከ አራት መቶ ተጨማሪ ዋጋ በማድረግ የምፈፀሚገዙ ናቸዉ። ደላላዎቹ «ባገር ዉስጥ ካከማቹት ሃብት በተጨማሪ ወደ ዉጪ ያሸሹትም እንዳለ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል።

ሜቴክ በአቅራብዮች፤ በህዝብና በአገር ላይ የምያደርሰዉ ጉዳት

ሜቴክ የወሰደዉ አካሄድ የዉስጥም ሆነ የዉጭ አገር የእቃ ወይም የአገልግሎት አቅራብዮቹን ዉድድርን እንደሚያቀችጭ፣የማኔጅሜንት ባለሙያዉ አቶ ታፈረ ገልፀዋል።
ታክስ ከፋዩ ሕዝብ መንግስትን አምኖ የሰጠዉን ገንዘብ ለታቀደዉ እቃዎች እና አገልግሎቶች ሳይዉሉ ቀርተዉ ባለስልጣናቱ ሲመዘብሩት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከመጠን ያለፈ ጫናና የብቃት ማነስ ወይም ፈረንጆቹ እንደምሉት «deadweight loss» እንደሚያስከትል በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የእኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ሳምሶን ገብረስላሴ ለDW ተናግረዋል።

የሙስና ወንጀል ምርመራ ግኝቶች ከተባሉት ዉስጥ የመርከብና አዉሮፕላን ግዢም ይገኝበታል።ንብረትነታቸዉ የኢትዮጵያ ባህር፣ ትራንዚትና ሎጅስትክስ የሆነ አባይና አንድነት የተሰኙት መርከቦች ከ28 ዓመት በላይ ስላገለገሉ የድርጅቱ ቦርድ ለመሸጥ መወሰኑ አቶ ብርሃኑ በመግለጫቸዉ ጠቅሰዋል። ሜቴክም መርከቦቹን ቆራርጦ ለብረት ለመጠቀም ቢገዛም መልሶ ብዙ ሕገወጥ የባህር ስራ እንዲሰሩ መደረጋቸዉን፣ በኋላም ለአንድ የቻይና ኩባንያ በ3.276 ሚሊዮን ብር መሸጣቸዉን የሺያጩ ገንዘብ ግን የዉሃ ሽታ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ አክሎበታል።

አቶ ብርሐኑ መግለጫዉን ከሰጡ ከአንድ ቀን በዋላ የሜቴክ ዋና ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ተይዘዉ ቁጥጥር ስር ዉለዋል። ከጄኔራሉ በፊት የኩባንያዉ ምክትል ኃላፊን ጨምሮ የተያዙ የ27 የቀድሞ ሹማምንታት ስም ዝርዝር ወጥቷል።

ትራንስፓራንሲ ኢንቴርናሽናል የተሰኘዉ ተቋም በባለፈዉ ዓመት የሙስና ይዞታ መዘርዘሩ ኢትዮጵያን ከ180 አገራት 107 ላይ አስቀምጧታል። ኢትዮጵያ በእርዳታ እና ብድር  በዓመት  ከ2 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላርስ እንደምታገኝ ይገመታል።ይሕንኑ ያሕል ገንዘብ ግን መልሳ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝዉዉር እንደምታጣ የፋይናንስ ባለሙያዎች ዘገባ ያመለክታል።

ሙሉ ዝግጅቱን ለመከታተል አዉድዮን ይጫኑ።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ